Print this page
Sunday, 27 August 2017 00:00

ኢህአዴግ በተለመደው ይቀጥላል ወይስ ራሱን ያስተካክላል?

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(5 votes)

  ባለፈው ሳምንት ጽሁፌ በገለጽኩት ሁኔታ ኢህአዴግ የሀገሪቱን የፖለቲካ መድረክ ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የእግር መትከያ ቦታ ካሳጣቸው በኋላ፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው፣ በየዓምስት አመቱ “ኑ እንፎካከር” የሚላቸው ራሱ የሚያቅደው፣ ራሱ የሚቆጣጠረውና፣ ራሱ የሚያስፈጽመው “ምርጫ” የሚመስል ብሔራዊ ምርጫ አዘጋጅቶ ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በከፍተኛ የስራ አጥነት፣ ስር በሰደደና ፈርጀ ብዙ በሆነ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ፍትህ በጎደለው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፤ እንዲሁም በከፍተኛ የሰብአዊና የዲሞክራሲ መብቶች ጥሰት የተነሳ ዜጎቹ ከፍተኛ ቅሬታ አድሮባቸው፣ በእጅጉ የተቀየሙት ገዢ ፓርቲ፤ በነፃ ምርጫ ከ99% በላይ የህዝብ ድምጽ አግኝቶ ያሸንፋል ብሎ ማሰብ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ ማናቸውም አይነት ገዢ ፓርቲ፣ 99% የህዝብ ድምጽ አግኝቶ ማሸነፍ የሚችለው፣ ብቻውን ከተወዳደረ አለያም ምርጫውን ከሂደቱ እስከ መጨረሻ አፈፃፀሙ ድረስ ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረው ብቻ ነው፡፡
ኢህአዴግም በግንቦት ወር 2007 ዓ.ም በተካሄደው አምስተኛው ብሔራዊ ምርጫ፣ 99.6% ድምጽ በማግኘት፣ በኢኳቶሪያል ጊኒ ዲሞክራቲክ ፓርቲ በ2005 ዓ.ም ተይዞ የነበረውን የአፍሪካ የምርጫ ውጤት ሬከርድ መስበር የቻለው፣ ይህን ዘዴ በመጠቀም እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡
ላለፉት 30 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆየውና በፕሬዚዳንት ቴወዶሮ ኦቢያንግ ምባሶጎ የሚመራው የኢኳቶሪያል ጊኒ ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ በ2005 ዓ.ም በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ያሸነፈው፣ 99% ድምጽ በማግኘት ነው፡፡ ይሄው ፓርቲ ከሴኔት ምክር ቤት 70 መቀመጫዎች 69፣ ከተወካዮች ምክር ቤት፣ መቶ መቀመጫዎች ደግሞ ዘጠና ዘጠኙን አሸንፏል፡፡
ፕሬዚዳንት ቴወዶሮ ኦቢያንግ ምባሶጎ፤ ከሰላሳ ዓመት በፊት ፕሬዚዳንት የነበሩትን አጎታቸውን ደም ባፈሰሰ መፈንቅለ መንግስት አስወግደው ስልጣን ከያዙ በኋላ፣ የኢኳቶሪያል ጊኒን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ በተሻለ ለሚያውቅ ሰው፣ ፓርቲያቸው 99% ድምጽ አግኝቶ፣ የ2005ቱን ምርጫ ማሸነፉ፤ እርሳቸውም በ2008 ዓ.ም የተካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ 93.53% ድምጽ አግኝተው መመረጣቸው፣ ጨርሶ ሊያስገርመው አይችልም፡፡
