Print this page
Saturday, 02 September 2017 12:48

“…እ …ና...ት….”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ኢሶግ)
Rate this item
(0 votes)

ማንኛዋም እናት፣-
ክብሯን የማያጉዋድልና አክብሮት የተሞላበት የጤና አገልግሎት የማግኘት፣
ከአድልዎ የጸዳ በእኩልነትና ፍትሐዊ የሆነ የጤና አገልግሎት ማግኘት፣
ጤንነቷ ተጠብቆ የመኖርና ተገቢ የጤና ክብካቤ በነጻነት የማግኘት፣
በነጸነት የጤና ክብካቤ የማግኘትና ያለመገደድ፣
ሰብአዊ ክብሯና የግል ውሳኔዋን የማስከበር መብት አላት፡፡
በዚህ እትም ለንባብ ያልነው የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ስለሚሰራው አንድ ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ RIF (Reproductive initiative fund)  ይሰኛል፡፡ ዶ/ር መሀዲ በክሪ RIF (Reproductive initiative fund)  ለተሰኘው ፕሮጀክት ዳይሬክተር ናቸው፡፡
ጥ/    RIF የተሰኘው ፕሮጀክት ምንድነው?
መ/    ይህ RIF የተባለው ፕሮጀክት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ተግባሩን የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እንዲያከናውነው ያደረገው ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በአጠቃላይም የሚያጠነጥነው በእናቶችና በጨቅላ ሕጻናቶቻቸው ጤና ዙሪያ ነው፡፡
ጥ/    ለተግባሩ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እንዴት ተመረጠ?
መ/    የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር (ESOG)  በስራ ላይ በቆየባቸው ጊዜያትም ይሁን ለወደፊቱ ዋነኛ እቅዱ አድርጎና ባላማው ቀርጾ የያዘው በእናቶችና በሕጻናት ዙሪያ በተለይም በቅድመ ወሊድ’ ወሊድ እና ድህረ ወሊድ ዙሪያ ያሉ የጤና እንክብካቤዎች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ ነው። ስለዚህም RIF ፕሮጀክት ይህንን አላማውን ለማሳካት ከሚረዱት አቅጣጫዎች እንደ አንዱ አድርጎ በመቁጠርና ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በዚህ ፕሮጀክት ለመሳተፍ ተወዳድሮ እድሉን አግኝቶአል፡፡
ጥ/    ስራው የሚሰራው የት ነው?
መ/    ስራው የሚሰራው አርብቶ አደሩ ዙሪያ ነው። ይኼውም በአፋር ክልላዊ መንግስት ዞን /2/ በሚባለው አካባቢ በስምንቱም ወረዳዎች /43/ ቀበሌዎች ነው። ይህ ፕሮጀክት በአጠቃላይ በአፋር ውስጥ ከኢሶግ ውጪም በክልል ጤና ቢሮ አማካኝነት እንዲሁም ሌሎች መስሪያ ቤቶች  በአፋር በስፋት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ በአጠቃላም በክልሉ ወደ 7/ሰባት የሚሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ መስሪያ ቤቶች RIF ፕሮጀክትን እየተገበሩ ይገኛሉ፡፡
ጥ/    የስራው ባህርይ ምንድነው?
መ/    ስራው የተለየ መንገድና ባህርይ የለውም፡፡ ነገር ግን መንግስት ማለትም የክልሉ ጤና ቢሮ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ላይ ESOG ያንኑ መዋቅር ያንኑ የስራ እንቅስቃሴ እና እቅድ በመከተል አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠት ነው፡፡ የሚሰጠው ድጋፍም ዋና አላማ በዚያ ነዋሪ እናቶች በአካባቢያቸው ያለውን የጤና ድርጅት እንዲጠቀሙ የሚያስችል ፍልጎት ለመፍጠር አስተዋጽኦ ማድረግ ነው፡፡  ለዚህም ስራውን ለመስራት በታቀደባ ቸው ስምንት ወረዳዎች ባለሙያዎች ተቀጥረው ለህብረተሰቡ ቅርብ ሆነው እንዲሰሩ የተመቻቸበት ሁኔታ አለ፡፡
ሌላው ደግሞ ይህ የታሰበው ነገር በአፋጣኝ ሊታይ ወይንም ሊፈጸም የማይችል ስለሆነ በዚያ አካባቢ ያሉ የጤና ድርጅቶች ወደሕብረተሰቡ ሄደው ስራው በተዘረጋባቸው 43/ ቀበሌዎች በወር አንድ ጊዜ እየወጡ የቅድመ ወሊድ’ የወሊድ እና የድህረ ወሊድ እንዲ ሁም ስለክትባት እና እናቶች ወደጤና ተቋም ሄደው እንዲወልዱ ለማስተማር ወይንም ከህብረተሰቡ ጋር ለመወያየት ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበትን መንገድ ነው ESOG የሚሰራው፡፡  
ጥ/    ቀደም ሲል  የህብረተሰቡ ልምድ ምን ይመስላል?
