Monday, 28 August 2017 00:00

“መካከለኛ ገቢ ለመድረስ ባለን ራዕይ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንግዲህ ዓመቱ እየተገባደደ ነው፡፡ መሥሪያ ቤቶች ስለ ‘ዕቅዳቸው’ ምናምን ነገር የሚያወሩበት ጊዜ ነው፡፡ “ልንሠራው ካቀድነው ውስጥ በሠራተኛው ከፍተኛ የሥራ መንፈስና ከማኔጅመንቱ ጋር ባለው መልካም ግንኙነት 56% አሳክተናል፡፡” እንዲህ የሚለው ኃላፊ፤ የእንግሊዝ ሱፉን፣ የጣልያን ከረባቱን፣ የስፔይን ጫማውን ግጥም አድርጎ መድረክ ላይ መውጣት ነበረበት? እንደውም ተሸማቆ ጭብጦ ባያክል እንኳን (ከዛ ሰውነት ወደ ጭብጦነት መቀነስ ለጊነስ የሚበቃ ታሪክ ስለሚሆን) አለ አይደል… ፊቱ ላይ ትንሽ እንኳን የሀዘን የሚመስል ነገር ቢያሳይ ምን አለበት!
ለክፉም ለደጉም አንዱ ጋዜጠኛ አንዱን አለቃ ያናግራቸዋል፡፡
“ስለ ድርጅታችሁ እንቅስቃሴ አንዳንድ ነገሮችን ቢነግሩኝ፡፡ ለመሆኑ በበጀት ዓመቱ የድርጅታችሁ እንቅስቃሴ እንዴት ነበር?”
“በእውነቱ ድርጅታችን አገሪቱ በተያያዘችው መካከለኛ ገቢ የመድረስ ራዕይ መሰረት፣ ልማቱን ለማፋጠን በሁሉም መልኩ በቁርጠኝነት እየሠራን ነው”
“ለምሳሌ ድርጀቱ አሳክቷቸዋል የሚሏቸውን ቢነግሩኝ--”
“ባስቀመጥነው እቅድና ስትራቴጂ በመመራት፣ የምርት ሥራውን ከረጅም ጊዜ ራዕይ ጋር በማሳለጥ፣ ምርታችንን ለማሳደግና በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ድርጀቱን ከአፍሪካ ተመራጭ ለማድረግ እየሠራን ነው”
“እና በአጠቃላይ ድርጅቱ በመልካም ጎዳና ላይ ነው እያሉኝ ነው?”
“አዎ፣ በመልካም ሁኔታ እየተንቀሳቀስን ነው”
“እንደው ከእናንተ ተሞክሮ በመነሳት፣ ለሌሎች መሰል ድርጅቶች ምን የሚያስተላላፉት መልእክት አለ?”
“አገሪቱ አሁን በፈጣን የእድገት ጎዳና ላይ ነች። በአጭር ጊዜ ውስጥ ህዝቡ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን መደረግ አለበት፡፡ ሁሉም ባስቀመጥነው ራዕይ በመመራት ጠንከሮ ሊሠራ ይገባል”
“እናመሰግናለን፣ ድርጅታችሁ ወደፊትም ከፍተኛ ስኬቶች እንደሚያስመዘግብ እምነታችን ነው፡፡”
“እኔም አመሰግናለሁ፡፡”
እናላችሁ… የዚሀ አገር ጥያቄና መልስ፣ የዚህ አገር ‘መልካም ገጽታ ግንባታ’ እንዲህ፣ እንዲህ እያለ ይሄዳል፡፡ ቢሆንም ባይሆንም ግን ከአለቅየው ብንሰማ የምንፈልገውን ለማግኘት፣ ‘በጥያቄ ማፋጠጡ’ ትንሽ ለየት ቢል እንመርጥ ነበር፡፡
“ስለ ድርጅታችሁ እንቅስቃሴ አንዳንድ ነገር ቢነግሩኝ፡፡ ለመሆኑ በበጀት ዓመቱ የድርጅታችሁ እንቅስቃሴ እንዴት ነበር?”
