Print this page
Saturday, 26 August 2017 11:56

“…ልጅ መውለድ …ተፈጥሮአዊ ሂደት …”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ልጅ መውለድ ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው፡፡ ልጅ መውለድ ተፈጥሮ እራስዋ የምታዘጋጀው መገታት የማይችል ፍላጎት ነው፡፡ የሰው ልጅ ልጅ መውለድን በሕይወቱ ውስጥ እንደ አንድ ዋስትና አድርጎ ይቆጥረዋል። ሰው ልጅ መውለድ ካልቻለ ትልቅ ነገር እንደጎደለው የሚ ቆጥርበት አጋጣሚ በብዛት ይስተዋላል፡፡ በእርግጥ አልፎ አልፎ አለመውለዳቸውን በፀጋ የሚቀበሉ ቢኖሩም የብዙዎች ስሜት ግን ሲጎዳ ይታያል፡፡
ዶ/ር መብራቱ ጀምበር
የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት
ልጅን ስለ መውለድ ለዚህ እትም እንግዳ ያደረግነው ዶ/ር መብራቱ ጀምበር የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ልጅን መውለድ በምጥ ወይንስ በኦፕራሲዮን? ለሚለው ሀሳብ ማብራሪያቸውን እንደሚከተለው ለአንባቢ አጋርተዋል፡፡
ጥ /    ልጅ በምን መንገድ ይወለዳል?
መ/ እስከአሁን ድረስ የሚታወቁት የልጅ መውለጃ መንገዶች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው በተፈጥሮ መንገድ በምጥ ሲሆን ሌላ ደግሞ በኦፕራሲዮን ነው፡፡ በኦፕራሲዮን የሚወልዱት በተፈጥሮአዊ መንገድ በተለያዩ ምክንያቶች መውለድ የማይችሉት ናቸው፡፡ በምጥ መውለድ ማለት ተፈጥሮአዊውና የተፈቀደው መንገድ በመሆኑም ትክለኛው የአወላለድ ዘዴ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ በዚህ መንገድ ልጆች ይወለዳሉ፡፡ በኦፕራሲዮን የሚወለደው በምጥ ከሚወለደው ቁጥሩ ያነሰ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ወይንም የህክምና ጥበቡ ባላደገበት ወቅት ብዙ እናቶች በተፈጥሮ መንገድ ልጅ መውለድ እያቃታቸው ለተለያዩ አካላዊ ጉዳቶች መጋለጥ እንዲሁም የሚወለዱት ልጆች ላይም ጫና የመድረስ ከዚህም ባለፈ እናቶች ብዙ የሚጎዱበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን ግን በኦፕራሲዮን ማዋለዱ በስፋት እና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየተሰራ ስለሆነ በምጥ መውለድ ያቃታቸው ሴቶችም ይሁኑ መወለድ ያቃታቸው ልጆች ከጉዳት ላይ የሚወድቁበት አጋጣሚ የለም ማለት ይቻላል፡፡
ጥ/    በምጥ የመውለድ ጠቀሜታ ምንድነው?
መ/    በምጥ መውለድ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ተፈጥሮአዊ ሂደት በመሆኑ የሚሰጠው ደስታ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በምጥ የወለዱ ሴቶች አቅማቸው ቶሎ ይጠነክራል፡፡ አምጠው ሲወልዱ የእናትነት ፍቅሩም የተሻለ ይሆናል የሚል ግምት አለ። በምጥ ሲወልዱ ቶሎ ያገግማሉ፡፡ ከልጃቸውም ጋር ወዲያውኑ ስለሚገናኙ ቶሎ ጡት መስጠት ይችላሉ። ይህ በፍጥነት መገናኘት ፍቅሩንም ከፍ ያደርገዋል። ለዚህም ሲባል ልጁ በምጥ እንደተወለደ እትብቱ ሳይቆረጥ ከእናቱ ሆድ ላይ እንዲያርፍና ጡት እንዲይዝ በመደረግ ላይ ነው፡፡  ልጆቹም ቶሎ የእናታቸውን አይን ማየታቸው ትልቅ ስሜት እንዳለው ጥናቶች ያረጋግጣሉ።
ጥ/    በኦፕራሲዮን የመውለድ ጠቀሜታ ምንድነው?
