Print this page
Saturday, 26 August 2017 12:52

የሰሞኑ አጀንዳ - ዝክረ መለስ

Written by 
Rate this item
(20 votes)

      “---አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ወዲህ፣ ኢህአዴግ አዲስ፣ መሬት የረገጠ ፖሊሲም ሆነ አስተሳሰብ ሲያፈልቅ አላየንም፡፡ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የፖሊሲ ገጽታ፣ “አብዮታዊ ዲሞክራሲን” ምርኩዝ አድርጎ እየተጓዘ ነው፡፡ ግብርና መርም ሆነ በኢንዱስትሪ ላይ ትኩረት የሚያደርገው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ሰነድ፣ በእርሳቸው ዘመን የተከተበ ነው፡፡---”
                      ከተመስገን ጌታሁን ከበደ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

       ሰሞኑን የኢህአዴግ መሪና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት የአቶ መለስ ዜናዊ አምስተኛ ሙት ዓመት ሲዘከር ሰንብቷል፡፡ የፓርቲው አመራሮችና  የትግል አጋሮች፣የአቶ መለስን ሁለንተናዊ ሰብእና የሚገልጹ ምስክርነቶችን በመንግስት መገናኛ ብዙኃን ሲሰጡ አድምጠናቸዋል፡፡ በኢህአዴግ ጥላ ስር የተደራጁ የአዲስ አበባ ወጣቶችም፤ በተለያዩ ሥነ ስርአቶች ጠ/ሚኒስትሩን በየአዳራሹ ዘክረዋል፡፡ የሁሉም  ሀሳብ የሚያጠነጥነውና የሚያሳርገው ታዲያ  የመለስ ሌጋሲን ማስቀጠል በሚለው ላይ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የአቶ መለስ ዜናዊ፣ ዜና እረፍት ሲነገር፣ እውነታውን  ለመቀበል የተቸገረ አንድ የኢህአዴግ አባል አጋጥሞኝ ነበር፡፡ ይህ አባል ሞታቸውን መቀበል ከመቸገሩ የተነሳ፣ አንድ ቀን ድንገት ብቅ ብለው ሕዝቡን እንደሚያስደምሙት እስከማመን ደርሶ ነበር፡፡ አይፈረድበትም፤የመውደዱና የአክብሮቱ ጥልቀት ይመስለኛል፣ ይህን ዓይነቱን እምነት የፈጠረበት፡፡ ስለ አቶ መለስ ዜናዊ አንባቢነት፤አርቆ አስተዋይነትና እንከን የለሽ  ሰብእና በቅርብ የሚያውቋቸው የትግል ጓዶቻቸው በሚገባ ነግረውናልና፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የምለው የለኝም፡፡
ከጠ/ሚኒስትሩ ህልፈት በኋላ ስለ ፓርላማው ውሎ ዜና ሲዘገብ፣ በፓርላማው አዳራሽ መግቢያና መውጫ በር፣ በውስጥ በኩል የተሰቀለውን ግርማ ሞገስ ያለው፣ የአቶ መለስ ዜናዊ ሙሉ ፎቶግራፍ በቴሌቪዥን በመደጋገም እመለከት ነበር፡፡ የፓርላማው ውሎ የዜና ሽፋን ሲሰጠው፣ ምስሉ በቴሌቪዥን ካሜራ ያለ ጭቅጭቅ ሰተት ብሎ ነበር የሚገባው፡፡ የፎቶው ጥራት፣ በአካለ ሥጋ - በሕይወት ያሉ ነው የሚመስለው፡፡ አንዳንድ ጊዜ  ተሰብሳቢው መሀል፣ በሀሳቤ ራሴን አገኘውና፣ ፎቶውን ሰርቅ እያደረግሁ እመለከታለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በበሩ መግቢያ ላይ ቆሜ አዳራሹ ውስጥ ያለውን የስብሰባ ታዳሚ እመለከትና፣ ስሜታቸውን ለማጤን እሞክራለሁ፡፡ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያላቸውን እውነተኛ ስሜት፣እንደ ኤክስሬይ ሰርስሬ መመልከት ብችል ብዬ እመኛለሁ፡፡ ስንቶቻቸው ከልባቸው ያከብሯቸዋል፤ ስንቶቻቸው ግድ አይሰጣቸውም፤ ስንቶቻቸውስ ይፈሯቸዋል፡፡ እርግጥ ነው መፈራት መጠላት ማለት አይደለም፡፡ የፓርላማ አባላቱ፣ አፈ-ጉባኤው ሳይቀሩ፣ የአቶ መለስ ዜናዊን ፎቶግራፍ ሲያዩ፣ አእምሮአቸው ውስጥ ምን እንደሚመላለስ ባውቅ እያልኩ እመኛለሁ፡፡  