“በእውነቱ ድርጅታችን አገሪቱ በተያያዘችው መካከለኛ ገቢ የመድረስ ራዕይ መሰረት፣ ልማቱን ለማፋጠን በሁሉ መልኩ በቁርጠኝነት እየሠራን ነው፡፡”
“በእውነቱ በጣም ያስደስታል…ግን ድርጅታችሁ በርካታ ስሞታዎች እየተሰሙበት ነው--”
“ምን አይነት ስሞታ?”
“ማለት ከፍተኛ የሆነ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉበት እየተባለ ነው--”
“ይሄ እንኳን ስለ ድርጀቱ አሠራር ግንዛቤ የሌላቸው ሰዎች የሚያስወሩት አሉባልታ ነው፡፡”
“ስሞታው እኮ ከውጪ ሳይሆን ከድርጅቱ ሠራተኞች የሰማነው ነው፡፡ ሠራተኞቹ የሚነግሩን፣ በማኔጅመንቱ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ችግር እንዳለ ነው…”
“ችግርማ የትም ይኖራል፡፡ ለምሳሌ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል እጥረት አለብን…”
“ሠራተኞች የተለያዩ ችግሮች እንዳሉ ነው የሚናገሩት፡፡ በመሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ብክነት አለ ነው የሚባለው--”
“ይሄ እንኳን አሉባልታ ነው፡፡ ማንኛውም አይነት ወጪ የሚወጣው ታምኖበትና ማኔጅመንቱ ሲፈቅድ ነው…”
“ከማኔጅመንቱ እውቅና ውጪ እርስዎ በግልዎ ውሳኔ አያስተላልፉም?”
“በተሰጠኝ ኃላፊነት መሰረት ውሳኔዎች አሳልፋለሁ፡፡ ሆኖም ግን ገንዘብን በተመለከተ የፋይናንስ ዲፓርትመንቱ ሳያምንበት የሚደረግ ምንም ነገር የለም፡፡”
“ለምሳሌ ከደረሱን ጥቆማዎች፣ የእርስዎ ጠረዼዛ ከተለወጠ ገና ዓመት እንኳን አልሞላውም…አሁን አዲስ መግዛቱ አስፈላጊ ነው!”
“አዎ፣ አስፈላጊ ነው፡፡”
“የቀድሞው ጠረዼዛዎ እኮ ከዱባይ ድረስ ነው ተጭኖ የመጣው፡፡ አሁን ደግሞ የሰማነው ከሚላኖ እንደመጣ…”
“ከሚላኖ አይደለም…ከታይላንድ ነው፡፡”
“እሱም ቢሆን ለምን አስፈለገ? ደግሞስ ይህን ያህል አጣዳፊ እንኳን ቢሆን ብዙ የአገር ውስጥ አምራቾች እያሉ፣ ያን ያህል ወጪ አውጥቶ ከውጪ ማስመጣቱ ለምን አስፈለገ ?”
“እንግዲህ እያንዳንዱን ሰባራና ሰንጥር ስንገዛ፣ ምክንያት መስጠት ያለብን አይመስለኝም…”
“እሺ፣ ሌላ የሰማነው ደግሞ ከፋብሪካ ከተገዛ ሁለት ዓመት ያልሞላው መኪና ጋራዥ ቆሞ፣ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ መኪና ተገዝቶልዎታል ይባላል…”
“የተገዛው ለእኔ ሳይሆን ለድርጅቱ ነው፡፡”
“ቢሆንም የተገዛው በእርስዎ ትእዛዝ ነው ተብሏል፡፡ መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ የበጀት እጥረት አለበት እየተባለ ይህን ያሀል ገንዘብ ለመኪና…”
“እና በእግርህ ተመላለስ ነው የምትለኝ!!…”
“ሳይሆን የነበረው መኪና ጥሩ ሁኔታ ላይ እያለ…”
“ወንድሜ፤ ይሄ ሁሉ የእኛን መልካም ሥራ ማጣጣል የሚፈልጉ ሰዎች የሚያስወሩት ነው፡፡ ከህግ ውጪ ያደረግነው ምንም ነገር የለም፡፡”
“እሺ… ባለፈው ወር አካሂዳችሁት የነበረው ስብሰባስ…”
“ደግሞ ስብሰባው ምን ሆነ፣ ህገ ወጥ ስብሰባ ነው አሉ እንዴ!”
