Monday, 11 September 2017 00:00

ዝሆን ይኸውና ቢሉት፤ ዱካው የታለ አለ

Written by 
Rate this item
(15 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ሶስት ሌቦች ወደ አንድ ሀብታም ግቢ ይገቡና፣ ጌትየው መተኛቱን ካረጋገጡ በኋላ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡
አንደኛው፡-
እኔ ጌትየው አካባቢ ሆኜ መንቃት አለመንቃቱን እያየሁ ልጠብቅ
ሁለተኛው፡-
እኔ ደግሞ ቀስ ብዬ የበረቱን በር ልክፈትና ከብቶቹን ላስወጣ
ሦስተኛው፡-
እኔ፤ እደጅ ልሁንና የወጡትን ከብቶች ራቅ ወዳለ ጫካ ነድቼ እናንተ እስክትመጡ ልጠብቅ
አንደኛው፡-
ከዚያስ ስንገናኝ ቀጥለን ምን እናደርጋለን? ከብቶቹን እንከፋፈላለን
ሁለተኛው፡-
ደሞ የምን ከብት መከፋፈል አመጣህ? በሚቀጥለው መንደር ገበያ ወስደን መቸብቸብ ነው እንጂ!
ሦስተኛው፡-
እኔ ገበያ ወስዶ በመሸጡ ሀሳብ ተስማምቻለሁ፡፡ ግን እስክንሸጥ ጌትየው ቢደርስብንስ?
ሁለተኛው፡-
እሱ ነቅቶ ወዲያ ማዶ መንደር እስኪመጣ ምን እንጠብቃለን? በተገኘው ዋጋ ሸጠን ከዐይን መሰወር ነው እንጂ?
ሦስተኛው፡-
ይሄ ድንቅ ሀሳብ ነው፡፡ በሉ አሁን ጊዜ አናባክን፡፡ ወደ ስምሪታችን እንሂድ፡፡
እንደተባባሉት የመጀመሪያው ሰውየው ተኝቶ ወደሚያንኮራፋበት መኝታ ቤት አካባቢ ሄዶ በተጠንቀቅ ቆመ፡፡ ሁለተኛው፤ በቀጥታ ወደ በረቱ አመራ፡፡ ሦስተኛው፤ ደጅ ወጥቶ የሚወጡትን ከብቶች ሊነዳ ተዘጋጀ፡፡
ሁሉም ነገር ያለምንም እንከን ተጠናቀቀ፡፡ ከዚያ ወደሚቀጥለው መንደር ከተማ መንገድ ጀመሩ፡፡ ሰውዬው እንቅልፍ ላይ እንደነበር ታውቋልና ዘና እያሉ ተጓዙ፡፡
ገበያ ውስጥ ገብተው፣ ቀንቷቸው፣ እንዳሉት በአንድ ጊዜ ቸበቸቡና ወጡ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ አንድ ጫካ ሄደው፣ ገንዘባቸውን ቆጥረው ሊካፈሉ ወሰኑ፡፡ ገንዘቡን ከመቁጠራቸው በፊት ግን አንደኛው አንድ ሀሳብ አመጣ፡፡
“ጎበዝ፤ ረሀብ አልተሰማችሁም?”
ሁለተኛው፡-
“እኔ በጣም ርቦኛል፡፡ ለምን አንዳችን ከከተማ ምግብ ገዝተን አንመጣም?”
ሦስተኛው፡-
“በጣም ጥሩ፡፡ እንግዲያው ዕጣ እናውጣ?”
በዕጣው ተስማሙና ዕጣው ወጣ!
የመጀመሪያው ሰው ላይ ወጣና፣ ገንዘብ ይዞ ወደ ከተማ ሄደ- ምግቡን ሊገዛ፡፡
ምግቡ ተገዝቶ እስኪመጣ፣ የቀሩት ሁለቱ መዶለት ጀመሩ፡፡
ሁለተኛው፡-
“አሁን ምግብ ሊገዛ የሄደው ጓደኛችን፣ ገንዘብ ክፍያው ውስጥ ባይኖርበት’ኮ ለሁለት ነበር የምንካፈለው?”
ሦስተኛው፡-
“ዕውነትክን’ኮ ነው፡፡ ታዲያ ለምን በሆነ ዘዴ አናስወግደውም?”
ሁለተኛው፡-
“ብንገድለውስ?”
ሦስተኛው፡-
“ጥሩ ዘዴ ነው፡፡ ደብድበን ለመግደል እንችላለን”
ሁለቱ ይህን እየዶለቱ ሳሉ ምግብ ሊገዛ የሄደው ደግሞ በበኩሉ ያሰበው ነገር ኖሯል፡፡
“አሁን የምገዛውን ምግብ መርዝ ባደርግበት’ኮ እነሱ ያንን መርዝ በልተው ክልትው ሲሉልኝ፤ የዚያ ሁሉ ገንዘብ ብቸኛ ባለቤት እኔ እሆናለሁ፡፡”
ስለዚህ የመጀመሪያው ሌባ፣ ከምግቡ ውስጥ መርዝ ጨምሮ ወደ ጫካው ተመለሰ፡፡
እንደደረሰ ሁለቱ አስቀድመው የዶለቱበት ሌቦች፣ ሳያስበው በዱላ ቀጥቅጠው ገደሉት፡፡ በመግደላቸው ተደስተው፣ ምግቡን አቅርበው በሉ፡፡ ሆኖም ምንም ሳይቆዩ ሁለቱም በያሉበት ክልትው ብለው ቀሩ!
*          *         *