መ/    በኦፕራሲዮን የመውለድ ጠቀሜታው በመጀመሪያ እናትየው በምጥ ብትወልድ ሊደርስ ባት የሚችለውን ጉዳት ማስወገድ መቻሉ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ልጁ በምጥ ቢወ ለድ የከፋ ጉዳት የሚደርስበት ከሆነ  እና አደጋ ሊደርስ ይችላል ተብሎ በሕክምናው ሲረጋገጥ ወደኦፕራሲዮን ይኬዳል፡፡  ነገር ግን በአሁን ጊዜ ያስቸገረው ነገር በፍላጎት በኦፕራሲዮን ካልወለድኩ የሚሉ ሴቶች መብዛታቸው ነው፡፡ የዚህም ምክንያቱ አንዳንዶቹ በፍርሀት ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ አስቀድመው በማንበብ ብልት አካባቢ የጡንቻ መላላት ሊያስከትልብኝ ይችላል ከሚል ስጋት የተነሳ ነው፡፡
ጥ/    በምጥ መውለድ የሚያደርሰው ችግር አለ?
መ/    በምጥ መውለድ ችግር ሊገጥመው ከሚያስችላቸው ነገሮች አንዱ ያልተመጣጠነ የምጥ ሁኔታ ከተፈጠረ ነው፡፡ ይም ማለት የልጁ ኪሎ ከእናትየው የመውለድ አቅም ጋር ካልተመጣጠነ በምጥ ሰአት በእናትየውም …በሚወለደውም ልጅ ላይ ጉዳት ሊከተል ይችላል፡፡ በምጥ ሰአት ምጡ ከባድ እና ረዥም ሰአት የሚወስድ ከሆነ የፊኛ፣ የሰገራ መውጫ መቀደድ፣ የፌስቱላ ሕመም ሊያጋጥም ይችላል፡፡ እነዚህን ነገሮች አስቀድሞ መተንበይ ስለሚቻል የእርግዝና ክትትል የምታደርግ ሴት ከሆነች ሐኪምዋ በምን መውለድ እንዳለባት አስቀድሞ መወሰን ይችላል፡፡
ጥ/    በኦፕራሲዮን መውለድ  የሚያደርሰው ችግር አለ?
መ/    በኦፕራሲዮን መውለድንና በምጥ መውለድን ስናወዳድር በኦፕራሲዮን መውለድ የበለጠ አሳሳቢ ነገር አለው፡፡ አስቀድሞ ከማደንዘዣው ጋር በተያያዘ ሊፈጠር የሚችል ጉዳት ሊኖር ይችላል፡፡ በኦፕራሲዮን ወቅት በማህጸን አካባቢ ያሉ ሌሎች የሰውነት ክፍሎችም ሊጎዱ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። ለምሳሌም አንጀት፣ ፊኛ፣ የሽንት መሽኛ መስመር፣ የሰገራ መውጫ ከውስጥ በኩል ሊጎዳ ይችላል።  በእርግጥ ይህ አልፎ አልፎ በተለይም ቀደም ብለው በኦፕራሲዮን የወለዱ ሴቶች ላይ የሚያጋጥም እንጂ ሁልጊዜ የሚከሰት አይደለም፡፡ አጋጣሚው ሊፈጠር ሚችለውም በአስቸኳይ ወይንም በአጣዳፊ በሚሰራበት ጊዜ ነው። በእርግጥ ጉዳቱ ከታየ የሚስተካከል ሲሆን መጥፎ የሚሆነው ግን ጉዳቱ መፈጠሩ ሳይታይ ከቆየ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ባለሙያ እንደዚህ ያለ አጋጣሚ ሊከሰት እንደሚችል አስቀድሞ ስለሚያውቅ ስራውን ሲጨርስ ሁኔታዎችን ሳያረጋግጥና ሳይፈትሽ አይወጣም። ኢንፌክሽን ወይንም መመረዝን በሚመለከት ግን በምጥም ይሁን በኦፕራሲዮን በመውለድ ጊዜ ሊያጋጥም የሚችል ሲሆን ነገር ግን በኦፕራሲዮን በመውለድ ጊዜ የሚፈጠረው የበለጠ አስከፊ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ወላዶች ከሐኪማቸው በሚነገራቸው መመሪያ መሰረት በጥንቃቄ ሁኔታዎችን መከታተል ይገባቸዋል፡፡
ጥ/    የምጥ ሕመም እንዳይሰማ የሚያደርግ መድሀኒት አለ?