ምነው ቢባል፣ ላለፉት 30 ዓመታት የገነቡት የፖለቲካ ስርአት የአውራ ፓርቲ ስርአት ብቻ ሳይሆን የእሳቸውን ፈላጭ ቆራጭ ፕሬዚዳንትነት፣ በሀገራቸውና በህዝቡ ላይ ያረጋገጠ ስርአት በመሆኑ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ቴወዶሮ ኦቢያንግ ምባሶጎ፤ ይህን የመሰለውን የአውራ ፓርቲና የፈላጭ ቆራጭ፣ ፕሬዚዳንታዊ አመራር ስርአት ሲገነቡ፣ የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ተቀናቃኞቻቸው እጣ ፈንታ ምን እንደነበር ለታሪክ ነጋሪዎች የተተወ ነው፡፡
በዚህ የተነሳም የኢኳቶሪያል ጊኒ ህዝብ፣ ገዢውን የኢኳቶሪያል ጊኒ ዲሞክራቲክ ፓርቲና ፕሬዚዳንቱን ድምፁን አሰምቶ መቃወም ይቅርና ለማሞገስ እንኳ ፈጽሞ የማይደፍር፣ በከፍተኛ ፍርሀት የተዋጠ ህዝብ መሆኑ፣ በድፍን አለሙ የታወቀ ነው፡፡
ዛሬ ገዥው ፓርቲ በሁሉም ነገር ከሀገሪቱና ከህዝቡ በላይ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ቴወዶሮ አቢያንግ ምባሶጎ ደግሞ ከፓርቲው በላይ ናቸው። በነዳጅ ዘይት ሀብት የበለፀገችው የኢኳቶሪያል ጊኒ ኢኮኖሚ ደግሞ የብሉምበርግ ቴሌቪዥን የኢኮኖሚ ተንታኝ አምና ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ፤ እንዳለው፤ “የኢኳቶሪያል ጊኒ ኢኮኖሚ ከሚባል ይልቅ የፕሬዚዳንቱ፣ የቤተሰባቸውና የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣናት ኢኮኖሚ ቢባል ይቀላል”፡፡
የእኛም ሀገር ሁኔታ ከዚህ ብዙም የተለየ አይደለም፡፡ በሁሉም ነገር ቢሆን ኢህአዴግ ከሀገሪቱና ከህዝቡ በላይ እንደሆነ አሳምረን የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በተመለከተም ሙሉ በሙሉ እንኳ ባይሆን በአብዛኛው ኢህአዴግ ባቋቋማቸው ግዙፍ የንግድ ድርጅቶችና ባጠገቡ በተኮለኮሉ የኢኮኖሚ ተዋናዮች ቁጥጥር ወይም የበላይነት ስር የወደቀ ነው፡፡ ይህን የምለው እንዲያው ለሀሜት ሳይሆን፣ ከራሱ ከኢህአዴግ የዘንድሮው “የጥልቅ ተሀድሶ” ግምገማዎቹ በመነሳት ነው፡፡  
ኢህአዴግ በመላ ሀገሪቱ ከመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ይልቅ እሱ ብቻ የሚገንበት የአውራ ፓርቲ ስርአት የመገንባት አላማውን ለማሳካት ከወሰዳቸው ወሳኝ እርምጃዎች አንዱ፣ በዜጎች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ ህገ መንግስታዊ መብት ላይ የተለያዩ ገደቦችና ክልከላዎችን በማበጀት፣ የሀገሪቱን የሚዲያ ምህዳር ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ስር ማድረግ ነው፡፡
የድህረ - ደርግ ኢትዮጵያን የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ፣ በአንድ አረፍተ ነገር ግለፁ ቢባል፣ ከሁሉም የተሻለው አገላለጽ፤ “እንደተወለደ አረፈ” የሚለው ነው፡፡ በኢህአዴግ አገዛዝ የመጀመሪያ አመታት የተለያየ ይዘት ያላቸው በርካታ የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች ታትመው መውጣትና የተለያየ የፖለቲካ አቋም የሚያንፀባርቁ ጽሁፎችን ማስተናገድ መጀመራቸው በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ይበል ተብሎለት ነበር፡፡
