Saturday, 26 August 2017 12:28

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን ወርቁ
Rate this item
(2 votes)

  ሰውየው የወደፊት ዕጣ ፈንታውን (fate) ለመጠየቅ ወደ እግዜር ዘንድ አቀና፡፡ እግዜርም ወደ ራሱ ጉዳይ በሰውየው አቅጣጫ ሲመጣ፣ መንገድ ላይ ተገናኙ፡፡
“ጤና ይስጥልኝ ጌታዬ ወዳንተ እየመጣሁ ነበር” አለ ሰውየው፡፡
እግዜርም፤ “ምነው ደህና?” ሲል ጠየቀው፡፡
“ወደፊት ምን እንደሚገጥመኝ ልጠይቅህ ነው”
“ይህማ የሚነገር ጉዳይ አይደለም፡፡” አለና፤ “የሚሆን ይሆናል፣ የማይሆን ደግሞ አይሆንም። … ሰው በራሱ ልቦና ይመራ ዘንድ ማሰቢያ ተሰጥቶታል” አለው እግዜር፡፡
“እባክህ ጌታዬ አታሳፍረኝ” በማለት ለመነ ሰውየው፡፡
እግዜርም፤ “እሽ እንግዲህ ‹ነገህ‹ ምን እንደሚመስል ልንገርህና ልሂድ” አለውና “የህይወት መዝገቡን” አውጥቶ፤ “ነገ ችግር ይገጥምሃል ግን ታልፈዋለህ” ብሎት መሄድ ሲጀምር፣ ‹ችግር› የሚለው ቃል ያስደነገጠው ሰውዬ… “እሽ ከዛስ፣ ተነገ ወዲያስ? እሱን ብቻ ንገረኝ እባክህ” እያለ አስቸገረው፡፡ እግዜርም መዝገቡን አይቶ፤“ተነገ ወዲያ ወርቅ የተሞላ ሳጥን ታገኛለህ” አለውና መንገዱን ቀጠለ፡፡ ሰውየው በሰማው ነገር እየፈነደቀ “ግን … ግን ጌታዬ …ግን” እያለ ተከተለው፡፡
እግዜርም ቆም አለና
“ግን ምን?” ሲል ጠየቀው፡፡
“አንድ የመጨረሻ ነገር ላስቸግርህ” በማለት ሰውዬው ድርቅ አለ፡፡
“ምንድን ነው?” ሲለው፤ “‹ነገን› አዘልለኝ፣ ‹ነገ› ይለፈኝ” አለ ሰውየው፡፡
እግዜርም፡፡… “ይሁንልህ” ብሎት መንገዱን ቀጠለ፡፡
ሰውየው በደስታ ሰክሮ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ስለ ወደፊቱ ኑሮው ሲያሰላስል አምሽቶ … ሌሊቱ ሲጋመስ ድብን ያለ እንቅልፍ ወሰደው፡፡ በሶስተኛው ቀን ከእንቅልፉ ነቃ፡፡ ዓይኑን ማመን አልቻለም፡፡ “ታምሜ ነበር? … እየቃዠሁ ይሆን‘ዴ?” ብሎ ራሱን ጠረጠረ፡፡
ቀዬው እንዳለ ወድሟል፡፡ ከራሱ በቀር አንድም ፍጡር ባካባቢው አልነበረም፡፡ ምን እንደተፈጠረ ሊገባው አልቻለም፡፡ … ግራ ተጋባ፡፡
እህል ከቀመሰ ሶስተኛ ቀኑ ነው፡፡ ረሃብ ሞረሞረው፡፡ እንደምንም አቅሙን አሟጦ ብድግ አለ፡፡ እግሮቹን እየጎተተ፣ ‘ሚበላ ነገር ሲፈልግ ጎርፍ ያመጣው ‘የሚመስል ሳጥን አገኘ፡፡ ሲከፍተው በወርቅ በገንዘብ፣ ዋንጫዎች፣ ቢላዋ፣ ማንኪያና በመሳሰሉት ተሞልቷል፤ … በጣም ደነገጠ። ወዲያውም ከ‘ግዜር ጋር ተገናኝቶ እንደነበር አስታወሰ፡፡
‹ትናንት›ን አልኖረም፤ ‹ትናንትን› ዘልሎታል። ባልኖረው ‹ትናንት› ውስጥ የተፈጥሮ አደጋ (disaster) በመድረሱ የነበረው እንዳልነበረ ሆኗል፡፡ ሳጥኑ ጎን ቁጭ ብሎ ማልቀስ ጀመረ፡፡
… መሸና ነጋ፡፡ ረሃቡ ፀናበት፣ እሚላስ፣ እሚቀመስ አላገኘም፡፡ ከሳጥኑ ውስጥ ቢላዋ አወጣና፣ አንድ እግሩን ቆርጦ መብላት ጀመረ፡፡ … ራሱን እየበላ… እየበላ…ሞተ፡፡
ወዳጄ፤ የሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ የሚያልፍባቸው የመከራና የደስታ ወቅቶች፣ በራሱ ፍቃድና ነፃ ምርጫ የተሰሩ ናቸው? ወይስ ከሱ ቁጥጥር ውጭ በሆኑ ሁኔታዎችና ተያያዥነት ባላቸው አጋጣሚዎች ሰበብ ወይም ምክንያት የተፈጠሩ ይመስልሃል?
በህይወት ጉዞህ ላይ ልክና ልክ ያልሆነን ነገር በሂሳብ ስሌት ማረጋገጥ አይቻልም (There is no mathematical certainty in life ይሉሃል ዲተርምኒስቶች!!)