መ/    በአለም ላይ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ የሚገኝ እንደግማሽ ማደንዘዢያ የሚቆጠር ሙሉ ለሙሉ የምጡን ሕመም ስሜት አጥፍቶ ሌላ ሰውነት ግን እንዳይደነዝዝ የሚያደርግ መድሀኒት አለ፡፡ በአገራችን ግን ገና ያልተለመደ ነው፡፡
ጥ/    በኦፕራሲዮን የሚወለዱ ልጆች አእምሮአቸው በምጥ ከተወለዱት ይልቅ ንቁ ነው ይባላል? እውነት ነውን?
መ/    ይሄ አሻሚና በትክክል ለመመስከር የሚያስቸግር ነው፡፡ አንዳንድ ጥናት አቅራቢዎች በኦፕራሲዮን የተወለዱ ህጻናት ጭንቅላታቸው በምጥ ስላልተገፋ ይበልጥ አእምሮአቸው ንቁ ናቸው ሲል አንዳንዶች ደግሞ ይልቁንም አንድ ሕጻን ከመወለዱ በፊት በሳንባው እና በአንጀት አካባቢ ውሃ ስለሚኖረው በምጥ ወቅት እየተገፋ በሚያልፍበት አጋጣሚ በሂደት እየተጨመቀ ውሀው ከሰውነቱ እንዲወጣ ስለሚያግዝ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ቅድሚያ የሚሰጠው በተፈጥሮ መንገድ በምጥ መውለድ ነው፡፡
ጥ/    ልጅ ወልጃለሁ ብላ የምትደሰተው የትኛዋ ናት?
መ/    ልጁ እንደተወለደ በእናቱ ሆድ ላይ እንዲቀመጥ ወዲያውኑ ጡት እንዲጠባ በፍጥነት ከእናቱ ጋር እንዲተያይ በመደረጉ ምክንያት በምጥ የወለደች ሴት እርካታዋ ፈጠን ያለ ይሆናል፡፡ ከነአባባሉም “ምጡን እርሽው ልጁን አንሽው” ይባላል፡፡ የነበረው ሕመም ሁሉ ልክ ልጁ ሲታይ ስለሚጠፋ ነው፡፡ በኦፕራሲዮን የምትወልደው ደግሞ ምንም እንኩዋን በፍጥነት ከልጁዋ ጋር ባትገናኝና ጡት ባታጠባውም እሱን ለማግኘት ስትል በከፈለችው መስዋእትነት የተነሳ በሰላም ከወለደችው ልጅ ጋር ለመገናኘት በመብቃትዋ ደስተኛ ትሆናለች። ስለዚህ ደረጃው ይለያይ እንጂ ሁለቱም ደስተኞች ይሆናሉ፡፡
ጥ/    የምጥ ሕመም እንዳይፈራ  ምን ማድረግ ይጠቅማል?
መ/    ማስተማር ነው፡፡ አስቀድሞ በእርግዝና ወቅት ሁኔታውን እንዲያውቁት ማድረግ ይጠቅማል። በእንግሊዝኛው አራት ..ፒ..ዎች አሉ፡፡ (passage, passenger, psychology, power) ይህ ማለትም ስለምጥ እውቀት እንዲኖር ከልጁ አፈጣጠር ጀምሮ እስከ ምጥ ድረስ ያለውን ሂደት በሚመለከት የስነልቡና ዝግጅት በማድረግ አቅምን እንዴት አምቆ ልጁን መውለድ እንደሚቻል የሚያሳይ ስልጠና ነው፡፡ ያረገዙ እናቶች በዚህ መልክ ቢዘጋጁ እና ምጥ ማለት ተፈጥሮአዊ ሂደት መሆኑን እንዲቀበሉ ቢደረግ  ትክክለኛውን መንገድ እንደያዙ ይቆጠራል፡፡

Read 6053 times
Administrator

Latest from Administrator