Saturday, 02 September 2017 12:19

‹‹ሸክሜ እና ፍቅር››

Written by  በሚኪያስ ጥ.
Rate this item
(6 votes)


       ሸክሙ ከበደኝ፡፡ የማላውቀው ጓዝ በውስጤ ተንከርፍፎ ተቀምጧል፡፡ እኔ ‹‹እንዲህ›› ብዬ አልጠራውም፤ እርሱም ‹‹እንዲህ›› ብሎ፣ራሱን አይጠራም፡፡
ሁለታችንም ያለ ስም ዕዉቂያ፣ ያለ አድራሻ  መለዋወጥ የተዋወቅን ወዳጆች ነን፡፡
ሲያሰኘን የማናደርገዉ ነገር የለም፡፡ እናወጋለን፣ እንጫወታለን፣ እንላፋለን!
ከማውጋቱ በአንዱ ቀን፣ እንዲህ አለኝ - የውስጤ ሸክም፡፡
‹‹አቶ ባለ ገላ! ጠንካራ ሰውነት አለህ?!›› ሊፈትነኝ ጠየቀኝ፡፡
‹‹እ…ምን አይነት ጥያቄ ነዉ?›› ተርበትብቼ፣ ጥያቄዉን በጥያቄ እየመለስኩ፡፡
‹‹ሸክምን የሚሸከም - የማይለግምና የማይሰለስል ገላ አለህ ወይ?››
‹‹አለኝ!›› በልበ - ሙሉነት መለስኩ፡፡
አያ ሸክሞ፣ አንጀቴ ላይ እየተንፈራፈረ ሲስቅ ተሰማኝ፡፡ የሆዴ አውታሮችም በአንጀቴ መረባበሽ የተነሳ ክፉኛ እየተናጡ ነዉ፡፡
‹‹ምነው?›› እኔም በተራዬ ጠየቅሁ፡፡
‹‹ሸክምን የሚቋቋም ገላ ካለህ፣እንዴት የሆድህ አውታሮች ይርበተበታሉ?››
‹‹ይሄ’ኮ አንተ…›› አቋረጠኝ፡፡
‹‹በል-በል! ዞረህ ደግሞ ወደ’ኔ አትምጣ! በፊት ያቺን የዋህ ልጅ በልብህ ስትረግማት እያየሁ ዝም አልኩ፤ አሁን ደ’ሞ ወደ’ኔ ልትመጣ ነዉ?›› እግሩን አመሳቀለና፣ ትልቁ አንጀቴ ላይ አረፍ አለ፣ ‹‹እኔ’ኮ እርሷ ልካኝ፣ እርሷ አዝዛኝ አይደለም - እዚህ የማይረባ ገላህ ውስጥ የተቀመጥኩት፡፡ በራሴው ፍላጎት ነዉ፡፡ ‹እስቲ! አቅምህን ልፈትነው፤ ደረጃህን ልመጥነው› ብዬ ገባሁ፤ ይኼዉ፣ ባ’ንዴ ‹ልፍስፍስ› ስትል አየሁዋ!››
‹‹ለምን?እንዴት?...›› ተደናግጬ ጠየቅሁት፡፡
‹‹ለምን? ማለት ጥሩ፤ ‹እንዴት?› ማለት ጥሩ!›› ብሎ ጉሮሮዉን ጠራረገ፣ ‹‹መጀመሪያ፣ ታሪካዊ ስህተት የሰሩት አይኖችህ ናቸዉ፡፡ አጓጉል ይህቺ ሴት ላይ አርፈዉ፣ አዕምሮህ እንዲመኛት አደረጉ። ሁለተኛ፣ ትልቁ ባለ ስህተት አዕምሮህ ነዉ፡፡ እርሱ ልቦናዋን ከመመርመር ይልቅ መቀመጫዋን፣ አይኗን ጠልቆ ከመመርመር ይልቅ የሽፋሽፍቷን ውበት ማጤን ያዘ፡፡ እና’ሳ! አሁን ደግሞ ስህተተኛዉ ማነዉ? ልብህ! ዘልለህ ‹ወደድኳት› እንድትል፣ እርሱ በደንብ - እንዲያውም ከዚያም በላይ - እንድትደፋፈር አደረገህ››
ፉት የሚለውን ፉት ብሎ ቀጠለ፡፡
‹‹ከ’ዛ ሄድክ - አወራሃት - በሆነ ነገር አማለልካት። እርሷም ጅል ናትና ከነፈችልህ፡፡ እዚህ ላይ ‹ከረፈፉ› ማነዉ?››
አልሰማሁትም፤ ከላይ አያ ሸክሞ፣ ያወራውን ሁሉ አዕምሮዬ ዉስጥ የሚገኝ አንድ ቃለ-ጉባዔ ያዥ የከተበው መሆን አለበት፡፡ እኔ’ማ ቀልቤና ሰዉነቴ ከተፋቱ ቆዩ’ኮ!
