Monday, 11 September 2017 00:00

ይድረስ ለሀገሬ ኢትዮጵያ ወዳጅ ለታላቋ ሀገር ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ መንግሥት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

    አመልካች እኔ ሳምሶን ጌታቸው ተክለሥላሴ, በሀገረ ኢትዮጵያ የዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ነዋሪ ስሆን፤ ሰሞኑን በሀገሬ ላይ በተከሰቱ አንዳንድ አስፈሪ የፖለቲካ ጉዳዮች የተነሳ, ይህንን የአቤቱታ ደብዳቤ ለመጻፍ ተገድጃለሁ፡፡ ይህን አቤቱታ በዚህ መልክ ከመጻፌ በፊት ነገሮች በራሳቸው ጊዜ ወይም በሆኑ የሀገራችን ሰዎች አማካይነት ይስተካከሉ ይሆናልም ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ሰው እየተነሳም በትላልቅ የሀገር ጉዳዮች በዚህ መልኩ አቤቱታ ላሰማ ካለም ለአሰራርም ሆነ ለውጤታማነቱ አስቸጋሪ እንደሆነም ስለማውቅ እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች በግሌ ለብዙ ጊዜያት ዝም ማለትን መርጬ ነበር፡፡ ነገር ግን የነገሮች አደገኛ ጎርፍ፣ ሀገሬንና ሕዝቦቿን ባለንበት ጠራርጎ ሊወስደን እየተንደረደረ መሆኑን ስመለከት፤ ቢያንስ የአቅሜን ማበርከት አለብኝ ብዬ በመወሰኔና በዚያም መንፈስ ሆኜ ይኼንን ደብዳቤ ልጽፍ ወደድሁ፡፡
በመጀመሪያ ከሁሉ አስቀድሜ ለዘመናት የሀገሬ ኢትዮጵያ የልብ ወዳጅ፣ የችግሯ ጊዜ ሁሉ ፈጥኖ ደራሽ፣ የዕድገቷና የሥልጣኔዋ ጉዞ ፍፁም አጋዥ እና ደጋፊ ለሆነችው፣ የዓለም ኃያሏ ሀገር ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ ሕዝብ እና መንግሥት የከበረ ሠላምታዬን በታላቅ ትህትና አቀርባለሁ፡፡ በዚሁ የተለየ አጋጣሚ ሀገሬ እና ሕዝቦቿ ወደ ሥልጣኔ በሚያደርጉት እርምጃ እና ጉዞ ሁሉ ከአሜሪካ ሕዝብ እና መንግሥት ለተደረገልንና እየተደረገለን ስለሚገኘው ውለታ፣ እንዲሁም ይህንኑ ከቅንነት፣ ከርኅራኄ እና ከፍቅር የመነጨ ድጋፍ ባለኝ የዜግነት ድርሻዬ በሀገሬ ስም ከልብ የመነጨ ምሥጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ፡፡ 
በመቀጠልም ሀገሬ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሠዓት አንገት ለአንገት እየተናነቀች ከምትገኘው የከፋ ድህነት እና ኋላቀርነት ባሻገር፣ በቀላሉ የማይታይ የፖለቲካ ችግርም እየተስተዋለባት እንደሚገኝ በአደባባይ የዋለ ሀቅ ከሆነ ከራርሟል፡፡ የፖለቲካ ችግሯ በተለያየ ደረጃና መንገድ ተጉዞ አሁን የደረሰበት አደገኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ፣ ከወዳጃችን የአሜሪካ መንግሥት የተደበቀና ድንገተኛ ክስተት እንዳልሆነም ይታወቃል፡፡ ይህንንም ስል የአሜሪካ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት የሚስተዋሉ መሠረታዊ የአስተዳደርና የአካሄድ ችግሮችን፣ በዚህ ደረጃ ሥር ሳይሰዱ መስተካከል ይችሉ ዘንድ በተለያዩ መንገዶች የወዳጅ ምክሮችን ሲያስተላልፍ እንደነበር ይታወሳልና ነው፡፡
