Monday, 11 September 2017 00:00

ግልጽ ደብዳቤ፡- ለክቡር ከንቲባ ለአቶ ድሪባ ኩማ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ጉዳዩ፡- ሚሊኒየም አዳራሽ ፈርሶ፣ ባለ 5 ኮከብ ኮንቬንሽን ሴንተር


      ክቡርነትዎ፤ ይህችን አነስተኛ ማስታወሻ የጻፍኩት፣ እንደ አንድ የአገር ተቆርቋሪ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪነቴ ነው። እንደሚታወቀው፤ የኢትዮጵያ ሚሊኒየምን ለማክበር በታቀደ ጊዜ፣ በወቅቱ  ሰፊ አዳራሽ ባለመኖሩ፣ ሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲን፣ አዳራሹን ለመስራት ቃል ገቡ፡፡ ይሄን ተከትሎም ለመሥሪያ የሚሆን ቦታ (ካልተሳሳትኩ፣ከሊዝ ነፃ የሆነ) ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መግቢያ ላይ ተረክበው፣ አዳራሹ በፍጥነት ተሰራ፡፡ ለታለመለት ተግባርም ዋለ፡፡ ሚሊኒየሙ፣ በዘፈንና በጭፈራ በደመቀ ሁኔታ ተከበረ፡፡ ሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲን፣ ቦታውን ሲረከቡ ግን፣ ይህ በጥድፊያ የተሰራ ኮንቴነር አዳራሽ ፈርሶ፣ በምትኩ በአውሮፓ ስታንዳርድ፣ ዘመናዊ አዳራሽ እንደሚገነቡ ቃል መግባታቸውን  አስታውሳለሁ፡፡
 እነሆ፤ ኢትዮጵያ ሚሊኒየሙን ካከበረች ድፍን አስር አመታት አስቆጥራለች፡፡ የዛሬ 10 ዓመት ለጊዜው ተብሎ የተሰራው ሚሊኒየም አዳራሽ፣አሁንም ባለበት ነው። የተባለው ደረጃውን የጠበቀ አዳራሽ ይሄን ሁሉ ዓመት አልተገነባም፡፡ በእኔ እምነት ሼክ መሀመድ፣ይሄንን አዳራሽ አፍርሰው፣ ባለ አምስት ኮኮብ የሆነ ዓለም አቀፍ ደረጃው የጠበቀ አስደናቂ አዳራሽ ማስገንባት  አያቅታቸውም። ከተማችን አዲስ አበባ፣ የአፍሪካ ዋና ከተማ መሆኑዋ ይታወቃል፡፡ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ለማካሄድ የምትመረጥ ከተማም እየሆነች መጥታለች። በዚህም የተነሳ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ  አዳራሽ እንደሚያስፈልጋት እሙን ነው፡፡
ክቡር ከንቲባ፡-
ሚሊኒየም አዳራሽ ላለፉት 10 ዓመታት በርካታ የሙዚቃ ድግሶችንና ኤግዚቢሽኖችን እያስከፈለ ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ አዳራሽ ለመስራት የሚያስችል አቅም እንደገነባ መገመት ይቻላል፡፡ እንደ ነጋዴ፣ እንዲህ ከፍተኛ ገቢን የሚያስገባ አዳራሽ ማፍረስ ሊያጓጓ ይችላል፡፡ ነገር ግን ቃል በተገባው መሠረት፣ ስታንዳርዱን የጠበቀ አዳራሽ መገንባት እንዳለበት አምናለሁ፡፡ ይሄንን የማስፈጸም ሃላፊነት ደግሞ የከተማ መስተዳድሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ከውጪ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ታላላቅ የሀገር መሪዎችና ጎብኚዎች፣ መጀመሪያ የሚመለከቱት ቦታ ላይ ተገትሮ የሚገኘው ቅርፅ የለሽ ኮንቴነርና ድንኳኖች ፈርሰው ፣አዲስ አበባ የአፍሪካን መዲናነቷን የሚመጥናት፣ ባለ አምስት ኮከብ Convention Center መገንባት አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ አገር ወዳድ ለሆኑትና ለኢትዮጵያ በርካታ ጥሩ ነገሮች ላበረከቱት ባለሀብት ሼክ መሀመድ፣ ያለኝን አክብሮት ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡  ነገር ግን ለጊዜያዊ ችግር ታስቦ የተሰራው 10 ዓመታት ያስቆጠረው ሚሊኒየም አዳራሽ፣ በአዲስ ደረጃውን የጠበቀ አዳራሽ መተካት ያለበት ይመስለኛል። መስተዳደሩም ሃላፊነቱን በአፋጣኝ መወጣት ይገባዋል ብዬ አስባለሁ፡፡  
 በላይ ጨብሲ /ልማታዊ ሀብት/
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.    

Read 2511 times