“ደባ ራሱን ስለት ድጉሡን” ማለት ይሄ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ለሌላው ማጥፊ ያሰቡት ተንኮል፤ ዞሮ የራስ መጥፊያም ሆኖ ይገኛል፡፡ በሀገራችን ይሄ አያሌ ጊዜ ተከስቷል፡፡ ለሌላው ብለው ያመጡት ህግ፣ መልሶ በራሰ ላይ ሊመጣ እንደሚችል የሚያስተውል የለም፡፡ ማንም ቀድሞ ከተመታው ጓደኛው አይማርም፡፡ “እሱ ጥፋተኛ ስለሆነ ነው የተመታው፡፡ እኔ ግን ንፁህ ነኝ!” የሚለው አስተሳሰብ፣ በታሪክ ክር ላይ ደጋግሞ ሲጠነጠን አይተናል፡፡ አባራሪው ተባራሪ ይሆናል፡፡ አሳሪው ታሳሪ ይሆናል! የዛሬው ገምጋሚ፣ የነገው ተገምጋሚ ነው፡፡ የለውጥ ሕግ የማይሰራበት ቦታ የለም፡፡ Every rule changes, except the rule of change እንዲሉ ፈረንጆቹ፡፡ ከለውጥ ህግ በስተቀር ሁሉም ህግ ተለዋጭ ነው እንደማለት ነው! በእርግጥም የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ለውጥ ማንንም አይምርም! ህዝብም ስለሚያየው ለውጥ ተገቢውን ጥያቄ አያቀርብም! በሆነውና በሚሆነው ሁሉ እሰየው ያለ ይመስል ነገሩን አዳምቆ፣ አዳንቆና ሆይ ሆይ ብሎ፣ የሆዱን በሆዱ ይዞ፣ ደግሞ መጪውን ድርጊት ወይም ክስተት ይጠብቃል፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ የትላንትናው አካሄድ ምን ጠቀመኝ? ምን ዓይነት ለውጥ ያሻኛል? ሁሌ “ቃና ውስጤ ነው” እያልኩ እዘልቀዋለሁ ወይ? እያደግሁ ነው ወይስ እያጠርኩ በመሄድ ላይ ነው ያለሁት? ብሎ መጠየቅ ማወቅ አለበት፡፡ ጥቂቶች የወርቅ ክምር ጉልላት ላይ የተቀመጡባት፣ ብዙዎች የፒራሙዱ ግርጌ ላይ ተረፍርፈው የሚተኙባት አገር “የዕንቁልልጬ” አገር ናት! ራስን የማያረካ፣ መንግሥትን የማያረካ፣ አገርን የማያረካ ሥራ፣ ሥራ ተብሎ የሚኖርባት አገር፣ የ“ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” አገር ናት! አብዛኛው ሕዝብ፣ ምሁሩም ጭምር፣ በብዥታ የሚጓዝባት አገር የራዕይ አገር ልትሆን ከቶ አትችልም፡፡ የዕንቁልልጩ አገር እንጂ! የታቀደው አልሳካ ሲል ወደ ዘመቻ የሚኬድበት አገር በዕቅድ ትመራለች ማለት ዕንቁልልጩ ነው! ትላንትን ሳናጣጥም፣ ዛሬን ሳንኖር፣ ነገን እየፈራን መኖር እርግማን ነው! ሼክሲፒር በፀጋዬ ገ/መድህን ብዕር እንደሚለው፡፡
“… በምናውቀው ስንሰቃይ፣ የማናውቀውንም ፈርተን በሕሊናችን ማቅማማት፣ ወኔያችንንም ተሰልበን፣ ከዕለት ወደ ዕለት ተስበን፣ ከአባቶች በወረስነው ጋድ እያደቀቅን እየደቀቅን፣ መጓተት በጥንቱ ልማድ፣ በሃሳብ ጭጋግ ስንዋኝ፣ መንፈስ ንቁነት ጥቅሙ የአድራጎት ምግባር አምሃ፣ የመንቀሳቀስ አቅሙ እያደር ከሕሊናችን፣ ይደመሰሳል ትርጉሙ!...”
የተግባር ሰዎች እንሁን! ዐይናችን የሚያየውን ከልባችን አንሸሽገው፡፡ በራሳችን እንተማመን፡፡ ዕውነታን አንካድ! “ዕምነት ሲታመም፣ ሺህ ወረቀት መፈረም” የሚለውን የአበው ብሂል አንርሳ! ሌቦችን ሌቦች ማለት እንልመድ! የዛፉን አክል በቅርንጫፉ ላይ አንላክክ! የዘገየ ፍርድ፣ ከሌለው አንድ መሆኑን አንዘንጋ! አሁንም አዲስ ነገር የምንፈልግ ከሆነ፣ አዲስ ልቦና እንግዛ! አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ ለመቀበል ዝግጁ እንሁን! የሚታየውን አንካድ! ተጨባጩ ላይ ዐይናችንን አንጨፍን! “ዝሆን ይኸውና ቢሉት፣ ዱካው የታለ፤ አለ” የሚለው ተረት የሚያጠነክረው ይሄንኑ ነው!!
መልካም አዲስ አመት!

Read 7146 times