Print this page
Sunday, 03 September 2017 00:00

በየዓመቱ ለእኛ እንቁጣጣሽ

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በየዓመቱ ለእኛ እንቁጣጣሽ
ደስ ይበለን እንኳን ደህና መጣሽ
ለማለት ያብቃንማ! እንዲህ የሚሆነው በይስሙላ ወሬ ያልተቀባባ፣ በቃላትና በባዶ መፈክር ያልተኳኳለ ተስፋ ሲኖር ነውና! የሚያልፈውን ዓመት “ከመጪው ይሻላል” ከሚል አስተሳሰብ ነጻ ሲኮን ነውና!
ለብዙዎች ምንም ምቾት ያልሰጠው ክረምት ሊወጣ ጫፍ ላይ ነው፡፡ “በቅርብ ጊዜ አይደለም እንዴ የገባው!” የምንለው 2009 - በምን ፍጥነት እንደሮጠ አንድዬ ይወቀው - ጓዙን ጠቅለሎ ሊወጣ ደርሷል፡፡ ጦሱንም ጠቅለሎ ይሂድልን፡፡
ዓመት ሁለት ዓመት ሲሄድ እያያችሁ
ጊዜው ገሠገሠ ለምን ትላላችሁ
በዘመን ግሥገሣ ዕድሜያችን ተማርኮ
ያለፍነው እኛ ነን  ጊዜ አይደለም እኮ
አሉ ከበደ ሚካኤል፡፡ መለስ ብለን ስናየው፣ እውነትም የሄደ ነገር ያለ አይመስልም፣ ከእድሜ በስተቀር፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ዘንድሮ ለምንድነው ሰዎች ‘ለመጪው ዓመት እቅዴ እንዲህ ለማድረግ ነው፣ እንደዛ ለማደረግ ነው አይነት ነገር ሲሉ የምንስማው፡፡ የተለመዱት ሲጋራ አቆማለሁ። መጠጥ አቆማለሁ ምናምን ነገሮች እንኳን ብዙ አይሰሙም ነው ወይስ ሲጋራ ማጨስና መጠጥ ማብዛት “ሶ ኋት!” ማሰኘት ጀምረዋል?
ጥላሁን እንዳለው የእውነትም ከልባችን…
በየዓመቱ ለእኛ እንቁጣጣሽ
ደስ ይበለን እንኳን ደህና መጣሽ
ለማለት ያብቃንማ!
በፊት እኮ የእቅዶች እጥረት አልነበረብንም፡፡ “ለመጪው ዓመት እቅድህ ምንድነው?” ስንባል… አለ አይደል…በእውነት የተዘጋጀንበት ይሁንም፣ ‘በህልም ደረጃ’ ያለ ይሁንም… የምንለው አናጣም ነበር፡፡
“እቅዴ የውጪ ስኮላርሺፕ ፈልጌ ማግኘት ነው፡፡”
“የሚቀጥለው ዓመት እቅዴ እዚህም እዛም ተሯሩጬ፣ ቤት መስሪያ ገንዘብ ማጠራቀም ነው፡፡”
“የእኔ እቅድ ባል አግብቼ፣ ቤተሰብ መመስረት ነው፣” አይነት ነገር እንል ነበር፡፡
እናላችሁ… “እቅድ አለኝ” ማለት እንኳን የሆነ ቅንጦት ነገር ሊመስልብን ምንም አልቀረውም፡፡  እንዲህ ለትንበያ እንኳን በሚያስቸግር የአየር ሁኔታ ውስጥ ሆነን፣ ጧት ጸሀይ ብልጭ ስትል. “ደግሞ እስኪመሽ ድረስ ምን ይከሰት ይሆን!” በምንልበት ጊዜ ራቅ አድርጎ ማሰቢያ ጉልበት እያጣን ነው፡፡
“የ2010 እቅዴ “አንዲት የእቃ ቤት የምትሆን ትንሽዬ ክፍል መጨመር ነው፣” ብሎ ነገር አስቸጋሪ ነው፡፡
በየዓመቱ ለእኛ እንቁጣጣሽ
ደስ ይበለን እንኳን ደህና መጣሽ
ለማለት ያብቃንማ!
