Saturday, 02 September 2017 12:53

ከሚላኖ እስከ መቀሌ የዘለቀ ኢንቨስትመንት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

ለመቀሌ የመጀመሪያ የሆነው ትልቅ ሪዞርት ተመርቋል

       የተወለዱት በመቀሌ ከተማ ነው፡፡ ህፃን ሳሉ በቤተሰብ የስራ ዝውውር ምክንያት በማይጨው መኖር በመጀመራቸው፣ እዚያው እስከ 8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ ወደ መቀሌ ተመልሰው፣ በአፄ ዮሐንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ በ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና፣ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ በቂ ውጤት በማምጣታቸውም፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው፣ በቴአትር ጥበባት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን በትግራይ ቴሌቪዥን ፕሮግራም በዳይሬክተርነት ተቀጥረው ሰርተዋል፡፡ ነገር ግን በወር ደሞዝ ህይወታቸውን የማሻሻል ህልማቸውን እንደማያሳኩ
በመረዳታቸው፣ ባህር ማዶ ተሻግረው የስደት ኑሮ በጣልያን ጀመሩ - የዛሬው እንግዳችን አቶ ሙሉጌታ…..፡፡ ለመሆኑ በጣሊያን ምን ጠበቃቸው? ፈተናዎችን እንዴት ተወጧቸው? በሚላን ከተማ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ሬስቶራንት፣ ናይት ክለብና ባር የመክፈት አቅም ከየት አገኙ? የ39 ዓመቱ አቶ ሙሉጌታ፤ የዛሬ 10 ዓመት ገደማ፣ ወደ ትውልድ ከተማቸው ጎራ ብለው፣ ትልቅ ሆቴል ከፍተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለመቀሌ የመጀመሪያ የሆነውን ሪዞርት ገንብተው፣ በዘንድሮው የአሸንዳ በዓል ላይ አስመርቀዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከባለሀብቱ አቶ ሙሉጌታ ጋር በስደት ህይወታቸው፣ በአገር ውስጥና በውጭ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴያቸው፣ አነጋጋሪ በሆነው የአለባበስ ዘይቤያቸው --- ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡

     ቤተሰብዎ ችግረኛ አልነበሩም፡፡ ተምረውም ሥራ ይዘው ነበር፡፡ ታዲያ እንዴት ስደትን መረጡ?
እንዳልሽው እንደ ማንኛውም ልጅ አድጌ፣ ተምሬ ስራ ይዣለሁ፤ ግን ሁልጊዜ ደሞዝ እየተቀበሉ አንድ ዓይነት ኑሮ ብቻ መምራት  ይከብዳል፡፡ ስለዚህ ህይወቴን ለመቀየር በማሰብ ተሰደድኩ። የወጣሁት በ1988 ዓ.ም ነው፡፡ ዋናው ዓላማዬ፣ እኔም ሰው ሆኜ ጥሪት አፍርቼ፤ አገሬ ላይ ኢንቨስት በማድረግ፣ ራሴንም ወገኔንም አገሬንም ለመጥቀም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ይሄንን ዓላማዬን እያሳካሁ እገኛለሁ።
እንደሰማሁት ጣሊያን ገብተው ብዙም ሳይንገላቱ ነው፣ የራስዎን ድርጅት ለመክፈት የቻሉት፡፡ እንዴት በቀላሉ ተሳካልዎ?
በነገራችን ላይ ወደዚህ ስራ የገባሁት አስቤበት አይደለም፡፡ ጣሊያን አገር ስሄድ ከሁሉም በፊት ዋናው አላማዬ፣ ህጋዊ መሆን ነበር፡፡ ምክንያቱም ህጋዊ ከሆንኩ፣ ህጋዊ ስራ መስራት እችላለሁ። እንደ ልቤም እንቀሳቀሳለሁ፡፡ በአጋጣሚ ደግሞ ይህን ለማድረግ በምሯሯጥበት ሰሞን አዲስ አዋጅ ወጥቶ ነበር፡፡ “እዚህ አገር በስደት የምትኖሩ፣ ይህን ይህን ሰነድ አሟሉና ህጋዊ ሁኑ” ይላል - አዋጁ፡፡ ይህ አዋጅ የወጣው፣ እኔ እዛ አገር እንደገባሁ ሰሞን ስለነበረ፣ እድሉን ተጠቅሜ፣ ሰነዶቼን አስተካክዬ፣ ህጋዊ ነዋሪ ሆንኩኝ፡፡ ጣሊያን አገር ዋናው ነገር፣ ህጋዊ መሆን ነው፡፡ ህጋዊ ከሆንሽና ስርዓታቸውን አክብረሽ ከኖርሽ፣ ረጅም ርቀት መጓዝ ትችያለሽ። አጉል ነገር ውስጥ ከገባሽ ግን ህይወት ይበላሻል፤ እድሜም ያጥራል፡፡ ለዚህ ነው እኔ ዋና ትኩረቴን ህጋዊ መሆን ላይ ያደረግሁት፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ድርጅቶቼን ወደ መክፈት የገባሁት፡፡
ሬስቶራንቶችና የምሽት ክበቦች ከመክፈትዎ በፊት ምን ነበር የሚሰሩት?