የሆነው ሆኖ ለተፈጠረው የፖለቲካ ውጥንቅጥ የመፍትሔ አካል ሆኖ ከመገኘት ይልቅ ይበልጥ የሚያወሳስብ እና የከፋ መልክ እንዲይዝ የሚያደርጉ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ ይገኛል፡፡ በእኔ ዕይታ እና አስተውሎት ከመንሥዔው ባልተናነሰ የችግሩ ዋነኛ አባባሾች እና አወሳሳቢዎች ደግሞ አንዳንድ በአሜሪካ ሀገር በነዋሪነት የሚገኙ የኢትዮጵያ ሰዎች ናቸው፡፡ የዚህ የአቤቱታ ማመልከቻ ደብዳቤዬ ዋነኛ መነሻዎቹም እነሱ ናቸው፡፡ እነዚሁ ወንድሞቻችን የአሜሪካ ሕዝብ እና መንግሥት ባመቻቹላቸው የኑሮ፣ የትምህርት እና የሥራ ዕድል ተጠቅመው፤ በተማሩት ትምህርት፣ በቀሰሙት ዕውቀት፣ በተግባር በተመለከቱት የሥልጣኔ ምጥቀት መሠረት፣ የሀገራቸውን የኢትዮጵያ አንድነት አስጠብቀው እና የሕዝባቸውን የፍትሕ፣ የዴሞክራሲ እንዲሁም የሥልጣኔ ጥማት ለማርካት እንደመጣር፣ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ትልቅ የፖለቲካ ሥህተት የሚታረምበትን መንገድ እና የተሻለ አማራጭ እንደመፈለግ፤ በተቃራኒው እነሱ ግን ሁኔታውን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ጭራሽ ወደ ከፋ ሁኔታ እንዲያመራ እና እንዲባባስ በማድረግ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያን ሊበታትን እና ሕዝቦቿን ሊያበጣብጥ በሚችል ደረጃ፣ በክልላዊ ብሔርተኝነት ስም በጥላቻ ላይ የተመሠረተ የጎሣ ፓለቲካ ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ ሕዝብ አሰፋፈር እና ስብጥር፣ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ እና ሐይማኖታዊ አኗኗር፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትሥሥር እንዲሁም የደም ለደም ውህደት ምክንያት ፈፅሞ ሊተገበሩ ቀሮቶ ሊታሰቡ የማይችሉ የተሳሳቱ የጎሣ ፖለቲካ አስተሳሰቦችን፣ በመስበክ እና በመቀስቀስ፣ ዛሬን ብቻ አሸናፊ መስለው ለማለፍ በመሞከር፣ ሕዝባችንን በተሳሳተ እና ፍፁም አደገኛ በሆነ በክልል ብሔርተኝነት ላይ በተንጠለጠለ የጎሰኝነት ሥነ ልቦና ላይ እንዲገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ የዚሁ ድርጊታቸው ውጤትም ከተራ ቅስቀሳነት አልፎ መርዛማ ፍሬውን አፍርቶና በመጠኑም ቢሆን በስሎ በተግባር በተለያዩ ሁኔታዎች መታየት ጀምሯል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገር የተከሰቱ እንቅስቃሴዎችን መመልከት ይቻላል፡፡
የሀገራችን ሕዝቦች ለዘመናት ሲታገሉለት የኖሩትን የፍትሕ፣ የመብትና እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመጥለፍና ተገቢውን አቅጣጫ በማሳት፤ ጥላቻ አዘል የጎሣ ፖለቲካ ያለከልካይ እየሰበኩ እና እያራገቡ ሀገራችንን የመበተን አቅሙን ከዕለት ወደ ዕለት በዕጃቸው እያስገቡት ይገኛል፡፡ ዛሬ ላይ ይኸው ድርጊታቸው ምናልባት ጀብድ እንደሚወድ ትንሽ ልጅ “እኔ ነኝ ይኼን ያደረኩት፣ ጉልበቴም እዚህ ድረስ ነው” ከማለት ያለፈ አንዳች ዘላቂ ጥቅም በግላቸው አያስገኝላቸውም፡፡ ነገር ግን ችግሩ የሚጀምረው ስህተታቸው ሥር ሰዶ መጨረሻው ደረጃ ላይ የደረሰ ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በእነሱ ያልተገባ የፖለቲካ ጨዋታ የመከራ ደመና በሀገሬ ኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እያንዣበበ እንደሚገኝ ይሰማኛል፡፡ አይበለውና ይኼው የመከራ ደመና ከዘነበ፤ ሀገሬ ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በቅርቡ በመካከለኛው ምሥራቅ አንዳንድ ሀገራት ከተከሰተው ያልተናነሰ፤ ምናልባትም ከዚያም በከፋ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አሰቃቂ የሕዝብ ፍጅት እና ዕልቂት ልታስተናግድ ትችላለች፡፡