ዘንድሮ ልናቅደው የምንችለው ስንትና ስንት ነገር አለ! የ“አቆማለሁ” ነገር ከተነሳ ልናቆማቸው የሚገቡ፣ በእንጭጩ ልናስቀራችው የሚገቡ ነገሮች ለቁጥርም ሳያስቸግሩ አይቀሩም፡፡
“ወይ ጉድ! እንደው መጨረሻችን ምን ይሆን!”  
“ይሄንን ሊያሳየኝ ነው ያቆየኝ!”
እየተባሉ በአግራሞትና ‘በወቸጉድ’ ብቻ ትከሻችንን እያዞርንባቸው፣ ‘ውሻው በቀደደው ጅብ እንዳይገባ’ ልንደፍናቸው የሚገቡ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡
እናላችሁ… ከአንድና ሁለት ቀን አልፎ ሂያጅ ሳለና መነፋነፍ ብሶ ዘለዓለም እንደማይለቅ ‘ካንሰር’ እየተጣበቀብን የፍረጃ ደዌ አለ፡፡ እናማ…ብዙ ነገሮች ገልጠን ስናያቸው የሆነ የአገር ልጅነት፣’ ‘የዘር’ ነገር ከጀርባቸው ስናይ ሊያሳስበን ይገባል፡፡፡ “ይሄ ነገር አሪፍ ነው፣” ያልነው ነገር ጠለቅ ብለን ስንመረምረው፣ የሆነ ቦታ ላይ እንዲህ አይነት ‘ፈርጆ የመጥቀምና የማግለል ክር’ ስናገኝ ሊያሳስበን ይገባል፡፡
እናላችሁ… “በሚቀጥለው ዓመት ሰዎችን በተወለዱበት ስፍራና በዘራቸው መፈረጅ እተዋለሁ፣” ማለት የሚገባን ሰዎች ቁጥራችን እየበረከተ ነው፡፡
እግረ መንገድ… ከወራት በፊት አንድ ወዳጃችን የወንድሙን ሰባት ወይም ስምንት ዓመት የሚሆነውን ልጅ “ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ልጁ ግራ ገባው፡፡ “ስታድግ ምን ትሆናለህ?” ብሎ ጥያቄ ምንድው? አድጎ የለም እንዴ! ትልቅ ሆኖ የለም እንዴ! ስማርትፎን፣ ታብሌት፣ ላፕቶፕ ይጠቀማል አይደል እንዴ! ከጓደኞቹ ጋር በስማርት ፎኖ ‘ቻት’ ያደርጋል አይደል እንዴ! “ስታድግ ምን ትሆናለህ?” ብሎ ጥያቄ ምንድነው!
እናማ… “ልጆቹን ወዴት እየወሰድናቸው ነው!” “ምን እያሳየናቸው ነው!”  “ወደየትኛው አቅጣጫ እንዲጓዙ እየገፋፋናቸው ነው!” የምንልበት ዘመን ላይ ነን፡፡
እንደ እውነቱ አሁን፣ አሁን “ስታድግ ምን መሆን ትፈለጋለህ?” ተብሎ ሲጠየቅ፣ ብዙ ጊዜ አንሰማም። ለምን እንደሆን ባለሙያዎቹ ይንገሩን፡፡ ምናልባት ወላጆች ራሳቸው፣ ልጆቻቸው ምን እንደሚፈልጉ አስበውት አላወቁ ይሆናል፡፡
ሀሳብ አለን… “ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ?” በዘንድሮ ልጆች የሆነ ጥናት ይካሄድልንማ!  እንደ ድሮው፤
“ፓይለት መሆን እፈልጋለሁ…”
“ዶክተር መሆን እፈልጋለሁ…”
“ኢንጂነር መሆን እፈልጋለሁ…”
ምናምን አይነት የወደፊት ምኞቶች በምን ያህል ‘ፐርሰንት’ እንደቀነሱ ይጠናልንማ!
ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…በቀዳሚነት “አርቲስት መሆን እፈልጋለሁ” “ዘፋኝ መሆን እፈልጋለሁ፣” የሚሉ የሚበዙ ይመስለኛል፡፡ ልክ ነዋ…እነኛን ‘ፏ’ ያሉ አርቲስቶችና የዘፋኞችን ‘ክሊፖች’ ሲያዩ ለምን አይማረኩ! የእውነትም ይበል የሚያሰኙ ትልቅ ምኞቶች ናቸው፡፡ “አርፈሽ ተማሪና ነርስ ወይም የቢሮ ጸሃፊ ሁኚ እንጂ የምን በየትያትር ቤቱ ማዘጥዘጥ ነው!” የሚባልበት ዘመን ታሪከ ሆኗል፡፡
በየዓመቱ ለእኛ እንቁጣጣሽ
ደስ ይበለን እንኳን ደህና መጣሽ
ለማለት ያብቃንማ!
