Saturday, 07 April 2012 09:10

አዳም ሳንድለር ትወና ይብቃው ተባለ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው በ”አፕሪል ዘ ፉል” ዕለት በተካሄደው የሆሊውድ መጥፎ የፊልም ስራዎችና ባለሙያዎች “አዋርድ” ላይ ኮሜድያኑ አዳም ሳንድለር በፀሃፊነት፤ ፕሮዲውሰርነትና ተዋናይነት በሰራባቸው ፊልሞች 10 “ሽልማቶች”ን ሰብስቦ ክብረወሰን አስመዘገበ ፡፡ 32ኛው የራዚስ ስነስርዓት  በሳንት ሞኒካ  ካሊፎርንያ የተካሄደ ሲሆን ለአሸናፊዎች የሚበረከተው ስጦታ ግምቱ 5 ዶላር ብቻ ነው፡፡  አዳም ሳንድለር መንትዮችን በተወነበት “ጃክ ኤንድ ጂል” ፊልም አዋርድ በሁለቱም ፆታዎች የመጥፎ ተዋናይ ሽልማትን አግኝቶበታል፡፡ በራዚ አዋርድ የ32 ዓመት ታሪክ በራዚ አዋርድ  10 ሽልማቶች በመሸለም በሆሊውድ የመጀመርያው ባለሙያ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

መጥፎ የፊልም ስራዎችን እና ባለሙያዎችን በመምረጥ ለራዚ አዋርድስ ድምፅ የሚሰጡት በ46 የአሜሪካ ግዛቶች ያሉ 657 ባለሙያዎች እና ከሌሎች 17 አገራት የሚጋበዙ ባለሙያዎች ናቸው፡፡የራዚ አዋርድን የሚወስዱ ዝነኞች በስነስርዓቱ ላይ ባለመገኘት የሚታወቁ ሲሆን አዳም ሳንድለርም በፕሮግራሙ ላይ ስለመገኘቱ ማረጋገጫ አልተገኘም፡፡ ከዓመት በፊት በአዳም ሳንድለር ፀሃፊነት፤ፕሮዲውሰርነትና ተዋናይነት የታዩት ሶስት ፊልሞች “ጃክ ኤንድ ጂል”፤ “ጀስት ጎ ዊዝ ኢት” እና “ዙ ኪፕር” ሲሆኑ ፊልሞቹ በድምሩ ከ450 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቶባቸዋል፡፡ የሰራቸው ፊልሞች አክሳሪ ባይሆኑም ሳንድለር  ትወና ይበቃዋል በሚል በአሜሪካ 97 በመቶ የሚሆኑት የፊልም ሃያሲዎች ክፉኛ ነቅፈውታል፡፡  በ32ኛው የራዚስ አዋርድ ላይ የ42 ዓመቱ አዳም ሳንድለር በ11 የሽልማት ዘርፎች ታጭቶ አስሩን መውሰዱ ስራ ያሳጣዋል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡ በራዚ አዋርድ ታሪክ ታዋቂዎቹ ኬቪን ኮስትነር፤ ሄሊ ቤሪና ሳንድራ ቡሎክ በመጥፎ ተዋናይነት ለሽልማት ተመርጠዋል፡፡ ከ37 በላይ ፊልሞች የሰራው አዳም ሳንድለር በአማካይ በአንድ ፊልም እስከ 73 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስገባ ይታወቃል፡፡ የቦክስ ኦፊስ ሞጆ መረጃ እንዳመለከተው በ20 ዓመት የሆሊውድ ቆይታው በሰራቸው ፊልሞች በዓለም ዙርያ ከ3.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝቷል፡፡

 

 

Read 1057 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 09:12