“እንደ እሱ አላሉም፡፡ ግን ለሁለት ቀን ስብሰባ ማጠቃለያ፣ ለእራት ግብዣ ከሁለት መቶ ሀምሳ ሺህ ብር በላይ ወጥቷል ይባላል…”
“ምን አዲስ ነገር አለው… ሁሉም  የሚያደርገው አይደለም እንዴ!”
“እናንተ እኮ በጀት ስላነሰን እንደገና ይታይልን ብላችሁ ለበላይ አካል ማመልከቻ አስገብታችኋል ይባላል፡፡”
“አዎ፣ በጀት በጣም ነው ያጠረን…”
“በጀት ያጠረው መሥሪያ ቤት እንዴት ነው ለውስኪና ለ…”
“ስማ! ነገሩን እያራገባችሁ ከህዝቡና ከበላይ አካል ጋር እንድንጣላ የምታደርጉት እናንተ ጋዜጠኞች ናችሁ፡፡ ምነው፣ በየጠጅ ቤቱና በየአረቄ ቤቱ እየዞራችሀ በዱቤ እንደምትጠጡ አናውቅምና ነው…”
“ግን እኮ እኛ በሰነድ አናወራርድም፣ ከኪሳችን ነው…”
“ወንድም አሁን ሥራ ስላለብኝ ይበቃል፡፡”
ዘግይቶ የደረሰን እንደሚባለው አይነት… ወጪ በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀነስ መመሪያ ከተላለፈ በኋላ፣ ያው ጋዜጠኛ እኚህኑ ባለስልጣን ያገኛቸዋል፡፡
“ሰሞኑን የወጣው መመሪያ መቼም ደርሷችኋል…”
“የምን መመሪያ?”
“የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወጪን እንዲቀንሱ የተላለፈው መመሪያ፡፡”
“እርሱማ እኛም ስንጮህለት የኖርነው ነው…”
“አልገባኝም…”
“በየመሥሪያ ቤቱ የገንዘብ ብክነት ስላለ፣ አንድ ወሳኝ እርምጃ መወሰድ አለበት ብለን እኮ እኛም ስንታገልለት የኖርነው ነው…”
“ይሄን ነገር ስብሰባ ላይ አንስታችሁታል? ወይም በጽሁፍ አቅርባችሁት ታውቃላችሁ?…”
“በራሳችን ማኔጅመንት ስብሰባ ላይ ሁልጊዜ የምናነሳው ነው፡፡”
“ግን እኮ ከዚህ በፊት እንዳወራነው፣ በገንዘብ ብክነት የእናንተም መሥሪያ ቤት ይታማል፡፡ በዛ ሰሞን ሳናግርዎ ስለ ጠረዼዛው፣ ስለ መኪናው...”
“አሁን እኮ ስላለፈ ነገር አይደለም የምናወራው። አሁን ማውራት ያለብን ስለ ወደፊቱ ነው…”
“እኮ በዚህ ላይ እናንተም ጥፋት እንደነበረባችሁ አምናችሁ…!”
“ስማ፣ እኛ በእንደዚሀ አይነት የጠላት ፕሮፓጋንዳ ተዘናግተን ወይም ፈርተን መካከለኛ ገቢ ደረጃ የመድረስ ራዕያችን እንደማይጨናገፍ ገንዘብ እየሰጡ ለሚያሰማሯችሁ ንገራቸው፡፡”
እንዲህ ብለው፣ ምናምን ሌብል ‘ሲፓቸውን’ ሊጠምዱት ሄዱ — በሰነድ የማይወራረድ ወጪ! “ወይ ነዶ!” ማለት ይሄኔ ነው፡፡
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 3004 times