መጀመሪያ ሱቅ ነው የከፈትኩት፡፡
ምን አይነት ሱቅ?
የወንድ ልብሶች፣ ከስክስ ጫማዎች፣ የኢትዮጵያ ካሴቶችና የባህል እቃዎች እሸጥ ነበር፡፡
ደንበኞችዎ ሃበሾች ነበሩ ወይስ…?
በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን፣ ሌሎች፣ የአፍሪካ አገራት ዜጎች፣ ጣሊያኖቹም ራሳቸው ደንበኞቼ ነበሩ፡፡ ሁሉም መጥቶ የሚፈለግውን ይገዛኛል፡፡ ብዙ የአረብ ደንበኞችም ነበሩኝ፡፡
ከዚያ ነው ባርና ሬስቶራንት የከፈቱት?
አዎ! ነገር ግን እግረመንገዴን ቤት እየገዛሁ እሸጥ ነበር፡፡ በዚህ መንገድ ገቢዬን እያሳደግኩ ነው የቢዝነስ ሥራዬን ማስፋፋት የቻልኩት፡፡
ባርና ሬስቶራንቶቹ በ‹ኢትዮጵያ› መሰየማቸውን ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ስለሱ ያብራሩልኝ …
የመጀመሪያው ሱቄ አቢሲኒያ ይባል ነበር። ሁለተኛው ባር ኢትዮጵያ ይሰኛል፡፡ ቀደም ሲል ባር አስመራ ይባል ነበር፡፡ ሶስተኛውና የመጀመሪያው ሬስቶራንቴን ከቻይናዎች ነበር የገዛሁት፤ “ሬስቶራንት ኢትዮጵያ” ብዬ ሰየምኩት፡፡ ቀጥሎ ፕሪንችፔ (ልዑል) የተሰኘ ባር ገዛሁና  “ባር አዲስ አበባ” አልኩት። ከጣሊያኖች ነበር የገዛሁት፡፡ እንደገና ከጣሊያኖች አንድ የምሽት ክበብ ገዛሁና “ብላክ ስታር ክለብ” ብዬ ሰየምኩት፡፡
ይሄኛው ለምን የእንግሊዝኛ ስያሜ ተሰጠው?
በጣም ጥሩ! እንግዲህ ኢትዮጵያንና ዋና ከተማዋን ቅድሚያ ሰጥቼ ሰየምኩኝ፡፡ ከዚያ በ”ብላክ ስታር” የምሽት ክበብ በርካታ አፍሪካዊያን ስለሚዝናኑበት፣ ሁሉንም አፍሪካዊ እንዲወክል በማሰብ ነው “ብላክ ስታር” ያልኩት፡፡ በዚህም አላቆምኩም፡፡ የማራዶና የጓደኛው “ግሪን” የሚባል ቤት ነበር፤ እሱንም ገዝቼዋለሁ፡፡ ባለቤቱ የናፖሊ ልጅ ነበር፡፡ ከዚያ “ናቅፋ” የሚባል ቤት ተጫርቼ  አሸንፌአለሁ፡፡ በኋላም “ዋን ላቭ” የተሰኘ ናይት ክለብ ከፈትኩ፡፡ አሁን መቀሌ ሚላኖ ሆቴል ጎን ያለው ክለብ፣ “ዋን ላቭ” ነው፡፡
በጣልያን ያሉት ባርና የምሽት ክለቦቹ ስንት ሆኑ ማለት ነው?
ሰባት ስምንት ይሆናሉ፡፡
በሰው አገር ይሄንን ሁሉ ድርጅት  ማስተዳደር አይከብድም?