የእነዚሁ ወንድሞቻችን ከበዙ አደገኛና አጥፊ ድርጊቶቻቸው መካከል እንደ አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ብሞክር፤ ኢትዮጵያን እነሱ በመሰላቸውና በዘፈቀደ እንዲሁም ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅማቸው ሲሉ ባሴሩበት መንገድ ብቻ፣ የወደፊት ሀገራችን ብለው የዛሬዎቹን የክልሎች ስያሜ ተከትለው፣ የራሳቸውን ድንበር በወረቀት ላይ አካለው እስከመጨረስ ደርሰዋል፡፡ ከጅምሩ የተነሱበት ሀገርን የመገነጣጠል ፖለቲካቸው በዕውነተኛ የሕዝቦች ጥያቄ ላይ የተመሠረተ ስላልነበረ እና እነሱ ራሳቸው በፈበረኩት የልብወለድ ታሪክ ለይ የተንጠለጠለ በመሆኑ፤ ጉዳዩን በተጨባጭ መሬት ላይ ለማውረድ በሚጥሩበት ጊዜ ደግሞ የማይያዝና የማይጨበጥ ሆኖ ሲያስቸግራቸው ይታያል፡፡ ለዚህም የሚነድፏቸው የድንበር ወሰን አመላካች ካርታ፣ አንደኛው የእኔ ግዛት ብሎ ያሰፈረው እና ሌላኛውም የእኔ የድንበር ወሰን ብሎ ከደነገገው ጋር እርስ በእርስ ተደራርቦ መገኘቱን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህን ድርጊት አሁን ላይ እንደ ቀልድ አይቶ መተው ቢቻልም፤ በሂደት ግን በሀገራችን ሕዝቦች መካከል ያልተገባ ከፍተኛ እና ማባሪያ የሌለው ግጭት የማስነሳት ዕምቅ አቅም ያለው እና ጊዜውንም ጠብቆ ሊፈነዳ የሚችል አጥፊ ተግባር ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ዛሬ ላይ ተሁኖ በዝምታ ማለፍ በተዘዋዋሪም ቢሆን የዚያ የጥፋት ድርጊት ተባባሪ እንደመሆን ያስቆጥራል፡፡ እንዲህ ያለውን አጥፊ ድርጊት የረጅም ዕደሜ እና ሠፊ ታሪክ ባለቤት በሆነች ሉዐላዊት ሀገር ላይ ለመተግበር ከመሞከር የባሰ ምንስ በደል ምንስ ሕገ-ወጥነት ይኖራል?
ይኼንኑ ድርጊት በማስረጃነት ለመጥቀስ ያህል ከዚህ ደብዳቤ ጋር በአባሪነት በብዙ ሰዎች ቅብብሎሽ በየኢንተርኔቱ ለመቀስቀሻነት በመሰራጨት ላይ የሚገኙ በየብሔሩ የተሸነሸነችውን የኢትዮጵያ ካርታ የሚያሳይ ምስል አያይዣለሁ፡፡
በእውነቱ እንዲህ ያለው የጭካኔ ሥራ አርቃቂ እና አስፈፃሚ ሆኖ መገኘት፣ በታሪክ ተወቃሽ ከማድረጉም አልፎ ጊዜውን ጠብቆ የሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ያልተገባ ተግባር እንደሆነ፣ በዚህ መልኩ ያለፉ ሀገራትን ልምድ ወደኋላ ዞር ብሎ መመልከት ብቻ በቂ ትምህርት ነበር፡፡ ከአንድ ሀገሩን እና ሕዝቦቿን በቅንነት ከሚወድ ዜጋ በሚጠበቅ ደረጃ የሚያኮራ ድርጊት እንዳልሆነም ይታወቃል፡፡
