Sunday, 27 August 2017 00:00

የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጭ ማነው? ኃይሌ፤ ቀነኒሳ፤ ሞ ፋራህ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

    · “ለኔ የምንግዜም ምርጥ ኃይሌ ነው” ሎርድ ሴባስቲያን ኮው
        · በዓለም ሻምፒዮናና በኦሎምፒክ ሞ ፋራህ 10፤ ቀነኒሳ 8፤ ኃይሌ 6 የወርቅ ሜዳሊያዎች
        · ብዙ ሪከርዶች ያስመዘገበው - ኃይሌ፤ በ10ሺ እና በ5ሺ ላፉት 12 ዓመታት የሪከርድ ባለቤት - ቀነኒሳ
          · በ2 ኦሎምፒክና በ2 የዓለም ሻምፒዮና ተከታታይ ድርብ ድሎች በማስመዝገብ - ሞ ፋራህ
          · ከ20 ሚ. ዶላር በላይ የስፖንሰርሽፕና የተለያዩ ንግድ ገቢዎች - ሞ ፋራህ
           · የገንዘብ ሽልማት ኃይሌ 3.6 ሚ. ዶላር፤ ቀነኒሳ 1.9 ሚ. ዶላር፤ ሞ ፋራህ 647.2 ሺህ ዶላር
            · 145 ድል ሞ ፋራህ፤ 142 ድል ኃይሌ፤ 115 ድል ቀነኒሳ
               · ብዙ የተፃፈለት ኃይሌ፤ ሁለቴ የዓለም ኮከብ የተባለ ቀነኒሳ

     የዓለማችን የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጭ ማነው? የሚለው ጥያቄ የአትሌቲክሱን ዓለም በየጊዜው ሲያከራክር ቆይቷል፡፡ በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሰሞን በተመሳሳይ አጀንዳ የወጡ ዘገባዎች፤ ክርክሮችና ውይይቶች ነበሩ፡፡ እንግሊዛዊው  ሞ ፋራህ በ10ሺ ሜትር የመጨረሻ ውድድሩን በዓለም ሻምፒዮና ከማድረጉ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ በ10 ሺ ሜትር ውድድሩ ላይ የኬንያ፣ የኢትዮጵያ፣ የኡጋንዳ የኤርትራ አትሌቶችን በፍፁም የበላይነት በማሸነፍ 10ኛ የወርቅ ሜዳልያውን በዓለም ሻምፒዮናው ሲወስድ  በብዙዎቹ የእንግሊዝና የአውሮፓ ሚዲያዎች በረጅም ርቀት የምንግዜም ምርጥ ሯጭ ተብሎ ተወድሷል፡፡ የሁለቱን የኢትዮጵያ ታላላቅ የረጅም ርቀት ሯጮች ኃይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለን  ስኬቶችን ከግምት ያላስገቡ ውዳሴዎች ነበሩ እንጅ።
በ2012 እኤአ ላይ ለንደን 30ኛው ኦሎምፒያድ ባስተናገደችበት ወቅት ከኦሎምፒኩ በፊት እና በኋላ ይሄው ጉዳይ አበይት መነጋገርያ ነበር፡፡ አትሌቲክስ ዊክሊ  የዓለማችን የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጭ  ማነው? በሚል ጥያቄ መነሻነት ከአንባቢዎቹ ድምፅ በማሰባሰብ  የሰራው ሪፖርት በተለይ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በወቅቱ ኃይሌ ገብረስላሴ አንደኛ ደረጃ የወሰደው ከተሰበሰበው ድምፅ 45.6 በመቶ ድርሻ በማስመዝገብ ነበር፡፡ ኤሚል ዛቶፔክ 20.3፤ ቀነኒሳ በቀለ 15.2፤ ሞ ፋራህ 8.6፤ አበበ ቢቂላ 8፤ ፓቮ ኑርሚ 5.5 እንዲሁም ላርስ ቪረን 3 በመቶ የድምፅ ድርሻ በማስመዝገብ ከሁለት እስከ ሰባት ያለውን ደረጃ ወስደዋል፡፡  በ2016 እኤአ ላይ ደግሞ  የብራዚሏ ሪዮ ዲጄኔሮ 31ኛውን ኦሎምፒያድ ስታዘጋጅ አሁንም በተመሳሳይ አጀንዳ በአትሌቲክሱ ዓለም ክርክሩ አገርሽቶ ነበር፡፡ ሞ ፋራህ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ለሁለተኛ ተከታታይ ኦሎምፒክ ድርብ ድል ካስመዘገበ በኋላ የዓለማችን የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጭ በሚለው ውዳሴ ሲደነቅ ብዙ ሙግት ነበር፡፡