በነገራችን ላይ፣ ስለ አርቲስትነት ካነሳን አይቀር… ሰኞ ዕለት ‘ማለዳ ኮከቦች’ ላይ ያየናቸው ልጆች የምር የሚገርሙ ናቸው…በተለይ ሴቶቹ! እነኚህ ልጆች ገና የትወናውን ዓለም ሊቀላቀሉ ትግል ላይ ያሉ ናቸው ብሎ ለማሰብ አስቸጋሪ የሆነ እጅ እስኪላጥ የሚያስጨበጭብ ችሎታ ነው ያሳዩን፡፡ አደባባይ የመውጣት እድሉን አጥተው፣ በየቤታቸው የተቆለፉ ችሎታው ያላቸው ስንት ወጣቶች  ሊኖሩ እንደሚችሉ ማሳያ ናቸው፡፡ (የማለዳ ኮከብ አዘጋጆች እየሠራችሁ ላላችሁት ሥራ፣ በእናንተው ቋንቋ፣ ‘ሰላሙን ያብዛላችሁ!’)
ስለ ዘፋኝነት ካነሳን ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው በሆነ አነስተኛ ግፋ ቢል ወር በሚያስቀጣ ደንብ መተላለፍ ተከሶ ዳኛ ፊት ይቀርባል፡ ዳኛው ትኵር ብለው አዩት፡፡
“ከዚህ በፊት አውቅሀለሁ?”
“አዎ፣ ክቡር ዳኛ፡፡”
“የት ነው የማውቅህ፡፡ አጥፍተህ እኔ ፊት ቀርበህ ነበር እንዴ?”
“እንደሱ አይደለም ክቡር ዳኛ፡ ሴት ልጅዎን ዘፈን ያስተማርኳት እኔ ነኝ፡፡”
ዳኛው ፊታቸው ቅጭም አለ፡ “እንግዲያው ሠላሳ ዓመት ጽኑ እስራት ፈርጃለሁ፣” አሉትና አረፉት፡፡ ‘ዘፋኝ አደርጋታለሁ’ ያላትን ልጅ አልቃሽ አድርጓት እንዳይሆን!
በየዓመቱ ለእኛ እንቁጣጣሽ
ደስ ይበለን እንኳን ደህና መጣሽ
ለማለት ያብቃንማ! እንዲህ የሚሆነው በይስሙላ ወሬ ያልተቀባባ፣ በቃላትና በባዶ መፈክር ያልተኳኳለ ተስፋ ሲኖር ነውና! የሚያልፈውን ዓመት “ከመጪው ይሻላል” ከሚል አስተሳሰብ ነጻ ሲኮን ነውና!
ሁሉም ይቀያየር ሁሉም ይቀያየጥ
የታቹ ላይ ይውጣ የላዩ ይገልበጥ
አልጋው መደብ ይሁን መደቡ ይሁን ቆጥ
ውኃ ሽቅብ ይፍሰስ ናዳ ዳገት ይውጣ
ሁሌ ታች ለሆኑት ለእነሱም ቀን ይምጣ
ያለቀሰው ይሳቅ የሳቀው ይቆጣ
ብለዋል መ/ገብረኪዳን የተባሉ ሰው፣ በ1968 የገጠሙት ግጥም ላይ፡፡ ሁሉም ነገር ጎርፍ እንዳመሳቸው የቴክሳስ ከተሞች ድብልቅለቁ ባይወጣም በእርግጥ በመጪው ዓመት ሊቀያየሩ፣ ሊቀያየጡ የሚገባቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ እነሱን ለይቶ ማውጣቱ ደግሞ ንጹህ ልብ፣ ንጹሀ ህሊናና ምንም ትርፍና ቅጥያ ነገር የሌለበት ንጹህ ሰብአዊነት ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ያድለንማ!
መልካም የበዓል መዳረሻ ይሁንላችሁ፡፡
በየዓመቱ ለእኛ እንቁጣጣሽ
ደስ ይበለን እንኳን ደህና መጣሽ
ለማለት ያብቃንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5301 times