አሜሪካንን በሚያህል የአንድነት፣ የዴሞክራሲ፣ የሕዝቦች ዕኩልነት፣ የሥልጣኔ፣ የዕውቀትና ብልፅግና ተምሣሌት በሆነች ሀገር ላይ ሲኖሩ፤ የተማሩትን፣ ያዩትን፣ የቀሰሙትን ዕውቀት እና ልምድ ወደ ሀገራቸው በሚመጥን መልኩ አምጥተው ለመተግበር እንደመጣር፣ ያን ያህል ዕውቀት እና ልፋት በማይጠይቀው የሀገርን አንድነት በመበታተን እና በማፈራረስ ተግባር ላይ ተሰማርቶ መገኘት ምን ይባላል፡፡ ይህም ድርጊታቸው የጋራ ሀገራችን ለሆነችው ኢትዮጵያ አውዳሚ ሲሆን፤ ዕድሉን ሰጥታ በከፍተኛ ወጪ ላስተማረቻቸው አሜሪካ ደግሞ ኪሳራ ነው፡፡ በእርግጥ ለቅንነት እና ለፍቅር ልቡን መስጠት ለማይችል ሰው የዕውቀት ዕድል ቢመቻችለትም ትርፉ እንዲህ ያለው ጥፋት ነው፡፡ መገለጫውም አፍራሽ ሥራ ነው፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡ ሆኖም ይህን ስል ግን ከአስቸጋሪዎቹ የሀገራችን ሰዎች በተቃራኒው ቁመው፤ ዕድሜያቸውንና ዕውቀታቸውን ሁሉ ለሀገራችን ዕደገት፣ ሰብአዊ መብቶች መከበር፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ብልፅግና የሚተጉ ብዙ ቁጥር ያላቸው ወንድሞቻችንም መኖራቸውም የታወቀ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ካላት ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት አንፃር፣ ብዙም መረጋጋት በማይስተዋልበት የምሥራቅ አፍሪካ ክልል ከመገኘቷም ጭምር፤ የእሷ መተራመስ በቅድሚያ የገዛ ሕዝቦቿን በሚዘገንን መልኩ የመከራው ዋና ተጠቂዎች ቢያደርግም፤ የውድቀቱ ንዝረት እና ርዕደት ደግሞ በመላው ዓለም ከጫፍ እስከ ጫፍ በሁሉም አቅጣጫ መሰማቱ እና ማናወጡ አይቀርም፡፡ በዚህም ምክንያት ዓለም ለብዙ ጊዜያት ሲታገለው እና ሲፋለመው ረዥም ርቀት የተጓዘበትን የሽብርተኝነት ተግባር፣ እንደ አዲስ እንዲያንሰራራ እጅግ የተመቻቸ ሁኔታን ስለሚፈጥርለት፣ የዓለምን ሽብርተኝነትን የመታገልና የመደምሰስን ልፋት መልሶና ቀልብሶ በብዙ ርምጃዎች እንደገና ወደኋላ የሚመልስ ውጤትም ማስከተሉ አይቀርም፡፡ በተጨማሪም በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱና አስከፊ ከሚባሉ የሕዝብ ፍልሰትና ስደት ታሪኮች ባልተናነሰ ምናልባትም የባሰ ሁኔታ በዓለም ላይ ሊያስከስት ይችላል፡፡
ስለሆነም ያ አሰቃቂ ጥፋት እና መከራ ከመከሰቱ በፊት፣ በእኔ ዕይታ የአሜሪካ መንግሥት ጉዳዩን ትኩረት ሠጥቶ በጥሞና ቢመለከተው ነገሩን በአጭሩ ማስቀረት የሚያስችል መፍትሔ እንደሚገኝለት እተማመናለሁ፡፡ የአሜሪካ ምድር ለሰው ልጆች ሁሉ የመብትና የነፃነት ምድር እንደሆነች ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ መብትንም ሆነ ነፃነትን በመጠቀም ጊዜ ደግሞ፣ በሌሎች ሰዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ወይም ውጤት እንዳያመጣ በሚገባ መጠንቀቅ ዋነኛው የመብቱ ተጠቃሚ ኃላፊነት መሆኑም የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ከላይ ለመጥቀስ በተሞከረው መሠረት በሀገሬ ኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ የክልል ብሔርተኝነትን አስተሳሰብ በማቀጣጠል ላይ ያሉት ወንድሞቻችን፣ በመሠረታዊ ደረጃ ይህን የመብት አጠቃቀም አግባብነት ባላገናዘበ ወይም ሆን ተብሎ ወደ ጎን በተወ መልኩ፣ የአሜሪካ ሀገር ነዋሪነታቸውን ብቻ ተገን በማድረግ እየፈፀሙ ስለመሆናቸው አልጠራጠርም፡፡ በዚህም ምክንያት እነዚሁ የሀገሬ ሰዎች የተሰጣቸውን መብት እና ነፃነት ላልተገባ ዓላማ እያዋሉት እንደሚገኙ አምናለሁ፡፡ በመሆኑም ይህ ድርጊታቸው ኢትዮጵያን ማለቂያ ወደሌለው የጎሣና የማንነት ጥያቄ ትርምስ፣ የድንበር ይገባኛል ውዝግብ፣ የነፃ አውጪዎች ጋጋታ፣ የሐይማኖት ቡድንተኝነት መዘዝ እናም በአጠቃላይ አሰቃቂ የእርስ በእርስ መተላለቅ ወደሚያስከትል የመከራ ገደል እየገፋት ይገኛል፡፡
