Saturday, 07 April 2012 09:06

ሪሃና ዊትኒን ለመተወን ትፈልጋለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የ23 ዓመቷ የሙዚቃ አቀንቃኝ ሪሃና ሰባተኛ አልበሟን እየሰራች፣ ጐን ለጐን የዊትኒን ህይወት በሚተርክ ፊልም ላይ ለመተወን ፍላጎት እንዳላት ተገለፀ፡፡ ሪሃና 6ኛ አልበሟን “ቶክ ዛት ቶክ” ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ለገበያ ያበቃች ሲሆን ዘንድሮ ወደ ፊልም ትውና በመግባት “ባትልሺፕ” በተባለ ሳይንሳዊ ልቦለድ ላይ መስራቷ ታውቋል፡፡ በዚሁ ትወናዋ የተደሰተችው ሪሃና በሙዚቃዋ ተምሳሌቴ ነበረች የምትላትን ዊትኒ ሂዩውስተንን የመተወን ፍላጎት እንዳላትም ሰሞኑን ተናግራለች፡፡

በዊትኒ ሂዩውስተን ግለ ታሪክ ላይ ተመስርቶ ለሚሰራው ፊልም ሪሃና መመረጧን አንዳንድ መረጃዎች ያወሱ ቢሆንም እስካሁን በይፋ የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡ የዊትኒን ታሪክ ለመተወን ከሪሃና ሌላ ጄኒፈር ሁድሰን፤ ቪቪካ ኤ ፎክስና ሜጋን ውድ የተባሉ አርቲስቶችም ስማቸው እየተጠቀሰ ነው፡፡  የዊትኒ ሂዩውስተን ሙዚቃዎች ሁሌም በቤቷ እንደሚሰማ የተናገረችው ሪሃና ማርያ ኬሪና ሴለንዲዮንም የምትወዳቸው ድምፃውያን መሆናቸውን ገልፃለች፡፡ ሪሃና፤ በቀጣይ ዓመት በመላው ዓለም በመዘዋወር አስደናቂ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ለመስራት ፍላጎት እንዳላትም ያስታወቀችው ሰሞኑን ነው፡፡

ሪሃና ከክሪስ ብራውን ጋር በፍቅር ለመቀጠል ማሰቧን ማኔጅመንቷ እየተቃወመ ሲሆን እንደውም አጠገቡ እንዳትደርስ ማዕቀብ ለማድረግ እየጣረ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ሪሃና በበኩሏ “ከክሪስ ጋር መሆን ከፈለግሁ የሚከለክለኝ የለም” ማለቷን የጠቀሰው ቦስተን ሄራልድ ጋዜጣ፤ በአንድ ወቅት “ፍቅር ሻርክ ባለበት ባህር ውስጥ እንደመዋኘት ነው” ብላ የተናገረችውን በመጥቀስ አርቲስቷ ፍላጎቷ ከክሪስ ጋር በጓደኝነት መቀጠል ነው ብሏል፡፡ ምናልባትም ሪሃና በድብቅ ከክሪስ ብራውን ጋር ያላትን ግንኙነት በመቀጠል ማኔጅመንቷን ለማሳጣት ሙሉ አልበም ትሰራ ይሆናልም ብሏል - ጋዜጣው፡፡

 

 

Read 1511 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 09:08