በ2013 እ.ኤ.አ ላይ በሞስኮ ተካሂዶ በነበረው የ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ሞ ፋራህ በ10 ሺህና በ5 ሺ ሜትር ድርብ ድል ለመጀመርያ ጊዜ ሲያስመዘግብ የእንግሊዝና የአውሮፓ ሚዲያዎች የምንግዜም ምርጥ እያሉ ሲያወድሱት ነበር፡፡ በሞስኮ ሉዝንስኪ ስታድዬም ከዓለም ሻምፒዮናው ጋር በተያያዘ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ የምንግዜም ምርጥ እየተባለ መጠራቱ ተገቢ አለመሆኑን በሚያመለክት ስሜት ያቀረብኩለት ጥያቄ ነበር፡፡
“የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጭ ለመባል የዓለም ሪከርዶች ማስመዝገብ አያስፈልግም ወይ….” በሚል ሞ ምላሹን ሲሰጥ “ለሪከርዶች የቀረበ ብቃት ቢኖረኝ ደስተኛ ነኝ፡፡ በርግጥ ያሉትን ክብረወሰኖች ለመስበር ብዙ ጥረት አላደርግም፡፡ ዋናው ትኩረቴ የዓለም እና የኦሎምፒክ ሻምፒዮናን በመሆን ተደጋጋሚ ድሎች ማስመዝገብ እና ለአገሬ ብዙ ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ነው፡፡” ብሎ ነበር፡፡
የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (laaf) ፕሬዝዳንት የሆነው  እንግሊዛዊው ሎርድ ሴባስቲያን ኮው በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ሰሞን የዓለምን የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጭ ማነው ተብሎ ተጠይቆ ነበር።  ‹‹ሞ ፋራህ የሚደነቅ አትሌት ቢሆንም፤ ለእኔ የምንግዜም ምርጥ ኃይሌ ገብረስላሴ ነው፡፡ በረጅም ዓመታት የሩጫ ዘመኑ፣ በብዙ ርቀቶች በመወዳደር እና በተደጋጋሚ የዓለም ሪከርዶችን በማስመዝገብ የሚፎካከረው ስለሌለ፡፡” በማለት ምክንያቱን አቅርቧል ፡፡ በርግጥ የምንግዜም ምርጥ አትሌትን ለመለየት የሚካሄዱ ምርጫዎችና ውጤቶቻቸው አከራካሪነታቸው ይጠበቃል፡፡ የማወዳደርያና የመለኪያ መስፈርቶች፤ የማነፃፀርያ መንገዶች እና መመዘኛዎች፤ የሩጫ ውድድር አይነቶች፤ እድሜና ሌሎች ሁኔታዎች …ታላላቆቹን አትሌቶች  በእኩልነት ለመመልከት የማያመቹ ናቸው፡፡ ሞ ፋራህ በረጅም ርቀት ተወዳዳሪነት በአትሌቲክሱ ዓለም የነገሰው ባለፉት 6 ዓመታት ነው፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ደግሞ በረጅም ርቀት ውድድሮች ከ20 ዓመታት የውጤት የበላይነት ሲያሳዩ የኖሩ ናቸው፡፡ በተጠቀሰው የሩጫ ዘመን ሁለቱ የኢትዮጵያ አትሌቶች ከኬንያውያን ምርጥ አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክር ይገጥማቸው ነበር።   የ10ሺ እና የ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርዶችን በማስመዝገብ ያበረከቱት አስተዋፅኦም መጠቀስ ያለበት ነው፡፡ ይህ የስፖርት አድማስ ትንታኔ ሶስቱን የዓለማችን የረጅም ርቀት ታላላቅ አትሌቶች በተለያዩ ሁኔታዎች የሚያነፃፅር ሲሆን የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጭ ማነው የሚለውን ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
በዓለም ሻምፒዮና፤ በኦሎምፒክ ሜዳልያዎችና ሌሎች