አሜሪካ ሽብርተኝነትን አጥብቃ የምትኮንነው እና የምትዋጋው የዘመናችን አስከፊ የሰው ልጆች ሁሉ ጠላት የሆነ ተግባር እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ሽብርተኝነት ደግሞ ብዙ መልክ እና መገለጫዎችም እንዳሉት እርግጥ ነው፡፡ በእኔ አረዳድ ለማንኛውም ዓላማ ሲባል፤ በሠላማዊ ሕዝቦች መካከል እልቂትን የሚፈጥር ቅስቀሳ ማድረግ፣ ነውጥን መጠንሰስ፣ ማስተባበር ብሎም ተግባራዊ ማድረግ፣ የሀገርን ብሔራዊ አንድነት የሚያናጋ የትርምስ ተግባራት ማቀድና መሳተፍ፣ በአጠቃላይ በሰው ልጆች እና በሀገር ላይ የሚፈፀሙ አውዳሚ ተግባራት ሁሉ የሽብር ድርጊቶች ናቸው፡፡ ጥፋቱ በገዛ ሀገር እና ሕዝብ ላይ ሲፈፀም ደግሞ ከሽብር ድርጊትነቱ በተጨማሪ የሀገር መክዳትን ተጠያቂነትም አብሮ የሚያስከትልና የሚያካትትም ይመስለኛል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት ከሌሎች ሀገራት የተቃውሞ ፖለቲካ አራማጆች በተለየ፣ ለእኛዎቹ የኢትዮጵያ ሰዎች ሠፋ ያለ የመጫወቻ ሜዳ ሳያመቻችላቸው አልቀረም፡፡ ይህም ለሀገራችን ካለው የወዳጅነት ስሜት የመጣ እንደሆነ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህን የተመቸ ዕድል በኃላፊነት ተጠቅመው ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው የተሻለ የፖለቲካ አማራጭ እንደማስተዋወቅ፤ አሜሪካንን እንደ የጦር ዕዝ ሠፈር በማስመሰል ኢንተርኔትን ደግሞ እንደ ጦር መሣሪያ በመቁጠር የውጊያ መመሪያ መስጫ የማድረግ ሙከራዎች እየተስተዋሉ ይገኛል፡፡ ይህም መብት እና ነፃነትን በአግባቡ የመጠቀምን አስፈላጊነት እና ግዴታን ወደጎን ከመተው አንዳንዴም ከግድየለሽነት በመነጨ መልኩ ስለመሆኑ፣ ከድርጊታቸው በመነሳት እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፡፡
ታላቋ አሜሪካ ዛሬ ለምትገኘው ሀገሬ ኢትዮጵያ በፍፁም ወዳጅነት እና አጋርነት ያበረከተችው አስተዋጽኦ እና ድጋፍ በሀገሪቱ ታሪክ ሁሉ የሚረሳ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ሁሉ በወንድማዊ ስሜት የተደረገልን ልባዊ ድጋፍ ለሁል ጊዜ ሲዘከር ይኖራል፡፡ በመሆኑም አሜሪካ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ፣ ስለኢትዮጵያ ከእኛ ከዜጎቿ ባልተናነሳ ከፍተኛ አቅሟን አውጥታ ስትለፋ ኖራለች፡፡ የዚህ ሁሉ የአንድ ክፍለ ዘመን ዕድሜ በላይ የአሜሪካ ሕዝብ እና መንግሥት ልፋት እና ጥረት ደግሞ የተረጋጋችና የበለጸገች ኢትዮጵያን የማየት ራዕይ እንደሆነ የታወቀ ሀቅ ነው፡፡
ስለሆነም ታላቋ ሀገር ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ባላት እጅግ የላቀ ወዳጅነት፣ አጋርነት እና ተሰሚነት ምክንያት የሚከተሉትን አንኳር ነጥቦችን የያዙ ሁለት ጥያቄዎችን በአክብሮት ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡
