Saturday, 26 August 2017 12:15

“ዓሥራ ሥድሥት” ዛሬ ይመረቃል፤

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   ”የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ለንባብ በቃ
                 • “ከንዱራ” ሰሞኑን በገበያ ላይ ዋለ

       በደራሲ ደመወዝ ጎሽሜ የተዘጋጀው “ዓሥራ ሥድሥት” የተሰኘ መጽሐፍ፣ በዛሬው ዕለት ከቀኑ 8፡30 ጀምሮ፣ አምስት ኪሎ በሚገኘው በብሔራዊ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን  አዳራሽ ይመረቃል፡፡ ኢጋ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ መጽሐፉ ሃይማኖታዊ ፍልስፍናዎችን የያዘ ሲሆን  የሥነመለኮት ባለሙያ ዶ/ር ዘሪሁን ሙላትና የጥበብ ታሪክ መምህርና ተመራማሪው አቶ አበባው አያሌው፣ በመጽሐፉ ውስጥ በቀረቡት ሃሳቦች ላይ የመወያያ ነጥብ ያነሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የመጽሐፉን ሃሳብ የሚያንጸባርቅ ዶክመንታሪ ፊልም ለዕይታ የሚቀርብ ሲሆን ለተወሰኑ ታዳሚዎችም በዲቪዲ በስጦታ ይበረከታል ተብሏል፡፡
አቤል ጋሼ የተባለ ደራሲ በመጽሐፉ ጀርባ ላይ ባሰፈረው ዘለግ ያለ አስተያየት፤ “-- በእውነት ጥበብን የፈለገ ከዚህ ከደመወዜ ታዛ ይጠለላል! ያጠይቅ! ከአዋቂ ይማር! ይህ ጽሁፍ ፍልስፍና ነው፤ ይህ ጽሁፍ ቀመር ነው፤ ይህ ጽሁፍ ሃይማኖት ነው፤ ይህ ጽሁፍ ስለ ሃይማኖት፣ ስለ ፖለቲካ፣ ስለ ታሪክ ነው፤ በተለይም ይኸ መጽሐፍ እውነትን የመፈለግ አንደምታ ነው--” ብሏል፡፡
 በ441 ገጾች ዳጎስ ብሎ የተሰናዳው “ዓሥራ ሥድሥት”፤ በ101 ብር ከ50 ሳንቲም እየተሸጠ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ ደራሲው ደመወዝ ጎሽሜ፣ ከዚህ ቀደም “ሶስተኛው ኪዳን” የሚል መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር በሆነው ብሩህ ዓለምነህ የተዘጋጀው፣ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የተሰኘ መጽሐፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል። የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት ሐተታዎችን  ከእነ ትንታኔያቸው ያካተተው መጽሐፉ፤ ታሪክ፣ ሃይማኖትና ፍልስፍና የተዋሃዱበት ነው ተብሏል፡፡
ደራሲው ይሄን መጽሐፍ የማዘጋጀት ሃሳቡ እንዴት እንደተጠነሰሰ ባብራራበት ጽሁፉ፤”ዘርዓያዕቆብ የፍልስፍና ት/ቤት የሚል ተቋም ለማቋቋም በማደርገው ጥረት ውስጥ በ3 ዙር (በሃምሌ 2008፣ በህዳርና በጥር 2009 ዓ.ም) ወጣቶችን በሳምንት ሦስት ቀን “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” እና ሌሎችንም የፍልስፍና ትምህርቶች በአማርኛ ማስተማር ጀመርኩ፡፡ ከእነዚህ ኮርሶች ውስጥ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚለውን ትምህርት  የመጀመሪያው ዙር ላይ በአንድ ሳምንት ነበር የጨረስኩት፤ ሁለተኛ ዙር ላይ ደግሞ አንድ ወር ፈጀብኝ፡፡ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ እምነትና ሥነ ጽሁፍ ጋር እያያያዝኩት ስሄድ ግን ነገሩ በጣም ሰፊ እንደሆነ ተረዳሁ፡፡” ይላል፡፡