በ10ሺ ሜትር እና 5ሺ ሜትር ውድድሮች በተለይ በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና  10 የወርቅ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ ብልጫ የሚወስደው ሞ ፋራህ ነው፡፡ ቀነኒሳ በቀለ በ8 የወርቅ ሜዳልያዎች ሲከተለው ኃይሌ ደግሞ 6 የወርቅ ሜዳሊያዎች ተጎናፅፏል፡፡ በኦል አትሌቲክስ ድረገፅ ላይ የሶስቱን አትሌቶች ዝርዝር የውጤት ታሪክ በመዳሰስ መገንዘብ የሚቻለው ግን የተለየ ነው፡፡ ከዓለም ሻምፒዮና እና ከኦሎምፒክ ሜዳልያዎች ባሻገር በሌሎች ስኬቶች ቀነኒሳ እና ኃይሌ እንደቅደም ተከተላቸው ከሞ ፋራህ በእጅጉ ብልጫ አላቸው፡፡
ቀነኒሳ በቀለ 3 ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮንና 5 ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ከመሆኑ በላይ  12 ጊዜ የዓለም አገር አቋራጭ አሸናፊ በመሆን ከሁለቱ አትሌቶች በተለየ ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግቧል። በተጨማሪም 3 ጊዜ የዓለም አትሌቲክስ ፍፃሜ አሸናፊ ፤1 ጊዜ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮን ፤2 ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን፤ 1 ጊዜ የኦል አፍሪካን ጌምስ አሸናፊ ፤1 ጊዜ የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮን፤ 2 የዳይመንድ ሊግ ውድድሮችና 17 የጎልደን ሊግ ውድድሮች ያሸነፈ ነው - ቀነኒሳ በቀለ። ኃይሌ ገብረስላሴ 2 ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮንና 4 ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ ከቀነኒሳ እና ከሞ ፋራህ በተለይ የሚልቅበት ውጤቱ ግን 4 ጊዜ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮን መሆኑና 9 ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች ማሸነፉ ነው። ሞ ፋራህ 4 ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮንና 6 ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን በመሆኑ ከሁለቱ የላቀ የውጤት ታሪክ ሆኖ ሲመዘገብለት፤ 18 ጊዜ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ማሸነፉም ይጠቀሳል፡፡
በሪከርዶች፤ በምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች እና ሌሎች ደረጃዎቹ
በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ውድድሮች በሩጫ ዘመናቸው ባስመዘገቧቸው ሪከርዶች ሶስቱ አትሌቶች ሲነፃፀሩ የላቀ ሆኖ የሚገኘው ኃይሌ ገብረስላሴ ነው፡፡ ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጭ ለመባል በውድድር ርቀቶቹ የዓለም ሪከርዶችን ማስመዝገብ ወሳኝ ነው፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ስማቸውን በተደጋጋሚ በሪከርድ መዝገብ ሊያሰፍሩ በመቻላቸው  ከሞ ፋራህ ይበልጣሉ፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ በ10ሺ ሜትር እና 5 ሺ ሜትር በሩጫ ዘመኑ 7 ሪከርዶችን ያስመዘገበ ሲሆን ቀነኒሳ በቀለ 3 ጊዜ ሪከርዶችን አስመዝግቧል፡