ለዚህ ራሱን የቻለ መላ አለው፡፡ አንድ ሰው ሁሉ ነገር የሚከብደው፣ ብቻዬን ልብላ ብሎ ሲስገበገብ ብቻ ነው፡፡ እኔ እንደዛ አይደለሁም፡፡ በየቦታው ሰዎችን በሀላፊነት አስቀምጣለሁ፡፡ ማስቀመጥ ብቻም አይደለም፤ ሀላፊዎቹ ላይ እምነት እጥላለሁ። ያ ዕምነት የተሰጠው ሰው፣ ዕምነቱን ካጎደለ የራሱ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ የጎደለውን እሞላለሁ፡፡ ያ ሃላፊ ምቾት ተሰምቶት እንዲሰራ አስፈላጊውን ሁሉ አመቻቻለሁ፡፡  ነፃ ሰው ሆኖ እንዲሰራ አደርጋለሁ፡፡ ስለዚህ እምነቱን ጠብቆ ይሰራል፡፡ ብዙ ሰው ችግር የሚገጥመው፣ ሰራተኛውን በአግባቡ ሳይዝ ሲቀር ነው፡፡ በአግባቡ ካልያዘው ሰራተኛ ደግሞ ብዙ ስራና ብዙ ውጤት ይጠብቃል፡፡ እኔ እንደዛ አይደለሁም። ጥንቃቄ ስለማደርግ በዚህ በኩል የሚገጥመኝ ችግር የለም፡፡ ቀን ቀን ሌሎች ስራዎቼን ስስራ እውልና ክለቦቹ ላይ ራሴ እንደ ቦዲጋርድ ሆኜ እሰራለሁ፡፡ በተረፈ ብዙ የመቆጣጠሪያ መንገዶች እጠቀማለሁ፤ ለምሳሌ CCTV ካሜራ እገጥማለሁ፡፡
ሁሉም ባርና የምሽት ክበቦች አንድ አካባቢ ናቸው?
ናይት ክለቦቹ ወጣ ያሉ ናቸው:: ባሮቹ ግን በአንድ አካባቢ ላይ ነው የሚገኙት፡፡ ፖርት ሌኒሲያ በተባለው የሀበሻ ሰፈር ነው የሚገኙት፡፡  
ጣሊያን ማፍያዎች የሚበዙባት አገር እንደሆነች ይታወቃል፡፡ በዚህ አይነት አገር ላይ ያውም ጥቁር ሆኖ ይህን ሁሉ ሀብት ማፍራት ለአደጋ አያጋልጥም?
በነገራችን ላይ አንቺ መጥፎ ነገር ውስጥ ካልገባሽና መጥፎ ካልሰራሽ በቀር ጣሊያን አገር ችግር የለም። መጥፎ ነገር ውስጥ የገባ ሰው፣ ከዚያ ለመውጣት ከፍተኛ ዋጋ ይከፍላል፡፡ እኔ ደግሞ ከአገሬና ከቤተሰቤ ተለይቼ ስወጣ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ ዓላማዬ ብዬ የያዝኩት፣ ሌት ከቀን ሰርቼ፣ ህይወቴን መቀየር ነው፡፡ የምሰራውም ህጋዊ በሆነ መንገድ ነው፡፡ ህጋዊ ስለሆንኩ በራስ መተማመን አለኝ፡፡ እርግጥ ነው ባልተገባ መንገድ ገንዘብ የሚጠይቅ ይኖራል፡፡ እኔ ግን ፊት አልሰጥም፡፡ እንደውም፤ “እኔ በጦርነት ያደግኩ ነኝ፤ እኔና እናንተን የሚያገናኘን ነገር የለም፤ ስራዬን ልሰራበት” በማለት አስፈራራቸዋለሁ፡፡ ምክሬን ተቀብለው ከሄዱ እሰየው፤ አሻፈረኝ  ካሉ ግን ከባንኮኒ ላይ ዘልዬ ቢላዋ ይዤ አሯሩጣቸዋለሁ፡፡
አያቶቻችን ፋሽስቶችን በቢላዋና በጎራዴ አይደል አሯሩጠው ያባረሯቸው?
