Saturday, 02 September 2017 11:52

“ጳጉሜን ለጤና”ዓመታዊው ነፃ የምርመራ አገልግሎት በሚቀጥለው ሳምንት ሊጀመር ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(7 votes)

በውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል የሚካሄደው “ጳጉሜን ለጤና” የተሰኘው አመታዊው ነፃ የምርመራ አገልግሎት የፊታችን ረቡዕ ይጀምራል፡፡
ማዕከሉ በተለያዩ ህመሞች ተይዘው የኤምአርአይ፣ የሲቲስካንና የአልትራሳውንድ ምርመራዎች በሃኪም ታዞላቸው በገንዘብ እጦት ምክንያት ምርመራውን ማካሄድ ላልቻሉ ህሙማን ነፃ የምርመራ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
በዚሁ “ጳጉሜን ለጤና” በተባለው ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን ከጳጉሜ 1 ቀን ጀምሮ እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ምዝገባ ማካሔድ ያስፈልጋል፡፡ በማዕከሉ ቀርበው አሊያም በስልክ ደውለው  ምዝገባ ላካሔዱና በሃኪም የታዘዘላቸውን የምርመራ ወረቀት ለሚያቀርቡ እንዲሁም ምርመራውን ለማድረግ የሚያስችል የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ህሙማን የኤምአርአይ፣ የሲቲስካንና የአልትራሳውንድ ምርመራዎች በነጻ ይደረጋል ተብሏል፡፡
ህሙማኑ በዚህ ዕድል ለመጠቀም ምርመራው በሃኪም የታዘዘላቸውን መሆኑን እንዲሁም የገንዘብ አቅም እንደሌላቸው የሚያረጋግጥ መረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ማዕከሉ ከዚህ ቀደም የነፃ ምርመራ አገልግሎቱን የሚሰጠው በመንግስት የህክምና ተቋማት ህክምናቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ ህሙማን ብቻ የነበረ ሲሆን በዘንድሮው ዓመት ግን ህክምናቸውን በግል የጤና ተቋማትም እየተከታተሉ፣ በሃኪም የሚታዘዝላቸውን ምርመራ ለማድረግ አቅም ለሌላቸው ህሙማን፣ ነፃ የምርመራ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡  ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል፤ “ጳጉሜን ለጤና” በሚለው ፕሮግራም ላለፉት ሰባት ዓመታት ከ7 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ህሙማን ነፃ የምርመራ አገልግሎት መስጠቱን አስታውቋል፡፡

Read 2872 times