በረጅም ርቀት ባስመዘገባቸው የበዙ ሪከርዶች በተለይ መጠቀስ ያለበት ኃይሌ ሲሆን ከ1999 እስከ 2009 እኤአ ባሉት 19 የውድድር ዘመናት 27 ሪከርዶች እና ምርጥ ፈጣን ሰዓቶችን ስላስመዘገበ ነው፡፡ ከ27ቱ መካከል በአይኤኤኤፍ የፀደቁለት 20 የዓለም ሪከርዶች የተነበሩ ናቸው፡፡ ኃይሌ  ሪከርዶቹን  በ17 የተለያዩ የአትሌቲክስ የውድድር አይነቶች ማስመዝገቡም በልዩ ስኬት ሊጠቀስለት ይበቃል፡፡ በ2000 እና 3000 የቤት ውስጥ አትሌቲክስ፤ በ5ሺ ሜትር የቤት ውስጥ አትሌቲክስና በትራክ ፤ በ2 ማይል የቤት ውስጥ እና ትራክ፤ በ10ሺ ሜትር በትራክ፤ በማራቶን፤ በጎዳናላይ ሩጫዎች በ10 ኪሎሜትር፤ በ15 ኪሎሜ፤ በ20 ኪሎሜ፤ በ25 ኪሎሜትር፤ በ10 ማይል፤ በግማሽ ማራቶንና በማራቶን ውድድሮች ክብረወሰኖችን ሊያስመዘግብ መቻሉ ለኃይሌ አድናቆት ያሰጠዋል፡፡
በሌላ በኩል በ5ሺ ሜትር እና በ10ሺ ሜትር ቀነኒሳ በቀለ ሁለት የዓለም ሪከርዶችን ላለፉት 12 ዓመታት ይዞ በመቆየቱ ከኃይሌ ገብረስላሴ ቀጥሎ የሚያስጠቅሰው የላቀ ስኬት ነው፡፡ በ5ሺ ሜትር  የዓለም ሪከርድ በ2004 እኤአ የተመዘገበው በቀነኒሳ በቀለ በ12 ደቂቃዎች ከ37.35 ሴከንዶች ሲሆን ከእሱ በፊት ኃይሌ ገብረስላሴ ለ4 ጊዜያት በርቀቱ ሪከርዶች ሲያስመዘግብ 25.25 ሰከንዶችን አራግፏል፡፡ በ10ሺ ሜትር ውድድር የዓለም ሪከርድ በ2005 እኤአ ላይ የተመዘገበው በቀነኒሳ በቀለ በ26 ደቂቃዎች ከ17.53 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ ሲሆን ከእሱ በፊት ኃይሌ ለ2 ጊዜያት ሪከርዱን ሲያሻሽል 13.80 ሰከንዶችን ቀንሷል፡፡
ከ10ሺ እና ከ5ሺ ሜትር ባሻገር ኃይሌ የዓለም ማራቶን ሪከርድን  ለሁለት ጊዜያት ማስመዝገቡ በከፍተኛ ስኬት የሚነሳ ይሆናል፡፡  ኃይሌ ሁለቱን የማራቶን ሪከርዶች በበርሊን ማራቶን ያስመዘገባቸው ሲሆኑ በ2007 እኤአ ላይ 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃዎች ከ26 ሰኮንዶች   በሆነ ጊዜ ፤ በ2008 እኤአ ላይ ደግሞ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ59 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ርቀቱን በመሸፈን ነበር።  በአጠቃላይ በሁለቱ ማራቶን ሪከርዶቹ የርቀቱን ክብረወሰን በ46 ሰከንዶች አፍጥኖታል፡፡ ኃይሌ በሩጫ ዘመኑ ካስመዘገባቸው በአይኤኤኤፍ የፀደቁ  20 የዓለም ሪከርዶች መሮጥ ካቆመ በኋላ  ያልተሰበሩ ሁለት ዓለም አቀፍ ሪከርዶች አሉ፡፡ በ20 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በ2007 እኤአ በቼክ ኦስትራቫ 56 ደቂቃዎች ከ25.98 ሰከንዶች  እንዲሁም በ1 ሰዓት ሩጫ አሁንም በ2007 እኤአ 21285 ሜትሮች ርቀትን በመሸፈን የተመዘገቡት ናቸው፡፡ ለሞ ፋራህ ብቸኛ የሪከርድ ታሪኩ በአውሮፓ ደረጃ የተወሰነ ነው፡፡ በ1500 ሜ፣ በ3000 ሜ፣ በ2 ማይል፣ በ5 ሺ እና በ10 ሜትር 5 የአውሮፓ ሪከርዶችን በስሙ ስላስመዘገበ ነው፡፡
በ10ሺ ሜትር የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃን የሚመራው ባለሪከርዱ ቀነኒሳ በቀለ ሲሆን  እስከ 10 ባለው ደረጃ ሶስት ፈጣን ሰዓቶች ያሉት ኃይሌ በዚሁ ደረጃ ላይ በ1998 የ10ሺ ሜትር ርቀትን በ26 ደቂቃ ከ22.75 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ የሸፈነበት ጊዜ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡  በ5ሺ ሜትር ውድድር  የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃን አሁንም ባለሪርዱ ቀነኒሳ በቀለ ሲመራው ኃይሌ ገብረስላሴ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ሞ ፋራህ በ5 ሺህ ሜትር ያስመዘገበው ሰዓት ከዓለም 31ኛ በ10 ሺ ሜትር ያስመዘገበው ሰዓቱ ደግሞ ከዓለም 16ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡
