Sunday, 27 August 2017 00:00

“መንግሥት የቤት ሥራውን አልሰራም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  ለ11 ወራት የዘለቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳው አብዛኞቹ ችግሮች ተፈተው ነገሮች ወደ ቦታቸው ተመልሰዋል በሚል ነው፡፡ ሆኖም ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ ማግስት ፖለቲካዊ ውጥረቶችና አለመረጋጋቶች ከቀን ወደ ቀን እየተባባሱ መጥተዋል፡፡ በቀን ግብር ግመታ ተቃውሞ መነሻነት፣በአማራና በኦሮሚያ አካባቢዎች ንግድ ቤቶችን የመዝጋት አድማ ተደርገዋል፡፡ መንግስት፣ህዝባዊ አመጽና ተቃውሞውን ተከትሎ፣የመንግስት ባለሥልጣናት ሹምሽረት አድርጓል፡፡ ከህዝቡ ጋር ውይይት አድርጌ፣መግባባት ላይ ደርሼአለሁም ብሏል፡፡ በቅርቡ ሙስና በፈጸሙ የመንግስት ባለሥልጣናትና ባለሃብቶች ላይ የወሰደው የጸረ-ሙስና ዘመቻም፣ ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ የመስጠት አካል መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡ ታዲያ ችግሩ ያለው የቱ ጋ ነው?
ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በበኩላቸው፤የህዝብ ጥያቄዎች መልስ አላገኙም ይላሉ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጥሎ በነበረባቸው ጊዜያት መንግስት መስራት የነበረበትን የቤት ሥራም አልሰራም በማለትም ይወቅሳሉ፤ይተቻሉ፡፡ ውይይት አድርጌአለሁ የሚለውም ከጉዳዩ ባለቤቶች ጋር ሳይሆን ከካድሬዎቹ ጋር ነው፤ለዚህም ነው ፖለቲካዊ ውጥረቱ ዳግም ያገረሸው ባይ ናቸው፡፡ አሁንስ መፍትሄው ምን ይሆን? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ አንጋፋ ፖለቲከኞችን፣ የህግ ባለሙያዎችንና የመንግስት አካላትን አነጋግሮ አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡ አሁንም ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ብቻ ነው፡፡

                      “አሁንም ግልፅ ውይይቶች ሊደረጉ ይገባል”
                            አቶ ገብሩ ገ/ማሪያም (ፖለቲከኛ)