አቶ መለስ ዜናዊ በፓርላማው ተገኝተው የሚያቀርቡት ማብራሪያ ሁለት ገጽታዎች ነበሩት፡፡ አንዱ ተቃዋሚዎች ከሚያቀርቡት ጥያቄ ተነስተው በሚሰጡት ምላሽ፣ አብዛኛውን የኢህአዴግ ተመራጭ  የምክር ቤት አባላት፣ በሳቅ ሲያጥለቀልቁ፣ ተቃዋሚዎች ደግሞ በሃፍረት ይኮስሳሉ፡፡ ምንም ጥያቄ ቢነሳ ጠ/ሚኒስትሩ መልስ ቸግሯቸው አያውቅም፡፡ መልሱ ግን ሁሌም ትክክል ነው ማለት አይደለም፡፡ ለጊዜው ግን ትክክል የሚመስሉት እሳቸው ነበሩ፡፡ የሚያበሳጫቸው ሀሳብ ሲያጋጥማቸውም ብስጭታቸውን መደበቅ አይችሉበትም፡፡ ሂሳቸው ከሰይፍ የሚሰላበትም ጊዜ ነበር፡፡ በተቃዋሚዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በኢህአዴግ አባላትም ላይ የሚሰነዝሩት ሀሳብ አባላቱን የሚያስበረግግ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ በፓርላማ፣ “የመንግስት ሌቦች” ያሏቸውን ወገኖች ያሸማቀቁበት አጋጣሚ በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡
ኢህአዴግ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ገብቶ፣ የሽግግር መንግሥት ከመሰረተበት ዕለት ጀምሮ ለተከታታይ አምስት አመታት የተካሄደውን የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በጥልቀት የዳሰሰ ጥናት የማንበብ ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ አጥኚዎቹ፤ ዘጠኝ ወራት ሙሉ በሽግግር መንግስቱ ወቅት ከመጀመሪያዋ ስብሰባ አንስቶ በመገኘት፣ በጉባኤው የተለያዩ ፖሊሲዎች ሲወጡና ሲጸድቁ ተከታትለዋል፤ ሰነዶችንም ፈትሸዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ለማጽደቅ የተካሄደውን ውይይት፣ በየትኛው አንቀጽ ላይ ብዙ ሰዓት የፈጀ ክርክር እንደተካሄደ፣ ባጠቃላይ ሕገ መንግሥቱን ለማጽደቅ የፈጀውን ጊዜ በቀናትና በሰዓት እየለኩ፣ የፓርላማውን አካሄድ ዝርዝር ጉዳይ በስፋት መርምረዋል፡፡ ሕገ መንግስቱን ለማጽደቅ 12  ቀናት መፍጀቱን የጠቀሱ ይመስለኛል፡፡ ጊዜ ሳይፈጁ የጸደቁ ሕጎችንም ከነምክንያታቸው አብራርተው ጽፈዋል፡፡ በዚህ ጥናት በደቡብ አፍሪካና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ አንቱ የተባሉ ምሁራን የተሳተፉበት ሲሆን  በጣም በጥልቀት የተካሄደ ጥናት ነበር፡፡   
የጥናታቸው ትኩረት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ (Contemporary Ethiopian politics) ላይ ነበርና፣ ፖሊሲ የሚያመነጨውንና የፖሊሲ ረቂቅ ጽሑፍ የሚያዘጋጀውን የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ለማወቅም ጥረት አድርገዋል፡፡ ፖሊሲ የሚያመነጩትን ሰዎች ሚና ለመፈተሽም ሞክረዋል፡፡ የእኒህ ተመራማሪዎች ትልቁ ፈተና፣ የፖሊሲ ረቂቁን ያዘጋጀውን ሰው ማንነት ለማወቅ የሚያቀርቡት ጥያቄ መልስ አለማግኘቱ ነበር፡፡ በወቅቱ በድርጅቱ ውስጥ ሰፍኖ በነበረው አሰራር፣ ሁሉም ፖሊሲዎች የሁሉም አባላት አስተዋጽኦ ያለበት መሆኑ የተነገራቸው ሲሆን  ኢህአዴግ በግለሰቦች ትከሻ ላይ ያልተንጠለጠለ እንደሆነ ለማሳየት የተደረገ ሙከራ መሆኑን ተመራማሪዎቹ የተገነዘቡ ይመስለኛል፡፡ የግለሰቦች ማንነት ላይ ማተኮር፣ የግለሰብ አምባገነንነትን ይፈጥራል ብሎ ኢህአዴግ ያምን  ነበር፡፡ ነገር ግን  የፖሊሲ መነሻ ሀሳቡ ከአንድ ግለሰብ መፍለቁ የግድ ነው፡፡
ፖሊሲ የሚያመነጨውን የኢህአዴግ ራስ ለማወቅ ያደረጉት ጥረት ይሳካላቸው አይሳካላቸው ባላስታውስም፣ ከአቶ መለስ ዜናዊ ሌላ  የፖሊሲ ሀሳብ ያመነጩ የኢህአዴግ ሰዎች ቁጥራቸው ከሁለት አይዘልም፡፡ ከአቶ መለስ ዜናዊ ሌላ የፖሊሲ ረቂቅ ካቀረቡት መካከል አቶ በረከት ስምዖን እንደሚገኙበት  ሰምቼአለሁ፡፡ ሌሎች ጓደኞቻቸው፣ በአቶ መለስ ዜናዊ ተነድፎ የተሰጣቸውን ፖሊሲዎች አንብበው፣ ውይይቱን ከሟሟቅ የዘለለ ሚና እንደሌላቸው በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ተገንዝቤአለሁ፡፡