ትክክል ነሽ፡፡ እነሱም ብን ብለው ነው የሚጠፉት። ልብሽን ያያሉ፤ ፈሪ ከሆንሽ የሚፈልጉትን ያደርጋሉ፤ ኮስታራ ከሆንሽ አጠገብሽ አይደርሱም፡፡ ዋናው ነገር ህጋዊ መሆን ብቻ ነው፡፡ አሁን አልጀሪያ፣ ሞሮኮና ሌሎችም ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሲሰሩ፣ መንግስትም ፖሊስም “ወይ እነዚህን አባርር፤ አለበለዚያ ቤትህ ይዘጋል” ብሎ ያስጠነቅቃል፡፡ ሁሉ ነገር የሚወሰነው በራስ ጥንካሬና ድክመት ነው፡፡ ጥሩ ከሰራሽ  የምትቀየሪበት እድል ሰፊ ነው፡፡
የመቀሌውን ሚላኖ ሆቴል እንዴት ነው የገዙት?
ሚላኖ ሆቴል የተገዛው፣ ለእኔም ህልም በሚመስለኝ መንገድ ነው፡፡ እንግዲህ የእናቴ አንድ ምክር፣ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ፣ ለዚህ ሆቴል መገዛት ትልቅ ምክንያት ነው፡፡
እንዴት?
እናትና አባቴን ጋብዣቸው ጣሊያን ሚላን ነበሩ። እዛ ለስድስት ወራት ሲቆዩ፣እናቴ አንድ ነገር መክራኝ ነበር፡፡ እኔ በዓመት 18 ጊዜ ከጣሊያን አዲስ አበባ እመላለሳለሁ፤ ነገር ግን መቀሌም ሆነ ማይጨው መጥቼ አላውቅም፡፡ ይሄ ነገር የከነከናት እናቴ፤ “ሙሉጌታ ልጄ፤ አንድ ቀንስ ሁለትስ ቀን ለምንድን ነው መቀሌን የማታያት? ማይጨውንም ቢሆን አድገህበታል፤ ምንድን ነው ችግሩ?” ብላ አምርራ ጠየቀችኝ፡፡ እናቴን በጣም ስለምወዳት የምትለኝን እሰማለሁ፡፡ በ1997 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመጣሁ ጊዜ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ሆቴል ለመግዛት እፈልግ ነበር፡፡ ብዙ ጥሩ ጥሩ ቦታዎችም አግኝቼ ነበር፡፡ ነገር ግን የመጣሁት ችግር በተከሰተበት የ97 ምርጫ ሰሞን ስለነበር፣ የአዲስ አበባውን ሆቴል የመግዛት ሀሳብ ሰረዝኩት። ከዚያ ፊቴን ወደ መቀሌ አዞርኩኝ ማለት ነው፡፡ ይሄ ቦታ (ቁጭ ብለን ያለንበት ሚላኖ ሆቴል) በፊት የአኢወማ ቢሮ የነበረበት ነው፡፡ ከጣሊያን መጥቼ፤ ከዘመዶቼ ጋር በዚህ ስናልፍ፣ ቤቱ በትልቁ ተሰርቷል ግን ጭለማ ነው፡፡ ይሄ ቤት ምን ሆኖ ነው ስላቸው፤ ጨረታ ወጥቶበት አልተሸጠም አሉኝ፡፡
እርስዎ ሲያውቁ ቤቱ ምን ነበር?
ሆቴል ነበር፤ ሀውዜን ሆቴል ይባል ነበር፡፡ ከዚያ “ይህን ሆቴል ሰው ቢፈልገው ማንን ነው መጠየቅ ያለበት?” ስላቸው፣ ልማት ባንክን መጠየቅ ይቻላል አሉኝ፡፡ በዚያች ቅፅበት፣ ቤቱ የኔ እንደሚሆን እርግጠኛ ሆንኩኝ፡፡ በቃ በሀሳቤ ቤቱን ወሰድኩት።
ከዚያስ?