ቀነኒሳ 21፣ ኃይሌ 18 እና ሞፋራህ 3 ውድድሮችን በ5 ሺ ሜትር ከ13 ደቂቃ በታች የገቡ ሲሆን  በ10 ሺ ሜትር ደግሞ ከ27.30 … በታች በመግባት  ኃይሌ 18 ቀነኒሳ 5 እና ሞፋራህ 4 ውድድሮችን አስመዝግበዋል፡፡
በማራቶን የምንግዜም ፈጣን ሰዓት ደረጃ ላይ ቀነኒሳ በቀለ የበርሊን ማራቶን በማሸነፍ ያስመዘገበው 2፡03፡03 የሆነ ጊዜ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠ ሲሆን የኢትዮጵያ ሪከርድም ነው፡፡ የኃይሌ ገብረስላሴ የማራቶን ፈጣን ሰዓት 2፡03፡59 እስከ 10ኛ ደረጃ የሚመዘገብ ሲሆን የሞፋራህ ደግሞ 2፡08፡29 ከ20ኛ ደረጃ የሚያልፍ ነው፡፡
በ10ሺ እና በ5ሺ ድርብ ድሎች
በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ በ10 ሺ እና በ5 ሺ ድርብድሎችን በማስመዝገብ የላቀ የሚሆነው ሞ ፋራህ ነው፡፡በዓለም ሻምፒዮና በ2013 እና በ2015 እኤአ እንዲሁም በኦሎምፒክ በ2012 እና በ2016 እኤአ ሞ ፋራህ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ድርብ የወርቅ ሜዳልያዎችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በቅርብ ርቀት ሊፎካከረው የሚችለው በዓለም ሻምፒዮና በ2009 እኤአ ላይ እንዲሁም በኦሎምፒክ በ2008 እኤአ ላይ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ድርብ ድሎችን ያስመዘገበው ቀነኒሳ በቀለ ሲሆን ኃይሌ ግን በዓለም ሻምፒዮናም በኦሎምፒክም ድርብ ድሎችን አስመዝግቦ አያውቅም፡፡
በብዙ የሩጫ ውድድር አይነቶች በመሳተፍ
በተለያዩ ርቀቶች ለረጅም የውድድር ዘመናት በመሮጥ ቀዳሚ የሚሆነው ኃይሌ ገብረስላሴ ነው፡፡ ለ27 አመታት በቆየበት የሩጫ ስፖርት ከመካከለኛ ርቀት 800 ሜትር አንስቶ፤ በረጅም ርቀት የ10ሺ እና 5ሺ ሜትር የትራክ እና የቤት ውስጥ ውድድሮች፤ ከ1 ማይል እስከ 10 ማይል በሚወስዱ ሩጫዎች፡ ከ10 እስከ 25 ኪሎሜትር በሚለኩ የጎዳና ላይ ሩጫዎች እና በማራቶን እና በግማሽ ማራቶን ውድድሮች በአጠቃላይ እስከ 26 በሚደርሱ የሩጫ ውድድር ዓይነቶች በመወዳደር እና አስደናቂ ውጤት በማግኘት በታሪክ መዝገብ ስሙን ያሰፈረ ነው። ሞ ፋራህ በ1500ሜ፤ በ3000ሜ፤ በ2 ማይል፤ በ5ሺ እና በ10ሺ ሜትር በግማሽ ማራቶን እና በማራቶን ተወዳዳሪነቱ ይታወቃል፡፡ ቀነኒሳ በቀለ ከሁለቱ የሚለየው በመካከለኛ ርቀቶች ምንም አይነት ተመክሮ ሳይኖረው በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር እንዲሁም በማራቶን በመሳተፉ ሲሆን በዓለም አገር አቋራጭ ሰፊ ልምድ በማካበት ኃይሌና ሞ ፋራህ አይስተካከሉትም፡፡
በስፖንሰርሺፕ፤ በሩጫ ኢንቨስትመንት እና ዘመናዊ ስልጠና