ግሪካውያን፤ “የትንግርት እድሜ ዘጠኝ ቀን ነው” እንደሚሉት፣ ይህ አዎንታዊ ሁኔታ እንደ አጀማመሩ ለመዝለቅ አልታደለም፡፡ የኢህአዴግ ጠንካራ የቁጥጥር መዳፍ ያረፈበት ገና ከጅምሩ ነው፡፡
ኢህአዴግ ቀድሞውኑ ከሱ ፍላጎት በተቃራኒ የሚቆምና ተቃራኒ አመለካከቶችን በሚገባ የሚያስተናግድ የፕሬስ ውጤትን ‹አርሂቡ› የሚልበት ፍላጎትም አንጀትም ፈጽሞ አልነበረውም። እናም የፕሬስ ነፃነትን በተመለከተ ባለፉት 25 ዓመታት ያወጣቸው የተለያዩ አዋጆች፣ በሀገሪቱ የፕሬስ ነፃነት ላይ የተለያዩ ክልከላና እገዳዎችን በመጣል ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡
በእነዚህ ከልካይና አጋጅ አዋጆች የተነሳ፣ የጋዜጠኞች በተለይም የግል ፕሬስ ጋዜጠኞች የእለት ተዕለት እጣ ስደትና፣ በአሸባሪነት ክስ ዘብጥያ መውረድ፤ የግል ጋዜጣና መጽሄቶች ህልውናም በየቀኑ መክሰም ብቻ ሆነ፡፡
ስለ ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ምሎ መገዘት የማይሰለቸው ኢህአዴግ፤ በ25 ዓመት የአገዛዝ ዘመኑ መቶ ሚሊዮን ህዝብ ላላት ሀገር፣ ያተረፈላት ጋዜጣና መጽሄቶች የእጅ ጣቶችን እንኳ የማይሞሉ መሆናቸው ሀፍረት ላይ እንደጣለው ግልጽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁኔታውን ተረድቶ ለማስተካከል ከመሞከር ይልቅ ለኢህአዴግ ቀላል የሆነለት ችግሩን በሌሎች ላይ ማመካኘት ነው፡፡ ኢህአዴግ የፕሬስ ነፃነትን እለት ተዕለት በማቀጨጭ የፈፀመውን ትልቅና አሳዛኝ ስህተት፣ “ከደሙ ንፁህ ነኝ” በሚል እንደ ጲላጦስ እጁን ለመታጠብ የሚሞክረው፣ “ባለፉት 25 ዓመታት የፕሬስ ነፃነትን መሰረት ለማስያዝና ለማጠናከር የሚያግዙ አዋጆችና ድንጋጌዎች ተግባራዊ ቢደረጉም የአገሪቱ የፕሬስ እንቅስቃሴ ግን የሚፈለገውን ያህል አልተጠናከረም፡፡” በማለት ነው፡፡
ነገሩ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ የሀገሪቱን ሚዲያ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር ማድረግ የፈለገው ኢህአዴግ፤ ሁሉንም ወገን በፍትሃዊነት ማገልገል የሚገባቸው የህዝብ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች በራቸውን መክፈት እርም ይሁንብን እንዲሉ አደረጋቸው፡፡ ይባስ ብሎም እነዚህ የሚዲያ ተቋማት በቅጡ ባልተረዱት፣ “ልማታዊ ጋዜጠኝነት” ሰበብ የጧት ማታ ስራቸው፣ በኢህአዴግ የልማት ስኬት እስክስታ መውረድ ብቻ ሆነና፣ የህዝቡን የቀን ተቀን ህይወት የገሀነም ያህል ያከበዱበትን ቁጥር ስፍር የሌላቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ ችግሮች ይፋ እንዲሆኑና በጊዜ መላ እንዲፈለግላቸው ለማድረግ ጊዜ የሚያጥራቸው ሆኑ፡፡
ኢህአዴግ የሚለውን ደግሞ ደጋግሞ ከማነብነብና አሰልቺ በሆነ “የልማታዊ ጋዜጠኝነት” ፕሮፓጋንዳ ከመባዘን ውጪ የተለዩ አማራጭ ሀሳቦችን ማቅረብ ሳይሆን ለማቅረብ መሞከር እንኳ በእነዚህ ተቋማት ዘንድ እንደ አይነኬ ወይም እንደ ነውር የሚቆጠር ሆነ፡፡
ህዝብ በሚከፍለው ታክስ የህልውና እስትንፋሳቸው የቆመው እነዚህ “የህዝብ ብዙኃን መገናኛ ተቋማት፤ ጭንቀቱን ጭንቀታቸው፣ ብሶቱን ብሶታቸው ጨርሶ እንዳላሉት የተረዳው ህዝብም፤ ቀስ በቀስ ልቡንና ቀልቡን ለውጭ ሀገር ሚዲያዎች፣ በውጪ ሀገር ለሚሰራጩ የሚዲያ አውታሮችና ለኢንተርኔት የማህበራዊ ሚዲያዎች ከፍቶ ሰጠ፡፡