ሃሳቤ ወደ’ርሷ ሮ…ጠ፡፡
የተዋወቅኳት ከወራት በፊት ቢሆንም፣ነገሩን በአዕምሮዬ ስክሪን ላይ ስመለከት የቀናት ያህል ይሰማኛል፡፡
አንድ መጽሃፍ ቤት ነበር፡፡ በ’ዛች ጨርጫሳ የከተማ ቀበሌ ውስጥ ከጠላ ቤትና ከ‹‹ጃምቦ ሃዉስ››፣ ከፍ ካለ፣ ከ‹‹ዲኤስቲቪ›› ቤት በቀር ሌላ ነገር ማግኘት የማይታሰብ ነዉ፡፡ በበጋ አስመራሪዉ አቧራ፣ በክረምት መረሬ ጭቃ ለመንቀሳቀስ ጸር ናቸዉ፡፡ እኔም በበጋዉ ላይ ተከስቼ፣ በአስመራሪዉ አቧራ ዉስጥ እግሬን እያናኘሁ እጓዛለሁ፡፡
መጽሃፍ ቤቱ ሩቅ ነዉ፤ ግፋ ቢል እስከ 45 ደቂቃ ድረስ ይፈጃል፡፡ ከምንሳለምበት ‹‹ክርስቶስ-ሳምራ›› ገዳም የበለጠ ይርቃል፡፡
የቀበሌ መታወቂያዬን በቀኝ እጄ ጨብጬአለሁ፤ በሌላ እጄ ደግሞ ጥቅልል ኩርቱ ፌስታል። መታወቂያውን መጽሃፍ ለመከራየት፣ ኩርቱ ፌስታሉን ‹‹ቡሌ›› ለመልቀም ታጥቄያለሁ፡፡
እንደ ምንም መንገዱን ከነጓጁ ሰዓት ጋር ገፍቼ፣ ቤቲቱ’ጋ ደረስኩ፡፡
ነጠላ ጫማዬ ላይ ያረበበውን አቧራ አራግፌ ወደ ዉስጥ ዘለቅኩ፡፡ ሼልፍ ሙሉ መጽሃፍት ተደርድረዉ ከፊቴ ተገትረዋል፡፡
ከመጀመሪያዉ ሼልፍ ጀመርኩ፡፡
‹‹እንደ ብረት ጠንካራ - ኒኮላይ ኦስቶርቭስኪይ››፤ ‹ከእናቴ ሌላ እንደ ብረት ጠንካራ ማን አለ?› በልቤ፡፡
‹‹እናት - ማክሲም ጎርኪይ››፤ ‹እናትነትን ማን ክእኔ እናት ነጥቆ ይወስዳል?!›
...እያልኩ፤ ከመጽሃፍቱ ጋር ነገር እየተወራወርኩ ስሄድ፣አንዲት ደንቃራ  ከፊቴ ተደቀነች፡፡
አንድ ረዥም፣ ፊተ-ክብና ቅርጻም ሴት፣ ከፊቴ ተገትራ፣ መጽሃፍ ታገላብጣለች፡፡
ርዕሱን ለማየት አንገቴን ከ’ነፊቴ አዘመምኩ፡፡
‹‹የኮሎኔል መንግስቱ ሃ/ማርያም ትዝታዎች- ገነት አየለ አንበሴ››
ደንግጬ ፊቴና አንገቴን አብሬ ወደነበሩበት መለስኩ፡፡ የመንግስቱን ሃያልነት በደንብ አዉቃለሁ። ታላቅ ወንድሜን ጣቱ ላይ ባንቀረቀባት እስክርቢቶ አይደለም - ተኩሶ የገደለዉ? ለምን አልደነግጥ?
ራሴን እንደምንም አረጋግቼ፣ ወደ ልጅቱ ቀረብኩ፤የ’ሷ ውበት የሚታወቀው ሲቀርቡ እንጂ ሲርቁ አይደለም፡፡ ስቀርባት እየገሞራች - ይበልጥ እየገሞራች መጣች፡፡
አይኖቿ ሲያተኩሱኝ፣ በግራ በኩል ወደአለው በር ዞርኩ፡፡
‹‹ምነዉ? የፈለግከዉ ነገር አለ?›› አይኖቿን እኔ ላይ ተክላ፡፡
‹‹አዎ!›› ወደ በሩ እንደዞርኩ፡፡
‹‹ምን?...››
‹‹መጽሃፉን…››
‹‹መጽሃፉን ምን?...›› ግራ ተጋብታ ጠየቀች፡፡
‹‹አዉሺኝ!›› የሞት ሞቴን፡፡
‹‹እሺ!›› ብላ፣ መጽሃፉን አስረከበችኝ፡፡
ተደናግጬ፣ መጽሃፉን ይዤ ወደ ቤት!