      ባለፈው አመት ተፈጥሮ የነበረውን ግርግር ያመጣው፣ ኢህአዴግ የሚጠበቅበትን የቤት ስራ ያለመስራቱ ነበር፡፡ አሁንም እየሠራ አለመሆኑ ደግሞ የበለጠ አሣሣቢ ነው፡፡ በፊት የፖለቲካ ምህዳሩን ማጥበቡ፣ ከተቃዋሚዎች ጋር ፊት ለፊት ለመነጋገር ፍቃደኛ ያለመሆኑ፣ የህዝብን ጥያቄዎች በጊዜ መመለስ አለመቻሉ ነው፣  አስፈላጊ ላልሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የዳረገን፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀም በኋላ፣ ሰው በገፍ ከማሰር ይልቅ ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ መስጠቱ ላይ ቢያተኩር ኖሮ፣ ዛሬ  ውጤት እናይ ነበር፡፡ የካድሬ ስብሰባ አድርጎ፣ ከህዝብ ጋር ተወያይቻለሁ፣ ከህዝብ ጋር ተስማምቻለሁ ማለቱ ሃሰት መሆኑን፣ አሁን በየአካባቢው ካሉት ውጥረቶች መገንዘብ ይቻላል። ተስማምቻለሁ ባለበት አካባቢዎች  ነው ዛሬ ውጥረት የሚታየው፡፡ መቼም በቦታው ላይ አዲስ ህዝብ አልፈለቀም፡፡ ይሄ የሚያሳየን ውይይቶቹ ሁሉ የውሸት መሆናቸውን ነው፡፡ ለእኔ የሚሰማኝ፣ችግሩ ነገሮችን ከስረ መሠረታቸው መርምሮ፣ መፍትሄ መስጠት ያለመቻል እንደሆነ ነው፡፡
 በጥልቀት ታድሻለሁ፤ሙሰኞችን  እያሰርኩ ነው የሚለውም፣ ያን ያህል ወደፊት የሚያራምድ አይሆንም፡፡ እንደኔ አረዳድ፣ ህዝቡ ውስጥ ያለው ችግር አሁንም ከስር መሠረቱ አልተደረሰበትም። እርግጥ ነው በሙስና ላይ የሚወሰደው እርምጃ የረፈደ ቢሆንም የሚደገፍ ነው፡፡ ቢሆንም ይሄ ዋነኛ ችግር ሳይሆን የችግሩ ማሳያ ነው፡፡ ኦሮሚያ አካባቢ ፕሬዚዳንቱ አቶ ለማ መገርሣ፣ ህዝቡን ለማነጋገር የሚያደርጉት ጥረት መልካም ቢሆንም የሚፈልጓቸውን ሰዎች ብቻ ሳይሆን ሊሰሟቸው የማይፈልጓቸውን ሰዎችም ማነጋገርና ከእነሱ ጋርም መመካከር አለባቸው፡፡
አሁን ጥቂት ካድሬዎችን ሰብስቦ፣ ህዝቡ፣ ፀረ-ሠላም ሃይሎችን አውግዟል የሚለው ብዙ ርቀት የሚያራምድ አይደለም፡፡ የሃገሪቱ ችግር ከዚህ አይነቱ ፕሮፓጋንዳም በላይ መሆኑን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ እየታዩ ያሉ ውጥረቶች ማረጋገጫ  ናቸው፡፡ መቼም የሚሰማ የለም እንጂ በርካቶች ለሃገሪቱ ይበጃል ያሉትን ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡ እንደኔ ብቸኛ መፍትሄው፣ የለበጣ ሳይሆን ሃቀኛ ውይይት ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ማካሄድ ነው። ይሄ ሽንፈት አይደለም፡፡ ብልህነት ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም ህዝብና ሃገርን ለማረጋጋት ከተፈለገ፣ ግልፅ ውይይቶች ሊደረጉ  ይገባል፡፡

--------------

                           “መንግሥት የቤት ሥራውን አልሰራም”
                             አቶ ልደቱ አያሌው (ፖለቲከኛ)

