Saturday, 02 September 2017 12:32

“ጣና የሶሻል ሚዲያ አዋርድ” ጳጉሜ 2 ይከናውናል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  ዘመራ መልቲ ሚዲያና ላመርጌር ኅትመትና ሚዲያ፣ በጋራ ያዘጋጁት “ጣና” ሶሻል ሚዲያ ሽልማት፣ ጳጉሜ 2 ቀን 2009 ከቀኑ 10፡00 ጀምሮ፣ ባህርዳር ከተማ በሚገኘው ብሉናይል ሪዞርት ሆቴል ይካሄዳል። ሽልማቱ፣ በባህልና ቱሪዝም፣ በፈጣንና ተአማኒ መረጃ፣ በፎቶግራፍ፣ በበጎ አድራጎት፣ በስፖርት፣ በጤና፣ በታሪክ፣ በትምህርት ምርምርና በማህበራዊ አገልግሎት በአስደማሚ ትርኢቶች፣ በኪነ-ጥበብ እና በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች በድምሩ በ10 ዘርፎች ሽልማት ይሰጣል፡፡
ተወዳዳሪዎች በተለይም በየዘርፉ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ማህበረሰቡን በሚጠቅም መንገድ አገልግሎት የሚሰጡ ሆነው፣ ከ2008 እስከ 2009 ዓ.ም መጀመሪያ፣ ፌስቡክን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሰሯቸው ስራዎች ተመዝነው ሽልማትና እውቅና እንደሚያገኙ፣ የዘመራ መልቲ ሚዲያ መሥራችና ዳይሬክተር አቶ ደምስ አያሌው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ሽልማቱ በክልሉ ሲዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በየዓመቱ እየተሻሻለና ሌሎች ዘርፎችን እያካተተ እንደሚቀጥል አቶ ደምስ ገልፀዋል ባህርዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ የአማራ ከተሞች ልማትና ግንባታ፣ ብሉ ናይል ሪዞርትና ሆቴል፣ ዩኒክ ማካሮኒና ፓስታ እንዲሁም ሆም ላንድ ሆቴልና ሌሎችም ድርጅቶች ላደረጉላቸው ትብብር አመስግነዋል፡፡

Read 1254 times