መ/    ቀደም ሲል የነበረውን ልምድ ለማግኘት በተደረገው ጥናት እንደታየው አብዛኞቹ ወደጤና ተቋም ሳይሄዱ በቤታቸው በልምድ አዋላጆች እየታገዙ ይወልዱ እንደነበር ነው፡፡ ይህ አሁንም የተለወጠ ወይንም የተሸሻለ አይደለም፡፡ ይህ የእናቶች አወላለድ አሁንም በከፍተኛ ደረጃ እየቀጠለ ያለበት ሁኔታ ስላለ መልኩን ለመለወጥ ትግል የሚደረግበት ነው፡፡ እናቶች በእርግዝና ወቅት በተገቢው ሁኔታ ክትትል ካለማድረጋቸውም በላይ በሚወልዱበት ወቅትም ለተለያዩ ችግሮች እስከ ሕይወት ማጣት ሊጋለጡ እንደሚችሉ የታመነ በመሆኑ ይህ እንዳይቀጥል የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና በማዳበር ቀስ በቀስ እየተነገራቸው ወደጤና ተቋም ሄደው እንዲወልዱ ጠቀሜታውን ማሳየት እና ምክር መስጠት ያስፈልጋል። በዚህም ምክንያት ESOG-RIF በተሰኘው ፕሮጀክት ለእናቶች በጎውን መንገድ ለማሳየት እና እንዲጠቀሙ ለማስቻል እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡
ጥ/    ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም ምን ድጋፍ ይሰጣል?
ESOG  በሁሉም ማለትም በ8/ ወረዳዎች ባሉ 43 ቀበሌዎች ውስጥ ስራውን ወደህብረተሰቡ ዘልቆ ለመስራት እንዲቻል ሲባል ህብረተሰቡን ለማስተማር ጥረት ከማድረግ ባሻገር  የወረዳው ጤና ቢሮ ስራውን ካለችግር እንዲያከናውን ሲባል የተለያዩ ድጋፎችን በፕሮጀክቱ አማካኝነት አቅርቦአል፡፡ ለምሳሌም በየወረዳውና በወረዳው ጤና ቢሮ እንደልብ ተንቀሳቅሶ ስራ ለመስራት እንዲያስችል ሞተር ሳይክሎች ታድለዋል፡፡ በዚህም በየቀበሌው ዘልቆ ትምህርት ለመስጠትና የጤና ስራዎችንም ለመስራት ያስችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደፎቶኮፒ ማሽን  የመሳሰሉትን ሰጥተናል፡፡ በሚቀጥለው የበጀት አመት ከተያዙት እቅዶች መካከልም ጤና ጣቢያዎቹ በሶላር አማካኝነት የመብራት አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል ይገኝታል። በሚቀጥለው የበጀት አመት ሌላው የተያዘው እቅድ  የእናቶች መቆያ መስራት ነው፡፡ ምክንያቱም እናቶች ወደጤና ተቋም እንዲመጡ ሲፈለግ ምጥ በተያዙበት ቀን መሆን የለበትም ፡፡  ነዋሪ ዎቹ ወደጤና ተቋም እንዲሄዱ ሲፈለግ ያሉበትን ርቀት ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ እጅግ በጣም እሩቅ ከሆነ ስፍራ በሐሩር በእግራቸው ይጉዋዛሉ፡፡ ምናልባ ትም በአዲስ አበባ አንድ ሰአት የሚፈጀው መንገድ በአፋር በረሐ እንደሶስትና አራት ሰአት ሊቆጠር ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከላይ ከሚወርደው ሐሩር በተጨማሪ መሬቱ የጋለ ድንጋይና አሸዋ በመሆኑ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ እናቶች የመውለጃ ቀናቸው ሲዳረስ  በዚያው በሕክምና ተቋሙ አቅራቢያ በእናቶች ማቆያ ቢያርፉ በማንኛውም ሰአት ምጥ ቢይዛቸው በሐኪም እጅ ላይ እንዳሉ ይቆጠራል፡፡
ጥ/    የፕሮጀክቱ  አጨራረስ    ም ምን መልክ እንዲኖረው ታቅዶአል?
መ/    አንድ ፕሮጀክት እንደመጀመሩ መጨረሻም እንደሚኖረው አስቀድሞ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክትም የሚከናወነው ለብቻው መዋቅር ይዞ ሳይሆን በክልሉ መዋቅር አንድ ቢሮ ተሰጥቶን አስተባባሪዎች በዚያ ውስጥ ሆነው የክልሉን ጤና እቅድ በተፋጠነና በተደራጀ ወይንም ጠንከር ባለ አካሄድ እንዲፈጸም ማገዝ ወይንም ድጋፍ መስጠት ነው፡፡ ስለዚ ህም ፕሮጀክቱ ሲያልቅ የአቅም ግንባታ ያደረግንላቸው የመንግስት ባለሙያዎች ተደራ ሽነታቸውን በማጉላት ለእናቶችን ጨቅላዎቻቸው ጤንነትና ሕይወት መትረፍ አስፈላጊውን እንደሚፈጽሙ እምነት አለን፡፡ የዚህም ምክንያቱ እቅዱ የESOG   ሳይሆን የክልሉ ጤና ቢሮ ስለሆነ ነው፡፡
ጤናማ እናትነትን እውን ለማድረግ በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተዘጋጀው መመሪያ የሚከተሉትን ነጥቦች አስቀምጦአል፡፡
የህክምና ባለሙያዎች ለእናቶች ክብርና ርህራሔ የተሞላበት አገልግሎት መስጠት፣
የህክምና ተቋማቱ አገልግሎት ለመስጠት የተሟሉ መሆን፣
እናቶች መብታቸውን በሚገባ አውቀው ማስከበር፣
ከዚህም በተጨማሪ የስራው ተባባሪ አካላት፡-
የቴክኒካልና የቁሳቁስ እንዲሁም የገንዘብ እገዛ ማድረግ፣
ስራውን የመከታተልና የመገምገም ተግባር ላይ መሳተፍ፣
የምክር አገልግሎት ስልጠና ‘ሴሚናር መስጠት በመሳሰሉት ተግባር ላይ የህክምና ተቋማትን እንዲያግዙ ይጠበቅባቸዋል፡፡

Read 1607 times