       ከዓመት በፊት የተነሳው ብጥብጥ፣ የሀገሪቱን ከግማሽ በላይ አካባቢ ያካለለ ነበር፡፡ በውስጡ የተሳተፉ ሰዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው። ጥያቄው እንደየ አካባቢው የተለያየ መልክና ይዘት የነበረው ነው፡፡ አንዳንድ አካባቢ የመልሶ አስተዳደር፣ በሌላው የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት መከበር ጥያቄ እንዲሁም የሥርአት ለውጥ ጥያቄም ተነስቶ ነበር፡፡ በኔ ግምገማ፣ ለነዚህ ሁሉ ሰፊ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎች፣ መንግስት እስከ አሁን ለአንዱም የሚጠበቀውን ምላሽ አልሰጠም፡፡ የቤት ሥራውን አልሰራም፡፡
እኔ የታሪክ ተማሪ እንደመሆኔ፣ በሀገሪቱ የህዝብ እንቅስቃሴ ታሪክ ውስጥ እንደዚያ ያለ የህዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ታይቶ አይታወቅም። ለአፄያዊ ስርአት መለወጥ ምክንያት የሆነው እንቅስቃሴ እንኳ በመጠንም በይዘትም ይሄን ያህል የሰፋ አልነበረም፡፡ ይሄ ከፍተኛ ሀገራዊ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ መንግስት ስልጣን ከያዘ ከ25 ዓመት በኋላ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የመገደዱ ሚስጥርም የችግሩ ጥልቀትና ስፋት ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ በአንፃራዊነት ለጊዜውም ቢሆን መረጋጋት ፈጥሯል፡፡ ጥያቄው ይህን የአዋጅ ጊዜ ተጠቅሞ፣ መንግስት ምን ያህል የቤት ስራውን ሰርቷል ከሆነ መልሱ፣ ምንም የቤት ሥራ አልሰራም የሚል ነው፡፡
ፕሬዚዳንቱ የ2009 የፓርላማ መክፈቻ ንግግራቸው ላይ፣ ጥያቄው የዲሞክራሲ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ እርምጃዎቹ ህገ መንግስቱን እስከ ማሻሻል ሊዘልቁ እንደሚችሉና ከተቃዋሚዎች ጋር ያለ ገደብ በማንኛውም ጉዳይ ላይ  ድርድር እንደሚካሄድ፣ በዚህም የህዝቡ ጥያቄዎች መሰረታዊ በሆነ መልኩ ምላሽ እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በሂደት እንዳየነው፣ አዋጁ ታውጆ፣ ብዙዎቹ አካባቢዎች በወታደራዊ ቁጥጥር ስር ሲውሉና በሺዎች የሚቆጠሩ ወደ እስር ቤት ሲጋዙ፣ ነገሮች የተረጋጉ ሳይመስላቸው አልቀረም። ከዚያ በኋላ ከህዝቡ ጥያቄ ጋር የሚመጣጠን መልስ ለመስጠት አልተሞከረም፡፡ እንዲያውም ችግሩ የጥቂቶች ብቻ እንደነበር አድርጎ ነው መንግስት የተገነዘበው፡፡ የፀረ - ሰላምና የፀረ- ልማት ኃይሎች ችግር ብቻ እንደነበርና እነዚህንም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥሩ ስር እንዳዋለ አድርጎ ነው ያቀረበው፡፡ ከዚህ በኋላም ተመልሶ የሚመጣበት እድል እንደሌለ አድርጎ ነው መንግስት መናገር የጀመረው፡፡ መፍትሄዎች ተብለው ከየአቅጣጫው በሀሳብ ደረጃ ቀርበው የነበሩ ሳይቀሩ ተረስተዋል፡፡ ስለዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳው፣ ለህዝብ ጥያቄ ምንም አይነት ምላሽ ሳይሰጥ ነው፡፡