ከዚያስ? ደራሲ ብሩክ ዓለምነህ ማብራሪያውን ይቀጥላል፤ ”ስለ ዘርዓያዕቆብ ይበልጥ ባሰብኩና ባስተማርኩ ቁጥር አዳዲስ ዕይታዎች ሁሉ ይመጡልኝ ጀመር፡፡ በሂደትም የዘርዓያዕቆብን፣ የወልደህይወትን፣ የዶ/ር እጓለንና የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን ትምህርቶች አንድ ላይ በመስፋት፣ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ምን እንደሚመስል ቅርጽ መስጠት እንደሚቻል እየተረዳሁ መጣሁ። እንግዲህ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚለውን ትምህርት፣ በመጽሐፍ መልክ የማሰናዳቱ ሃሳብ የመጣው በዚህ ወቅት ላይ ነበር” ብሏል፡፡
“ትንታኔ”፣”ሀገራዊ ቁጭት” እና “የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት ሐተታዎች” በሚሉ ሦስት ክፍሎች፣ በ352 ገጾች ተቀንብቦ የተሰናዳው የኢትዮጵያ ፍልስፍና የማስተማሪያ መጽሐፍ፤ ዋጋው 91 ብር ከ50 ሳንቲም እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡  ደራሲው ከዚህ ቀደም “ፍልስፍና-1” እና “ፍልስፍና-2” የተባሉ መጻህፍትን ለንባብ ያበቃ ሲሆን በአዲስ አድማስ ጋዜጣና ውይይት መጽኄት ላይ የተለያዩ ፍልስፍናዊ መጣጥፎችን በመጻፍ ላይ ይገኛል፡፡  
በአያሌው ወረታ የተጻፉ የወግ፣መጣጥፍ፣ ማስታወሻና ልቦለድ ስብስቦችን ያካተተው፣ “ከንዱራ” የተሰኘው መጽሐፍም በገበያ ላይ የዋለው ሰሞኑን ነው። የመጽሐፉ ታሪኮች፤ “ወዮላችሁ”፣”ቤዛ”፣ “ከንዱራ”፣ ”የኛ ቀበሌ ወጎች”፣ ”የጉዱ ጣሴ ማስታወሻ”፣ ”ናጽነት” እና “አንጎልን ውጦ” በሚሉ ርዕሶች የቀረቡ ሲሆን በ194 ገጾች የተቀነበበው ስብስቡ፤ በ70 ብር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡
“ዘመነ ኮንዶሚኒየም ሲቃረብ የህዝብ ብዛት ይጨምራል፤ ቤት አልባዎች ይበዛሉ፤ የጨረቃ ቤቶች ይስፋፋሉ፤ መሬትም እንቁነቷን ታውጃለች። አልጠግብ ባዮች እንደ አሸን ይፈላሉ፤ መንግስትንም መከታ ያደርጋሉ፤ በጉያውም ይሰገሰጋሉ፡፡ እልፍ አዕላፍ ቤት የለሾችንም ይንቁአቸዋል፤ ምሬታቸውንም ይዘባበቱበታል፡፡ ይህን ጊዜ ጭንቀትና አበሳ በመንግስት ላይ ይወድቃል። እርሱም የባሰባቸውን “ኑ ወደ እኔ” ይላቸዋል። ሽቅብ ያሰፍራቸው ዘንድም ይሯሯጣል። የተቀሩትንም አይዟችሁ ይላቸዋል፡፡ ምድርን ግን  ትመቻቸው ዘንድ ላላቸው ይመትርላቸዋል---” እያለ ይቀጥላል -”ወዮላችሁ” በሚል ርዕስ የቀረበው የመጀመርያው መጣጥፍ፡፡

Read 2817 times