ዲተርምኒዝም (Determinism) የሚባለው ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ … “ማንኛውም የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት ሆን ብሎና አስቦበት በዝግጅትና በዕቅድ የሚፈፅመው እንኳ ቢሆን በሰውየው ፍላጎትና ምርጫ የሚወሰን አይደለም፡፡ ከሱ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ የሌሎች ሁኔታዎች ግፊት ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ሰው በራሱ ወይም በሌላው ሰው ላይ በሚያደርሰው ጥቅም ወይም ጉዳት መጠየቅ የለበትም፡፡ … መጀመሪያውኑ የተወሰነ ጉዳይ ነውና (…human actions are determined before hand, or not free, and every event in the universe has it’s own explanatory cause) ይለናል፡፡
አንዳንድ እምነቶችም የሰው ልጅ ከልደቱ እስከ ሞቱ በሚያደርገው ጉዞ ወይም ውጣ ውረድ ሳይቀነስ፤ ሳይጨመር እንዳለ በ‹በህይወት መዝገብ› ላይ የሰፈረ ነው ስለሚሉ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከዲተርምኒስቶች ጋር ይዛመዳሉ፡፡… “ያለ እግዚአብሔር ወይም ያለ አላህ ፍቃድ የሚሆን አንድም ነገር የለም” እንደሚባል፡፡
በክርስትና ዕምነት የሰው ልጅ ከሃጢአቱ ይፀዳ ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ህይወቱን ሰጥቷል። ይህም ይፈፀም ዘንድ የየሁዳ ሚና ዋነኛው ነበር። ይሁዳ ጌታውን አሳልፎ ባይሰጥ ኖሮ፣ የዕምነቱ አቅጣጫ ሊቀየር ወይ ጨርሶ ላይኖር ይችላል። ጥያቄው ይሁዳ ጥፋተኛ ነው? ጥፋተኛ አይደለም? ቢሆን ዲተርምኒዝም፤ “አይደለም” ነው መልሱ፡፡ ምክንያቱም ቀደም ብሎ የተወሰነ (predetermined) ጉዳይ በመሆኑ… ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ ግድ ነው፡፡
ዲተርምኒስቶቹ በአንድ በኩል ደግሞ የአንድን ነገር (የሰው ፀባይን ጨምሮ) ተፈጥሯዊና ነባራዊ ባህርያትን በጥልቀት በማጥናት፣ የወደፊቱን ሁኔታ መተንበይም ይቻላል ብለው ያምናሉ፡፡ በቂ ውሃና በቂ ሙቀት ካለ፣ በሂደት ዝናብ እየተሰራ ነው እንደማለት፡፡
ፈረንሳዊው ኒውተኒያን ፊሎዘፈር ፔሬ ስምዖን ዴ ፕላሴ፤ “በህዋው ውስጥ ያሉትን የእያንዳንዱን ሰብ አቶሚክ ፓርቲክል አቅጣጫና እንቅስቃሴ ካወቅሁ፣ በማንኛውም ጊዜ ዩኒቨርስ ውስጥ የሚፈጠረውን ነገር አስቀድሜ ማወቅ እችላለሁ” ብሎ ነበር፡፡ ቆይቶ ግን የፊዚክስ ዕውቀት እያደገ ሲመጣ፣ አንዱ ዋነኛ ግኝት የአንድን ሰብ አቶሚክ ፓርቲክል አቅጣጫ ወይም እንቅስቃሴ በተመሳሳይ ጊዜ በፍፁም ማወቅ እንደማይቻል ያረጋገጠ ሆኗል።
ዲተርምኒዝምን የሚቃወመው አስተሳሰብ ደግሞ ኢንዲተርምኒዝም (indeterminism) የምንለው ሲሆን የፍልስፍናው መሠረት ባጭሩ፤ “ሰው ለሚያደርገው ነገር (ለሚሰራው ሥራ) ምክንያት ሳያስፈልግ ቀጥታ ተጠያቂ መሆን አለበት” የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ሰርቆ “ስለራበኝ ነው” ቢል ወይም ወንጀል ፈፅሞ የተገፋፋበትን ምክንያት ቢደረድር ወይ “ሰይጣን አሳሳተኝ” ቢል ተቀባይነት አይኖረውም እንደማለት ይሆናል። የፊዚክስ ፈላስፋው ሰር አርተር ኤዲንግተን፤ የዚህን አስተሳሰብ ሳይንሳዊ ጎን (physical side) በሚገባ ያብራራው ሲሆን አንዳንድ ሊቃውንት ደግሞ ኤግዚስተንሺያሊዝምን (existentialism) የኢንዲተርምኒዝም ሌላኛው ገፅ ነው ይላሉ፡፡
ሶስተኛው አስተሳሰብ ኮምፓቲቢሊዝም (compatibilism) ወይም ሶፍት ዲተርምኒዝም ይሰኛል፡፡ ይህ አመለካከት ከሞላ ጎደል ሁለቱን አስተሳሰቦች በማቀራረብ ‹ዲተርሚኒዝም ትክክል ነው፤ ሆኖም ግን የሰው ልጅ ለድርጊቱ ተጠያቂ መሆኑ ተገቢ ነው፡፡› በማለት ያስገነዝባል፡፡
እንግዲህ ወዳጄ፤ ወደ ተረታችን እንመለስና፣ ሰውየው ለደረሰበት ገጠመኝ ከላይ ባየናቸው ፍልስፍናዊ አቀራረቦች አንፃር ሃላፊነቱን ለማን እናሸክም?... ለራሱ ለሰውየው?፣ ለእግዜር? ለተፈጥሮ? ለባለተረቱ? ወይስ “የሚሆን ሆነ!” ብለን እንደምድም? ወይስ …??
ሠላም!!

Read 5041 times