በእኔ እምነት፣ ባለፈው አመት የተነሳው  የህዝብ ጥያቄ መልስ አላገኘም፡፡ መልስ ባላገኘበት ሁኔታ ደግሞ በዘላቂነት የፖለቲካ መረጋጋት ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ስለዚህ የጊዜ ጉዳይ ይሆናል እንጂ ተመልሶ ችግሩ መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡ እኔ ፋና አዘጋጅቶት በነበረው የሸራተን ውይይት ላይ የሀገሪቱን ችግሮችና የመፍትሄ ሀሳቦች ሳቀርብ፣ መንግስት ተቀብሎ ሀሳቦቹን እንደማይሰራባቸው ጥርጣሬ ነበረኝ። የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ናቸው እውነቶችን እየደበቁ፣ ችግሩን እያባባሱ ያሉት የሚል ሃሳብ ባቀርብም፣ ይሄ ውይይት በመንግስት መገናኛ ብዙኃን ለህዝብ እንዳይደርስ ነው የተደረገው፡፡ ይሄ በራሱ፣ መንግስት ለለውጥ ራሱን እንዳላዘጋጀና ቅን እንዳልሆነ ያሳያል፡፡
ከዚያ በኋላም ህዝቡም ሆነ የፖለቲካ ሰዎች፣ ለሀገሪቱ ይበጃሉ ብለው ያቀረቧቸው ሃሳቦች ተቀባይነት ሲያገኙ አላየንም፡፡ አሁንም “የህዝብ ድጋፍ አለኝ፤ ችግር ፈጣሪዎቹ ጥቂቶች ናቸው” ወደሚለው የተሰለቸ ፕሮፓጋንዳ ነው የተገባው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ለመለወጥ ዝግጁ እንዳልሆኑና ሥርአቱ ራሱን ለማጥፋት እየጣረ መሆኑን ነው የገመገምኩት፡፡ ባለፈው ዓመት የተከሰተው ህዝባዊ እንቅስቃሴ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች የተመራ ባለመሆኑና የተቀናጀ ስላልነበረ በአፈና ተኮላሽቷል። ከዚህ በኋላ የሚመጣ ካለም፣ በአፈና ሊኮላሽ ይችል ይሆናል፡፡ ግን አፈና በዘላቂነት ሊያዋጣ አይችልም።
ምክንያቱም ለአፈና የሚሰማራው የፀጥታ ኃይል ከህዝብ የወጣ ነው፡፡ በሂደት የህዝቡ የእንቅስቃሴ አካል ሊሆን ይችላል፡፡ ወደዚያ አይነት አቅጣጫ ከተሄደ ደግሞ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ይሆናሉ፡፡ ያኔ የሚያሳዝነው ሥርአቱም አይድንም፡፡ ሀገሪቱም ወደማይጠበቅ ሁኔታ ውስጥ ልትገባ ትችላለች የሚል ስጋት አለኝ፡፡ ይሄ ስጋት ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው የመጣው፡፡
በግልፅ ለመናገር፣ ይህ ሁሉ ችግር ቀላል መፍትሄ ነው ያለው፡፡ አንደኛ፣ ያሉትን የሰብአዊ መብትና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች፣ ያልተመለሱ ከፍተኛ የፖለቲካ ችግሮች አምኖ መቀበል ነው መፍትሄው፡፡ ሥርአቱና ህዝቡ፣ ሆድና ጀርባ እየሆኑ እንደመጡ ማመንም ያስፈልጋል፡፡ ይሄን አምኖ ከተቀበለ በኋላ በሚቀጥለው ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ ፍትሃዊ ምርጫ የሚኖርበትን መደላድል መፍጠር ነው፡፡ ህብረተሰቡ በቀጣይ ምርጫ ላይ እምነት ኖሮት፣ በነፃነት የመምረጥ ዕድል እንዳለው በትክክል ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ የምርጫ መደላድል ውስጥ ሁሉም ተቃዋሚና የሲቪክ ማህበራት እንዲሳተፉ ከተደረገና ሁሉም ከተመቻቸ በኋላ፣ ህብረተሰቡ የፈለገውን እንዲመርጥ እድል ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄ ይሄ ነው፡፡ ህብረተሰቡ በቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ ከወዲሁ እምነት እንዲያድርበት የሚያደርግ ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡
ሁለተኛው፣ የሰብአዊ መብትና የህግ የበላይነት፣ ከፕሮፓጋንዳ ይልቅ በተግባር መሬት መውረድ አለበት፡፡ እነዚህ ከተደረጉ ነው ደርግን ለመጣል መስዋዕትነት ከፍለዋል የሚባሉት ዋጋ የሚያገኙት። አሁን ዋጋ አላገኙም፤ በእነሱ ስም እየተነገደ ነው ያለው፡፡    


