Saturday, 07 April 2012 09:12

350 ሚ.ዶላር የፈጀው “ጆን ካርተር” ከኪሳራ እየዳነ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ለዕይታ ከበቃ አምስት ሳምንት ያለፈው ሳይንሳዊ ልቦለድ ፊልም “ጆን ካርተር”  ሰሞኑን በዓለም ዙርያ ገቢው 254.53 ሚ ዶላር የደረሰ ሲሆን ከተሰጋው ኪሳራ  የመዳን ፍንጭ ማሳየቱን ፎርብስ አስታወቀ፡፡ በወቅቱ በ250 ሚሊዮን ዶላር ከፍተኛ ባጀት ወጥቶበት የተሰራውን ፊልሙን ለማስተዋወቅ ተጨማሪ 100 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ሆኖበታል፡፡ በአጠቃላይ 350 ሚሊዮን ዶላር የፈጀው ፊልሙ፤ አስራ አንድ “የስታር ዎርስ” ፊልሞች ሊሠራበት እንደሚቻልም ታውቋል፡፡

ፊልሙ በሰሜን አሜሪካ ለመጀመርያ ጊዜ ሲታይ  ያስገባው 30 ሚ.ዶላር ያልተጠበቀ ሆኖ ለኪሳራ ይዳርጋል የሚል ስጋት አንዣቦ ነበር፡፡ ከሰሜን አሜሪካ ውጭ ባለው ዓለም አቀፍ ገበያ  ግን የፊልሙ ገቢ መነቃቃት ማሳየቱ አደጋውን ቀንሶለታል፡፡ የቦክስ ኦፊስ ሞጆ  ትንተና እንደሚያመለክተው፤ ባለፉት አምስት ሳምንታት “ጆን ካርተር” በሰሜን አሜሪካ 66 ሚሊዮን ዶላር ሲያስገባ በመላው ዓለም  ደግሞ 188 ሚሊዮን ዶላር ተመዝግቦለታል፡፡ፊልሙ ከ100 ዓመት በፊት ከታተመና “ኤ ፕሪንሰስ ኦፍ ማርስ” ከተባለ ባለ 11 ክፍል መጽሐፍ   በዋልት ዲዝኒ ፒክቸርስ የተሰራ ነው፡፡ “ጆን ካርተርን” ዲያሬክት ያደረገው አንድሪው ስታንተን ነው፡፡ ማርስ የሞተች ፕላኔት አለመሆኗን በማረጋገጥ የሚጀምረው ሳይንሳዊ ልቦለድ ፊልሙ፤ ጆን ካርተር የተባለው ጀብደኛ ገፀባህርይ በዚህችው ፕላኔት ከሚኖሩ ፍጡራን ጋር የሚያካሂደውን ጦርነት ያሳያል፡፡ የጆን ካርተር ፊልሞችን እስከ 3ኛ ክፍል ለመቀጠል ፍላጎት እንዳለ ሲታወቅ ቀጣይ ስራዎች የባለ 11 ክፍሉን መፅሃፍ በመንተራስ እንደሚሰሩ ይገለፃል፡፡በጆን ካርተር ሶስት ተከታታይ ክፍል ፊልሞች እንደ ፓይሬትስ ካረቢያን እና ሃሪ ፖርተር ከፊልሙ ጋር በተያያዘ በሚገኙ የንግድ ገቢዎች ለመጠቀም ታቅዷል ተብሏል፡፡ ዋልት ዲዝኒ ፒክቸርስና ተባባሪው ፒክሳር  ተከታታይ ክፍል ያላቸውን ፊልሞች ለመስራት ፍላጎት ኖሯቸው እንደማያውቅ የገለፀው ዋሽንግተን ታይምስ፤ ጆን ካርተር የመጀመርያ ሙከራቸው በማድረግ ስያሜውን ብራንድ አድርጎ ለመስራት  እንዳቀዱ ጠቁሟል፡፡ጆን ካርተር የተሰራው በአሜሪካዋ ግዛት ኡታህ ውስጥ ሲሆን ክልሉ በረሃማነት ያለውና ከማርስ ከርሰ ምድር ጋር የተመሳሰለ በመሆኑ ለቀረፃው አመቺ እንደሆነላቸው ታውቋል፡፡ በቀረፃው የናሳን የማርስ ምርምር ተፈታትኗል የተባለ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ታይቶበታል፡፡ በፊልሙ ላይ በማርስ ይኖራሉ ተብለው የተገመቱ ፍጡራንን ለመፍጠር ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ቅንብር የታየበት ሲሆን  በተለይ ታራስ ታራክስ የተባሉትና የዝንጀሮ ዝርያ ያላቸው ግዙፍ ነጫጭ ጎሪላዎች የፊልሙን ገፅታ አድምቀውታል ተብሏል፡፡

 

 

Read 1021 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 09:13