ነፃና ጠንካራ የሲቪል ማህበራት፣ ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የራሳቸውን ገንቢ ሚና መጫወት እንደሚችሉ መናገር፣ የአንባቢን ንቃተ ህሊና አለአግባብ እንደ መሞገት ይቆጠራል፡፡ የሲቪል ማህበራት በሚንቀሳቀሱባቸው ክልሎች፣ ህዝቡ በተለይም የገጠር ነዋሪዎች ህገ መንግስታዊ ግዴታቸውን ብቻ ሳይሆን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውንም ጭምር ጠንቅቀው እንዲያውቁና ጥቅም ላይ እንዲያውሉ በማድረግ ረገድ ቀላል የማይባል ተግባር ከውነዋል። ይህ ተግባራቸው በተለይ በምርጫ 97 ምን ዓይነት ለውጥ እንዳመጣ በአብዛኞቻችን ዘንድ የታወቀ ነው፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ “ምሁራን” በተለይ ከ1997 ዓ.ም ወዲህ፣ “ሲቪል ማህበራት ለዲሞክራሲ ግንባታ የራሳቸው ዋጋ ቢኖራቸውም ባልተገባ መንገድ ሲተገብሩት ይታያሉ” የሚል ወቀሳ በተደጋጋሚ ያቀርባሉ፡፡ ይህን የ “ምሁራን” ወቀሳ፣ ኢህአዴግም ሙሉ በሙሉ ይጋራዋል፡፡
አስገራሚው ነገር፣ ኢህአዴግ የምሁራኑን ወቀሳ መጋራቱ ሳይሆን ለወቀሳው የሰጠው ተግባራዊ ምላሽ ነው፡፡ ኢህአዴግ ለዚህ ወቀሳ የሰጠው ምላሽ፣ ሲቪል ማህበራት ያልተገባ ነው የተባለውን መንገዳቸውን አስተካክለው በዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደቱ፣ ገንቢና ተገቢ ሚና መጫወት እንዲችሉ አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ ሳይሆን የማያላውስ አሳሪ ህግ በማውጣት፣ ፋይዳ ያለው ነገር እንዳይሰሩ፣ ማሽመድመድና ድራሻቸውን ማጥፋት ነው፡፡
ኢህአዴግ በሲቪል ማህበራት ላይ ባወጣው ህግ፣ የምርጫ 97 ቂሙን በመወጣት፣ የልቡን ማድረስ ችሏል፡፡ የሲቪል ማህበራት፤ በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት መጫወት የሚችሉትን ገንቢ ሚናና ሀገሪቱም ሆነ ህዝቧ ከዚህ ሊያገኙ የሚገባቸውን ትልቅ ጥቅም ግን ያለ አንዳች የኃላፊነት ስሜት ገድሎባቸዋል፡፡
እንግዲህ ላለፉት 25 ዓመታት እስካሁን ከሞላ ጎደል ባየነው አይነት መንገድ የተጓዘው ኢህአዴግ፤ በሀገሪቱ የመድብለ - ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ሳይሆን በራሱ የሚመራ የአውራ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት በመገንባት እንዳሻው ሆኗል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ 25 ዓመት ሙሉ የተደከመበት የአውራ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርአት የማታ የማታ ውጤቱ ምን እንደሆነ፣ እያገባደድነው ያለው ዓመት በግልጽ አሳይቶናል፡፡ ቀጣዩና ወሳኝ የሆነው ጥያቄ፤ “ኢህአዴግ የተሀድሶ ቀልዱን አቁሞ፣ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደቱን የምር ይጀምራል ወይስ ውጤቱ በታየው የአውራ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት መጓዙን ይቀጥላል?”  የሚለው ነው፡፡ ሁሉንም አብረን የምናየው ይሆናል፡፡  

Read 3052 times