-----------------

                            “ጊዜያዊ መድሃኒት በሽታውን ማስታገስ እንጂ መፈወስ አይችልም”
                              አቶ ተሾመ ወ/ሃዋሪያት (የህግ ባለሙያ)

     በሃገሪቱ ተፈጥሮ ለነበረው አለመረጋጋትም ሆነ አሁን ለሚታዩት ውጥረቶች ምክንያቱ፣ የሠብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ በህገ መንግስቱ የተረጋገጡ ቢሆንም በተግባር  መጣሳቸው ነው። ለእነዚያ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች፣ በእርጋታ ጥያቄዎች እየመለሱና እያስተካከሉ መሄድ ቢቻል  ኖሮ፣ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መምጣት ገፊ ምክንያት አይኖርም ነበር፡፡ በመጀመሪያ ደረጃም፣ “ችግሩ የመንግስት አፈፃፀም ስህተት ውጤት ነው” ከተባለ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ስህተት ነበር፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥም ቢሆን መንግስት ሃገሪቱን ለማረጋጋት የሰራው ስራ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ አሁን አዋጁ ከተነሳ በኋላ የምናየው ውጥረትም የተከተለው ከዚህ በመነጨ ነው፡፡ አስቀድሞ ተድበስብሰውና ተሽሞንሙነው  የታለፉ ነገሮች ይበዛሉ፡፡ ከተፈቱ ችግሮች ያልተፈቱት ይበልጣሉ፡፡ ሃገር በህግ መግዛት የሚቻለው፣ የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ጊዜያዊ መድሃኒቶች ብቻ በመሰጠታቸው፣ ዋናውን ችግር ሊፈውሱ አልቻሉም፡፡ ጊዜያዊ መድሃኒት በሽታውን ማስታገስ እንጂ መፈወስ አይችልም። መንግስት ጊዜያዊ መፍትሄ ላይ ማተኮሩ ነው፣ አሁን ለምንገኝበት የውጥረት ስጋት የዳረገን፡፡ ለአለመረጋጋቱ ገፊ ምክንያቶች የነበሩት፣በመንግስት በሚገባ አልተፈተሹም፡፡ መንግስት እነዚህን ለማወቅ ከካድሬዎቹ ጋር ሳይሆን ከጥያቄው ባለቤቶች ጋር መመካከር ነበረበት፡፡  
በፊትም መንግስት የሃሣብ ብዝሃነትን ይፈራል፤ አሁንም በዚህ ፍርሃቱ ነው የቀጠለው። መስማት የሚፈልገውን ብቻ ነው እየሰማ ያለው እንጂ የህዝቡን ብሶት አላወቀም፡፡ የማህበረሰብ መብት ተሟጋቾችን አንድም ቀን ሲያወያይ አልታየም፡፡ ሲቪል ተቋማትንም እንዲሁ ወደ ጎን ገፍቶ፣ የራሱን ሊጎችና ፎረሞች ነው የሚያወያየው። ይሄ አሁንም ዋጋ ሊያስከፍለው ይችላል፡፡ በሌላ በኩል፤ ከግርግሩ ጋር በተገናኘ ዋና ዋና የሚባሉ፣ በህብረተሰቡ ተሰሚነት ያላቸው ፖለቲከኞች እንደታሠሩ ነው ያሉት፡፡ እነዚህን ቢፈታ ምን ይጎዳል? እንደውም ከህዝብ ጋር የበለጠ ሆድና ጀርባ እንዳይሆን ያግዘው ነበር፡፡ የበለጠ የፖለቲካ ስፋት ለመፍጠርም ተቃዋሚዎችን መፍታቱ ይበጃል፡፡ ዞሮ ዞሮ እነዚህ ሠዎች’ኮ መፈታታቸው አይቀርም፡፡ የህግ የበላይነት የመከበሩ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ እነዚህን ሰዎች ቢፈታ ግን ከሚጎዳው ይልቅ የሚጠቀመው ይበልጣል፡፡ ለሃገርም ይጠቅማል፡፡
አሁንም በጊዜ ወደ ዘላቂ መፍትሄዎች ከተሄደ፣ ሃገርን ማረጋጋት የሚቻልባቸው መንገዶች አሉ፡፡ ከነዚህ አንዱ፣ ትልልቅ ሃሣብ የሚያመነጩ የሃገሪቱ የተከበሩ ምሁራን አሉ፤ ከእነሱ ጋር መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ውይይቱ ደግሞ እውነተኛ፣ ግልፅና ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ እዚህም እዚያም ሰዎችን በማሰር ግን የሃገሪቱ ችግር አይፈታም፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ  በፍትህ፣ በሚዲያ፣ በሲቪክ ተቋማት ነፃነት ጉዳይ ላይ መንግስት በርካታ ትችቶች ተሠንዝረውበታል፡፡ አሁንም ግን በእነዚህ ተቋማት ነፃነት ጉዳይ ላይ የማስተካከያ እርምጃ እየወሰደ አይደለም፡፡ ይሄ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላልና ሽንገላው ቀርቶ፣ የምር ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
እንግዲህ በግርግሩ ወቅት መንግስት ብዙ ቃል ገብቷል፡፡ አንዱ፣ ለወጣቶች ተዘዋዋሪ 10 ቢሊዮን ብር ፈንድ ይለቀቃል መባሉ ነው፡፡ አሁን ይህ ጉዳይ ምን ላይ ደርሷል? ከሃገሪቱ ህዝብ 70 በመቶ ወጣት ነው፡፡ ይህ ወጣት ምን ያህል የስራ እድል ተጠቃሚ ሆኗል? የሚሉት ጥያቄዎች ዛሬም እንዳሉ ነው፡፡ እኔ በግሌ የሃገርን ሠላም፣ ልማትና የወደፊት ተስፋ የሚያደናቅፍ ነገር እንዲፈጠር ፈፅሞ አልፈልግም፡፡ ግን ይሄ በምኞት ብቻ አይሆንም፡፡ አሁን የሚታዩት ምልክቶችና ሁኔታዎች በቅርቡ ወደ ነበርንበት እንዳንመለስ ያሰጋኛል፡፡ የድንበር ግጭቶች አሉ፡፡ በኦሮሚያ ክልልና በሶማሌ ክልል ያለው የድንበር ችግር መፍትሄ ተሰጥቶታል ከተባለ በኋላ፣ ግጭቶች መኖራቸውን እየሰማን ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ መፍትሄው እየሠራ አለመሆኑን ነው የሚያሳየው። ለዚህ አሁንም ቢሆን መፍትሄው፣ እንደ ምንም መንግስት ጨክኖ፣ መስማት የማይፈልጋቸውን ድምጾች፣ የሚሰማበትን ህዝባዊ የምክክር መድረክ ማዘጋጀት ነው፡፡ ምክክሮቹ ለሚዲያ ፍጆታና ለይስሙላ መሆን የለባቸውም፡፡ ሁላችንም፣ ይህቺን ሃገርና ህዝቦቿን በቀናነት ከችግር የመታደግ ሃላፊነታችንን መወጣት አለብን፡፡