1ኛ) ዩ ኤስ አሜሪካ በዓለም መድረክ በተግባር ከምትታወቅበት ለፍትሕ፣ ለሰው ልጆች መብትና ዴሞክራሲ ከመቆሟ አንፃር፤ በአሜሪካ የሚኖሩ የአንዳንድ ወንድሞቻችን ድርጊት በእርግጥ በዚያ ትክክለኛ ማዕቀፍ ውስጥ መሆኑን የአሜሪካ መንግሥት እንዲያጤነው፣ አጢኖም ከላይ እኔ በዘረዘርኩት መጠን የአካሄድ ስህተት መኖሩ ከታወቀ ደግሞ፣ ይህን የተወገዘ እና ያልተገባ ድርጊት በሀገረ አሜሪካ ላይ ቁጭ ብለው በገዛ ትውልድ ሀገራቸው ላይ እየፈፀሙ የሚገኙትን የሀገራችንን ሰዎች ተግባር ጉዳዩን ከሕግ አግባብነት፣ በሀገሬ ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ ላይ ከሚያስከትለው ጉዳትና ውድመት አንፃር ተመልክቶ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ
2ኛ) ከላይ ባልተገባ ድርጊታቸው ከወቀስኳቸው ወንድሞቻችን ባልተናነሰ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ለምትገኝበት አስፈሪ የፖለቲካ ሁኔታ እና ውጥንቅጥ፣ ከጅምሩም ሆነ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የሀገሬ መንግሥት ዋናው ባለድርሻ አካል መሆኑን አምናለሁ፡፡ የሆነው ሆኖ አሁን የደረስንበት አደገኛ ሀገራዊ ሁኔታ ከመወነጃጀል አልፈን ነገሮችን በጣም በፍጥነት፣ በቅንነት እና በእርቅ መንፈስ ለማስተካከል ካልተጣረ፣ መጪው ቅርብ ጊዜ ለሀገሬ ኢትዮጵያ ማንም ምንም የማያተርፍበት እጅግ የከፋ የውድመት እና የመከራ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡
በአሁኑ ሰዓት ሁሉንም ሰው በብሔር ማንነቱ ጥግ የማስያዝ ክፉ አስተሳሰብ ሀገራችን ላይ በመስፈሩ፣ ለሁሉም የሀገራችን “ፖለቲከኞች” በጋራና በዕኩልነት ተሰሚነት ያለው ሀገራዊ የሚባል አስታራቂ እና መካሪ ትልቅ ሰው እንዳይኖረን ተደርጓል፡፡ ስለሆነም ከፊት ለፊታችን ከተደቀነብን አስከፊ ሀገራዊ ጥፋት ለመዳንና መፍትሔ ለማግኘት፣ ሌላ የጋራ ወዳጅ እና ገለልተኛ አካል ማስፈለጉ ተገቢ መስሎ ይሰማኛል፡፡ በመሆኑም በእኔ ዕውቀት በዚህ ሰዓት ከታላቋ አሜሪካ መንግሥት በላይ ለኢትዮጵያ የቀረበ ተሰሚነት እና ተጽዕኖ ያለው አጋር መኖሩን እጠራጠራለሁ፡፡
ስለሆነም የአሜሪካ መንግሥት ሀገሬ ኢትዮጵያ በጉልህ የተደቀነባትን አስፈሪና አደገኛ ሁኔታ ቅርብነትና ድርስነት ከግምት ውስጥ አስገብቶ፣ ልዩ ተኩረት እንዲሰጠው እና መንግሥታችንን ጨምሮ በሁሉም ጎራ በያገባኛል ስሜት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ሰዎችን፣ በተገቢው ጫና እና ምክር ወደሚበጀው ሀገራዊ ስምምነት እንዲመጡ ጥረት እንዲያደርግልን፣ የአሜሪካ መንግሥት የተለመደ የወዳጅነት እና የመፍትሔ አፈላላጊነት ሚናውን እንዲያበረክት ከልብ በመነጨ አክብሮት ባለኝ የዜግነት ድርሻዬ እማፀናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ የተደቀነባቸው አስከፊ ውድመት ከመከሰቱ በፊት ዛሬ አድኑልን፡፡ ከውድመት እና ከፍጅት በኋላ የሚደረጉ ርብርቦሾች በሁሉም ነገሩ አስከፊ፣ አክሳሪ፣ የማይሽር ቁስል ጥሎ የሚያልፍ እና ወደነበረበት የመመለስ ዕድሉም በበዙ መልኩ የመነመነ ነውና፡፡
ከልባዊ አክብሮት ከመነጨ ምሥጋና ጋር
ሳምሶን ጌታቸው ተክለሥላሴ

Read 7220 times