Sunday, 27 August 2017 00:00

ከ500 ሚ. ብር በላይ የፈጀ የፓስታ ፋብሪካ ሥራ ሊጀምር ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

      ገበሬዎች የስንዴ ምርት ለፋብሪካው ያቀርባሉ ተብሏል
        በጅቡቲ ባለሃብቶች በአዳማ ከተማ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የዱቄትና ፓስታ ፋብሪካ በመጪው መስከረም ወር ሥራ ይጀምራል፡፡
በቀን 66 ቶን ፓስታ የማምረት አቅም ያለው ይኸው ፋብሪካ ፤የማምረቻ ማሽኖቹን ከጀርመን ያስመጣ ሲሆን በአዲሱ ዓመት መስከረም ወር የመጀመሪያ ሳምንታት ላይ ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት እንደሚገባ የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ድሬ አሊ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት አስርት አመታት በዋናነት የመዋል ፓስታ አስመጪና አከፋፋይ በመሆን ሲሠራ በቆየው አልቪማ አስመጪና ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተገነባው ፋብሪካው፤ በቀን 120 ቶን ዱቄትና 66 ቶን ፓስታ የማምረት አቅም አለው ተብሏል፡፡ የተለያዩ የፓስታ ምርቶችን ከውጪ አገር የምታስገባው ኢትዮጵያ፤ ባለፈው ዓመት ብቻ 40 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የፓስታ ምርቶችን ከውጭ አስገብታለች፡፡ ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ፣ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚያስፈልገውን የፓስታ ምርቶች በማምረት የተጠቃሚውን ፍላጎት ለማርካት እንተጋለን ብለዋል - ሥራ አስኪያጁ፡፡
ኩባንያው፤ ለዱቄትና ፓስታ ምርት የሚያስፈልገውን የስንዴ አቅርቦት ለማሟላት በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ በሥራቸው 1000 ገበሬዎችን ከያዙ የህብረት ሥራ ማህበራት ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

Read 2081 times