መጽሃፉን ሁለት ሌሊት በፍርሃት የሳሎኑ ቡፌ ላይ አስቀምጬ አደርኩ፤ መንግስቱ እንደ ወንደሜ እንዳይገድለኝ፡፡ በኋላ ላይ በረደልኝና አንብቤ ጨረስኩት፡፡ ‹‹የት?›› ብዬ ልመልስላት? ግራ ግብት ቢለኝ፣ ጓደኛዬን አናገርኩት፡፡ ተፈልጋ ስትገኝ፣ ጎረቤቴ ሆና ቁጭ፡፡ አጠገቤ ባለግርማ ሞገስ በር፣ የ’ርሷና የቤተሰቦቿ ቤት ኖሯል፡፡
አንኳኳሁ፤ ተከፈተልኝ፡፡
‹‹ኦዉ!...መጽሃፉ እንዴት ነበር?›› ፈገግታ ፊቷ ላይ ዘርታ ጠየቀችኝ፡፡
‹‹እየፈራሁ አነበብኩት…›› ተሽኮርምሜ፡፡
‹‹ለምን?›› በመደነቅ፡፡
‹‹ወንድሜን መንግስቱ ስለገደለዉ ፈርቼ…››
ሳቀች፡፡ ‹‹አይዞህ- አትፍራ! እርሱ’ኮ…››
ልትጠቅሰዉ የፈለገችዉን ቃል አወቅሁትና ‹‹እፎይ!›› አልኩ፡፡
‹‹እንተዋወቅ?›› እጄን ዘርግቼ ጠየቅኋት፡፡
‹‹ሜቲ››
‹‹ምን አይነት ስም ነዉ?›› ገርሞኝ፡፡
‹‹እኔ’ንጃ! ኮስማናዉ አባቴ ነዉ ያወጣልኝ፡፡ ወፍራሟን እናቴን ታውቃታለህ?››
‹‹አላውቃትም፤ ማናት?››
‹‹ወፍራም፣ ወጣት - መሳይ ፣አሁን ቮልስ የገዛች…››
‹‹አወቅኳት፤ የ’ርሷ ልጅ ነሽ?››
‹‹አዎ!›› በደስታ መለሰች፣‹‹ያ’ንተስ ስም?››
‹‹መሳይ››
በዚሁ ተዋወቅን፡፡ ቀን ቀንን ሲተካ፣ ያልታወቀ ስሜት በአዉሎ ነፋስ መልክ ሁለታችንም ገረፈን። ‹‹አውሎ ነፋሱ ከየት መጣ? ማን አስነሳው?›› ብዬ ጠይቄ ነበር፡፡ መልስ አጣሁ፡፡ አንጀቴንም የተቆጣጠረ ሸክም ተንሰራፋ፤ የሚያወራ ሸክም!
‹‹አንቺን አውርቶሽ ነበር?›› ከምሽቶች በአንደኛዉ ጠየቅኋት፡፡
‹‹ማን?››
‹‹አያ ሸክሞ!››
ሳቀች፤ አስደናቂ ነዉ - ሳቋ፡፡
‹‹…የሚባል ሰዉ አላዉቅም››
‹‹አንጀትሽ ዉስጥ…›› አቋረጠችኝ፡፡
‹‹በል! ተረትህን ወዲያ!›› ብላ፣ ጸጉሬን ደባብሳ ሳቀች፡፡
ትውስቱ በዚህ ሲያበቃ፣ የአያ ሸክሞ ወግ ቀጠለ፡፡
‹‹ስታሳዝን ግን! ምግብ አትበላም- ባ’ንተ ምክንያት፡፡ አታወራም- ባ’ንተ ምክንያት፡፡ አታነብብም- ባ’ንተ ምክንያት…›› የአበሳ መዓት  ዘረዘረብኝ፡፡
‹‹ለምን?››
‹‹ባ’ንተ ምክንያት! ወድዳህ! ቤተሰቦቿ በዛች ቮልስ ወይ ወንቅሸት፣ወይ እዚህ ሰፈር ካለዉ ገዳም እየወሰዱ ያስጠምቋታል፤ዋጋ የለውም እንጂ!››
‹‹እንደ’ርሷ ‹ታመም› ነዉ የምትለኝ?›› አናደደኝ።
‹‹የጥፋትህን ምስ መቅመስ አለብህ፤ ራስህን ማጥፋት - መቅጣት አለብህ!››
‹‹ለምን?›› በድጋሚ ጥያቄ፡፡
‹‹ጠንካራ ገላ የለህም፤ ሰው ጎድተሃል፡፡ ስለዚህ…››
አያ ሸክሞ ተናግሮ ሳይጨርስ፣ በረኪናውን አፌ ላይ ለጉሜ ጨለጥኩት፤ ከዛ በኋላ ምን እንደተፈጠረ አላውቅም...ሲነግሩኝ ግን፣
‹‹ጥፋት ወይስ ስርየት? ...ሃጥያት ወይስ ስርየት?...ሜቲ ወይስ እኔ?››
አረፋ እየደፈቅኩኝ፣ ለፈለፍኩ፤የቅጣቴን ምስ እየገመጥኩ፡፡

Read 5058 times