ማታ ነበር ያየነው፤ ሌሊቱ አልነጋልህ አለኝ። አንዳንዴ አንድን ነገር ለማግኘት ስትጓጊ ሰዓቱ ይረዝም የለ? እንደዛ ሆነብኝ፡፡ በጠዋቱ ወደ ልማት ባንክ ሄድኩኝ፤ ቤቱን ወስደው አስጎበኙኝ፡፡ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነበር፡፡ እቃዎቹ አዳዲስ ነበሩ፣ ባሩ ለየት ያለ ነው፤ ብቻ ብዙ ነገሩ ማራኪ ስለነበር  በጣም ወደድኩት፡፡ እነሱ ግን “ሼህ አላሙዲን ይፈልጉታል” አሉኝ፤ እኔም “ሼህ አላሙዲን በርካታ ሰራተኞችን ያስተዳድራሉ፤ ብዙ ቢዝነሶች አሏቸው ሲባል ስለምሰማ፣ እሳቸው ከፈለጉት ይውሰዱት” ብዬ ስወጣ፣ “ለማንኛውም ማመልከቻ አስገባ” አሉኝ። ማመልከቻዬን በእጅ ፅሁፍ አዲስ አበባ ለሚገኘው ልማት ባንክ አስገብቼ፣ ወደ ጣሊያን ተመልሼ ሄድኩኝ፡፡ ከዚያ መጣሁ፡፡ ዋጋህን አስገባ አሉኝ፡፡ ዋጋውን አስገብቼ ሲያዘገዩብኝ ተመልሼ ሄድኩኝ፡፡ ዋጋው አንሷል ጨምር ሲሉኝ፣ እንደገና ተመልሼ መጣሁ፡፡
በብዙ ውጣ ውረድ ነዋ የተገዛው?
ብዙ ለፍቻለሁ፡፡ ከዚያ ዋጋ ጨመርኩና አስገብቼ ተመልሼ ሄድኩኝ፡፡ አንድ ቀን ሮም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካኝነት ከኢትዮጵያውያን ጋር ስብሰባ ተካሂዶ ነበረ። በስብሰባው ላይ “ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች አሉ፤ መንግስት ለዲያስፖራዎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል” እያለች የኤምባሲው ተወካይ ታብራራለች፡፡  ዲያስፖራው ደግሞ “እንደዚህ እያላችሁን አገራችን ስንገባ፣ ምንም የለም” የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ፡፡ እኔ ደግሞ በዚህ ሆቴል ጉዳይ አራት ጊዜ አመላልሰውኝ በተግባር አይቼዋለሁ፡፡ ግን ዝም አልኩና ለሻይ እረፍት ስንወጣ፣ ስለ ራሴ ጉዳይ በዝርዝር ነገርኳቸው፡፡ አምባሳደሩ ጋሽ መንግስቴ ምን አሉኝ፤ “አለባበስህ ወጣ ያለ ስለሆነ ዱርዬ መስለኻቸው ይሆናል፤ ያለህን ንብረትና ስለ አጠቃላይ ሁኔታህ ፅፌ እልክላቸዋለሁ”
በእርግጥም ከፀጉር ስታይልዎ ጀምሮ አለባበስዎ ትንሽ ለየት ያለ ነው፡፡ በተለይ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ችግር አይገጥምዎትም? ከአገሩ ወግና ልማድ ለየት በማለትዎ ሰዎች ምን አስተያየት ይሰጣሉ?
እንግዲህ የእኔ ፍላጎት ይሄ ነው፡፡ የምለብሰው… ፀጉሬን የማስይዘው እንደዚህ ነው፡፡ እርግጥ ነው ብዙ ሰው ግራ ሊጋባ ይችላል፤ እኔ ግን ምንም አይመስለኝም። አሁን አሁን ሁሉም ሲቀርበኝ ባህሪዬ ላይ እንጂ አለባበሴ ላይ አያተኩርም። ደግሞ በዚህ ቅር የሚሰኝ ካለ፣ምንም ማድረግ አይቻልም። ይህን የማደርገው፣ ሰው ለምኜና አስቸግሬ አይደለም፡፡ ራሴን ችዬ ነው፤ ይሄ ፍላጎቴ ነው። ብዙ ሰው አለባበሴን አይቶ እኔን በፈለገው መንገድ ሊገምት ይችላል፤ እኔ ግን እኔ ነኝ፡፡
ምናልባት ጣሊያን ውስጥ በምሽት ክለቦች መስራትዎ የፈጠረው ተጽዕኖ ይሆን? እንዴት ነው ይሄን ዓይነት አለባበስ የጀመሩት?
ከምሽት ክለቦች ሥራ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ሚላን የፋሽን ከተማ ናት፡፡ እኔም ፋሽን ልብሶችንና ጫማዎችን በመደብሬ ውስጥ እሸጥ ነበር፡፡ የዘመኑን ፋሽን ተከትሎ መልበስ የጀመርኩት በዚህ መልኩ ነው፡፡
አሁን ወደተቋረጠው ጨዋታ ልመልስዎ፡፡ “ደብዳቤ እጽፍልሃለው--” ካሉት አምባሳደር ጋር ቀደም ብሎ  ትተዋወቁ  ነበር?