ሰሞኑን የአቶ መለስ ዜናዊ አምስተኛ ሙት ዓመታቸው ሲዘከር፣ የተሰጠው ምስክርነት ይህንኑ ያረጋግጣል። ስለዚህ ኢትዮጵያ የምትገዛበት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍና ዋና አመንጭ፣ አቶ መለስ ዜናዊ መሆናቸውን መገመት ይቻላል፡፡ በሙስና ወንጀል ተከሰው ለዓመታት ወህኒ ወርደው የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ፣ ከኢህአዴግ የታሪክ መዝገብ ላይ የተፋቁ ቢሆኑም፣ በዚያን ወቅት በርከት ያሉ የፖሊሲ ሰነድ በማዘጋጀት፣ ሌላው የተዋጣላቸው የኢህአዴግ ቁንጮ ባለስልጣን እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ይሁንና የአቶ መለስን  ያህል የጎላ ሚና የነበረው የኢህአዴግ መሪ ማግኘት ይከብዳል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ወዲህ፣ ኢህአዴግ አዲስ፣ መሬት የረገጠ ፖሊሲም ሆነ አስተሳሰብ ሲያፈልቅ አላየንም፡፡ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የፖሊሲ ገጽታ፣ “አብዮታዊ ዲሞክራሲን” ምርኩዝ አድርጎ እየተጓዘ ነው፡፡ ግብርና መርም ሆነ በኢንዱስትሪ ላይ ትኩረት የሚያደርገው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ሰነድ፣ በእርሳቸው ዘመን የተከተበ ነው፡፡
በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭት ሳቢያ፣“ጦርነት ይካሄድ አይካሄድ” የሚለው ክርክር፣ ለህውኃት መሰንጠቅ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል፡፡ አቶ ስዬ አብርሀ በጻፉት መጽሐፍ፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤ ባይሳካላቸውም፣ ጦርነት መካሄድ የለበትም ከሚሉት ወገኖች እንደነበሩ ተገልጿል፡፡ እንደ አቶ ስዬ አባባል ከሆነ፣ አቶ መለስ ዜናዊ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የኢትዮጵያ ነገሥታት የጦረኝነት አባዜ፣ በአስተሳሰብ ደረጃ አሸንፈው ነበር ማለት ነው፡፡
የአቶ መለስ ዜናዊ አስተሳሰብ ጎዳም ጠቀመም፣ የ14 ዓመቱ የጫካው ዘመን ሲቆጠር፣ ላለፉት 42 ዓመታት ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታዋ የተወሰነው በእሳቸው አስተሳሰብ መሆኑ የሚካድ አይደለም። ይህ አስተሳሰብ በሥራ ዘመናቸው የተፈጠረውን ስህተትና ጥፋት አያካትትም፡፡ ምናልባት በባህላችን ሙት ወቃሽ መሆን ነውር በመሆኑ ይመስለኛል፣ በጣም የጎሉ ስህተቶች እንኳ አልተጠቀሱም። በሌላ በኩል፤ ስለ አቶ መለስ ዜናው ሰብእና እንደዚህ ጎልቶ ከተነገረ፣ የአሁኖቹ የኢህአዴግ መሪዎች፣ ሩጫቸውን ጨርሰዋል ብለን ለማሰብ ያስገድደናል፡፡ በአንድ በኩል፤ በአገራችንም ሆነ በዓለም የማያቋርጥ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ክስተት ነው የሚታየው፡፡ በሌላ በኩል፤ የአቶ መለስ ዜናዊን ሀሳብ ዘላለማዊ አድርጎ የማሰብ አዝማሚያ በስፋት ተንሰራፍቷል፡፡ የአማራ ክልል ማናጅመንት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር በጨረፍታ በቴሌቪዥን ላይ ሲናገሩ እንደሰማሁት፤ አቶ መለስ ዜናዊን የወደፊቱን የሚያውቁ ነቢይ ያህል ነበር ሰብእናቸውን አግዝፈው ሲናገሩ የሰማሁት፡፡ ዓለም በፍጥነት በምትለዋወጥበት በዚህ ዘመን እንደዚህ አይነቱ  አስተሳሰብ የሚያዋጣ ነው ወይ የሚለው ያከራክራል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ፣
 አንድ ሀሳብ ይዞ መቆምን ፈጽሞ የሚደግፉት አይመስለኝም፡፡ አሁን ያሉት የኢህአዴግ መሪዎች አዳዲስ ሀሳቦችን እንዳያፈልቁ የሚያሰንፍ ወይም የሚገታ አስተሳሰብ እንዳይሆንም ስጋት አለኝ። የአቶ መለስ ዜናዊን ሌጋሲ ለማስቀጠልም እኮ ከጊዜው ጋር መጓዝ የግድ ይላል፡፡  

Read 7712 times
Administrator

Latest from Administrator