--------------------------

                            “መንግሥት አሁንም ችግሮችን በጥልቀት መመርመር አለበት”
                                  አቶ ሙሉጌታ አበበ (ፖለቲከኛ)

      መንግሥት ለተፈጠሩት ችግሮች መፍትሄ አድርጎ ካስቀመጣቸው አንዱ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ነበር፡፡ አዋጁ ከመነሳቱ በፊት ግን ህዝብ አድማ ሲመታ ነበር፡፡ ይሄ እንግዲህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጥሎም፣ ችግሮች መቀጠላቸውን  ያሳያል፡፡ ሰሞኑን ኦሮሚያ አካባቢ ውጥረቶች እንዳሉ አረጋግጫለሁ፡፡ እነዚህ ውጥረቶች  ህዝቡ ለጥያቄዎቹ መልስ እንዳላገኘ ማረጋገጫ ናቸው፡፡ በእርግጥም መልስ ያላገኙ ጉዳዮች በርካታ ናቸው። ለግርግሩ ገፊ ምክንያቶች የነበሩ ዋና ዋና ጉዳዮች፣ አሁንም ተገቢ ምላሽ እየተሰጣቸው አይደለም፡፡ ይህ ባለበት ደግሞ የታክስ ውዝግቡ ቀጠለ፡፡ ይሄ እንግዲህ መንግስት ሁነኛ አማካሪዎችና የሃገሪቱንና የህዝቡን ወቅታዊ ሁኔታ የሚገመግሙ ባለሙያዎች እንደሌሉት ነው የሚያመለክተው፡፡
በየቦታው የስራ ማቆም አድማዎች እንዲፈጠሩ ካደረጉት ጉዳዮች አንዱ፣ የግብሩ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ መንግስት በራሱ ፍላጎት ያመጣው ችግር ነው፡፡ እኔ እንደውም፣ መንግስት ጭር ሲል አልወድም በሚሉ ሰዎች የተሞላ ነው የሚመስለኝ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተነሳ በኋላ፣ እየተፈጠረ ያለው ውጥረት፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው ችግር የተለየ አይደለም፡፡
ስለዚህ አሁንም መንግስት ጉዳዩን በጥልቀት መመርመር አለበት፡፡ መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር አሁንም መቀራረብ ይገባዋል፡፡ አመለካከቱንና ፍልስፍናውን መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ህዝቡ ብሶቱ ከፍተኛ መሆኑን መረዳት አለበት፡፡ ችግሩን ለመፍታት፣ውይይት እንጂ ሃይል ቦታ ስለሌለው፣ አሁንም ውይይት መቅደም አለበት፡፡

Read 1741 times