አዎ፡፡ አንዳንድ የኢትዮጵያውያን ፕሮግራም ሲኖር፣ ፋሺን ሾው ሲዘጋጅ፣ ሁሌም በሬ ክፍት ነው፤ በዚህም ብዙ ኢትዮጵያዊያን ጭምር ያውቁኛል። አምባሳደሩ እንደውም፤ “ከንቲባችን” እያሉ ነበር የሚጠሩኝ። ከእሳቸው ጋር ተመካከርኩና ደብዳቤውን አፅፌ፣ እንደገና ተመልሼ ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ፡፡ ከዚያ የካምፓኒ ፕሮፋይላችሁን አቅርቡ ተባልን፡፡ ከእኔ ጋር ይጫረቱ የነበሩትን ሰዎች ስመለከት፣ ትልልቅ ባለሥልጣን ነው የሚመስሉት። ይሄ ነገር እንዴት ነው ብዬ ማሰብ ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያ የጨረታውን ልዩነት አስፍቼ መጫረት አለብኝ ብዬ አሰብኩ፡፡
እንዴት ማለት?
ከፍ ባለ ገንዘብ መጫረት ማለቴ ነው፡፡ መጨረሻ ላይ ጨረታው ግልፅ ስለሚሆን፣ በሰም በታሸገ ኤንቨሎፕ አስገቡ ተባልን፡፡ ወዲያው ጨረታው ተከፈተ፤ አሸነፍኩኝ፡፡ ማመን ነበር ያቃተኝ፡፡ ሆቴሉ 3 ዓመት ተዘግቶ ነበር የተቀመጠው፡፡
በምን ያህል ዋጋ ነው  ጨረታውን ያሸነፉት?
በ11 ሚሊዮን 750 ብር፡፡
ልዩነቱ ስንት ብር ነበር?
3 ሚሊዮን 750 ሺህ ብር ልዩነት ነበረው፡፡ እኔ ለመገንባት ብዙ ዓመት ይወስድብኝ ነበር፤ ግን ያለቀ ቤት አገኘሁ፡፡ ታዋቂ ሆቴል ሆነ፤ ስሙም ሚላኖ ተባለ። ለምን? ሚላን ከተማ ውስጥ ባፈራሁት ገንዘብ የተገዛ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚያ ጣሊያን የሚኖር ሰው ነው የገዛው ሲባል፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ “7 ሚ. ብር ጨምረን እንግዛህ” አሉኝ፤ ግን የእናቴ ምክር ውጤት ስለሆነ፣ አልሸጥም ብዬ ይሄው 11 ዓመቱ ነው፡፡
እርስዎ ከገዙት በኋላ መከላከያዎች ገብተውበት ነበር ይባላል?
አዎ! እኔ ሁሉን ጨርሼ ጣሊያን ስመለስ፣ ልማት ባንክ ለመከላከያ አከራይቶ ጠበቀኝ፡፡ ከዚያ ዘመዶቼ ደውለው፣ “ቤቱን በጨረታ አሸንፈህ ተረክበህ ስታበቃ፣ ለምን መከላከያ ገባበት?” ሲሉኝ፣ እየበረርኩ መጣሁ። ያኔ ስሙ አልተዛወረም ነበር፡፡ ለሁለት ሳምንት 40 ሺህ ብር አከራይተውት ጠበቁኝ፡፡ ከዚያ እዚህ ያለው ልማት ባንክ፣ ይቅርታ ጠየቀኝ፤ እኔም አብረን ስለምንሰራ ብዙም አልከፋኝም፤ ከሁለት ሳምንት በኋላ ለቀቁ፡፡   
አሁን ደግሞ ለመቀሌ ከተማ የመጀመሪያ የሆነውን ትልቅ ሪዞርት አስገንብተው፣ በአሸንዳ በዓል ዕለት አስመርቀዋል፡፡ እስኪ ስለ ሪዞርቱ ግንባታ ያጫውቱኝ?
ይህ ሪዞርት የተገነባበት ቦታ የአፄ ዮሐንስ የልጃቸውና የልጅ ልጃቸው ቦታ የነበረ ነው፡፡ የራስ ጉግሳና የራስ አርአያ ሥላሴ ቤት የነበረበት ነው። ቦታውን መንግስት ፕራይቬታይዝ ለማድረግና ባለሀብትና መንግስት በመተጋገዝ ለማልማት ነበር የታለመው፡፡ በመጨረሻ እኔ ጨረታውን አሸንፌ ወሰድኩት፡፡ ሪዞርቱ 245 ሚ. ብር በጀት የተያዘለትና በ40 ሺህ ካሬ ላይ ያረፈ ነው። መጀመሪያ ላይ ትግራይን የሚወክል ሪዞርት እንዲሰራ ነበር ስምምነቱ፡፡ እኔ ግን ፕሮፖዛሉን አሻሻልኩት፡፡
በምን መልኩ ነው ያሻሻሉት?
ሪዞርቱ ትልቅና በከተማዋ የመጀመሪያው እንደመሆኑ፣ ከተማዋም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገች በመምጣቷ፣ ክልሉም በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ስላሉት፣ ብዙ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ለጉብኝት ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ ይህ ሪዞርት ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ ውክልና ይኑረው የሚል ነው፤ የኔ የተሻሻለው ፕሮፖዛል፡፡ ሃሳቡም ተቀባይነት አገኘ፡፡ ቦታው በቅርስነት የተመዘገበ ነው፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ  ኪነ ህንፃው፣ የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦችና የአፍሪካን ማንነት እንዲያጎላ ተደርጎ ነው የተሰራው፡፡
እዚሁ አካባቢ የሚገኝ ድንጋይ እየተጠረበ መሰራቱን ሰምቼአለሁ፡፡ ለግንባታው ከውጭ የመጣ ግብአት የለም የሚባለው እውነት ነው?
እውነት ነው! እዚሁ በሚገኝ ድንጋይና ከደቡብና ከሌሎች አካባቢዎች በሚመጣ እንጨት ነው የተሰራው። ግንባታው የተጀመረው ከ6 ዓመት በፊት ነው፡፡ ድንጋዩን መጥረብና ማስተካከል ብዙ ጊዜ ወስዶብናል፡፡ አሁንም ሁለት በመቶ ስራ ይቀረዋል፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ የሪዞርት ግንባታ ላይ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከደቡብ የመጡ በርካታ ባለሙያዎች ናቸው እየተሳተፉ ያሉት፡፡ ከ300 እስከ 400  ለሚደርሱ ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡
ለሪዞርቱ ግንባታ 60 በመቶ ብድር እንደሚያገኙ፣ ቀሪው ደግሞ በእርስዎ እንደሚሸፈን ከመንግስት ጋር ስምምነት ነበራችሁ፡፡ ሆኖም ሙሉ በሙሉ በራስዎ ወጪ ነው የገነቡት ተብሏል። ብድሩ አልተገኘም?
ስምምነቱ በገለፅሺው መሰረት ነበር፡፡ በአጋጣሚ ውሉን እነሱ አፈረሱ፤ እኔው ቀጠልኩበት፡፡ ጣሊያን ከሚገኙት ድርጅቶቼ የማገኘውን ገቢ፣ እዚህ ላይ እያፈሰስኩ ነው የሰራሁት፡፡ አሁን ከውጭ የምናስገባው እቃ ስለሌለ፣ የውጭ ምንዛሬ ችግር የለብንም፡፡ ወጪው ግን አሁንም አላለቀም፤ ከተመደበለት 245 ሚ. ብር በላይ ይወስዳል፡፡ ሆኖም በራሴ አቅም በመስራቴ ደስተኛ ነኝ፡፡
እንዴት ነው ከጣሊያን ጠቅልለው የመምጣት ሃሳብ የለዎትም?
ጠቅልዬ አልመጣም፤ ቢያንስ ጣሊያን ጤና መጠበቂያና መዝናኛ ይሆነኛል፡፡
የጣሊያን ዜግነት አለዎት?
ለረጅም ጊዜ አልነበረኝም፤ እኔም አላተኮርኩበትም ነበር፡፡ አሁን ግን አለኝ፡፡
በቢዝነስዎ በጣም ስኬታማ ሆነዋል፡፡ ትዳርና ቤተሰብስ መስርተዋል?
አዎ፤ ሚስት አግብቼ፣ ሦስት ልጆች አሉኝ፤ እዚሁ ነው የሚኖሩት፡፡

Read 1939 times