ከሪዮ ኦሎምፒክ ማግስት በታዋቂ የቢዝነስ ሚዲያዎች እንደተዘገበው ከሆነ ሞ ፋራህ በስፖንሰርሺፕና በተለያዩ የንግድ ገቢዎቹ ከኃይሌና ከቀነኒሳ ይበልጣል፡፡ ሞ ፋራህ  በሩጫ ዘመኑ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሃብት ማካበቱን የሚያመለክቱ መረጃዎች በደሞዝ፣ በገንዘብ ሽልማቶች ለተለያዩ የቦነስ ክፍያዎች እስከ 11 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በማስታወቂያ እና በተለያዩ የንግድ ገቢዎች ከ9 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቱን ገልፀዋል፡፡ ቨርጂን ሚዲያ፣ ሉሚዝ፣ ቪየተን እና ሃያንዳይ ማስታወቂያ ሞ ፋራህን የሚያሰሩ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ኃይሌ ሯጭ በነበረበት ወቅት ዋና ስፖንሰሮቹ፤ አዲዳስ እና ፓወር ባር ነበሩ፡፡ ሞ ፋራህ በልምምድ መርሃ ግብሮቹ ከኃይሌና ከቀነኒሳ የተለየ ነው፡፡  በቀን 120 ማይሎች የሚጠጋ ርቀትን ለልምምድ የሚሮጥ ሲሆን ለትልልቅ ውድድሮች በሚዘጋጅበት ወቅት የእረፍት ቀን የለውም፡፡ በስልጠና ወቅት አብረውት የሚሰሩት ከ12 በላይ ባለሙያዎች ሲሆኑ 3 ዶክተሮች ናቸው፡፡ በስነምግብ፤ በስነልቦና፤ በፊዚዮቴራፒ ከሚያገለግሉት ከእነዚህ ባለሙያዎች ጋር ዘመናዊ የስልጠና መርኃ ግብር በመከተል እየሰራ ስኬታማ ሊሆን ችሏል፡፡ በየዓመቱ  ለ6 ወራት በካምፕ ዝግጅት ያደርጋል፡፡
በገንዘብ ሽልማት
በዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ስታስቲክስ እና ውጤት አሰባሳቢ ተቋም በተሰራ ስሌት የምንግዜም ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ ያገኙ አትሌቶች ደረጃን የሚመራው  ኃይሌ ገብረስላሴ ሲሆን  በሰበሰበው 3 ሚሊዮን 546ሺ 674.80 ዶላር ነው፡፡ ቀነኒሳ በቀለ 1,882,063 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት 5ኛ ደረጃ ላይ ሲሆን ሞፋራህ በ647,153 ዶላር 19ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የጎዳና ላይ ሩጫዎች የስታትስቲክስ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ማህበር (ARRS/ Associations of Road racing statisticians)  በድረገፁ ይፋ እንዳደረገው  ኃይሌ ገብረስላሴ በሩጫ ዘመኑ በ142 ውድድሮች ያሸነፈ ሲሆን ሞ ፋራህ 145  እንዲሁም ቀነኒሳ 115 ውድድሮችን ማሸነፋቸው ተመዝግቧል፡፡
በመፅሃፍት
ስለሩጫ ህይወታቸው በተዘጋጀው መፅሐፍት ኃይሌ ገብረሥላሴ ግንባር ቀደም ነው፡፡ ቢያንስ አምስት እውቅ መፅሃፍት የሩጫ ዘመን ስኬቱንና ህይወት ታሪኩን በመንተራስ ለንባብ በቅተዋል። “ዘ ግሬተስት፡ ዘ ሃይሌ ገብረስላሴ ስቶረሪ” የሚባለው መፅሃፍ በራሱ ሃይሌ ገብረስላሴ እና በጂም ዴኒሰን የተፃፈ ነው፡፡ ሁለተኛው መፅሃፍ ደግሞ “ኃይሌ ገብረስላሴ ዘ ግሬተስት ራነር ኦፍ ኦል ታይም” በሚል ርእስ በክላውስ ዊዴት የተፃፈው ነው፡፡ ሶስተኛው በጀርመንኛ ቋንቋ የተፃፈውና ስለልምምድ ፕሮግራሙ እና የውድድር ብቃቱ “ላውሪን ዊዝ ሃይሌ ገብረስላሴ፤ ዳትሬኒንግ ፕሮግራም” በሚል ርእስ አበበ በተባለ ግለሰብ፤ በቀድሞ አሰልጣኙ ወልደመስቀል ኮስትሬ እና በራሱ በኃይሌ ገብረስላሴ ትብብር የተዘጋጀው ነው፡፡ አራተኛው መፅሃፍ  በታዋቂው ጃፓናዊ የአትሌቲክስ ፎቶግራፈር ጂሮ ሞቺዙኪ ‹ኃይሌ ገብረስላሴ ኤምፐረር ኦፍ ሎንግ ዲስታንስ› በሚል ርእስ በተለያዩ ፎቶዎች ታጅቦ የቀረበ ነው፡፡ አምስተኛው መፅሃፍ ደግሞ “ኃይሌ ገብረስላሴ፤ አፍሪካ ሌጀንድ ሲርዬስ” በሚል በኤልዛቤት ቴብላ የተዘጋጀው ነው፡፡ በሞ ፋራህ ዙሪያ ከተጻፉት 3 እና 4 መፅሐፍት “ትዊንአምቢሽን፡ ማይ አውቶ ባዮግራፊ” እና “ሬዲ ስቴዲ ሞ” ዋናዎቹ ናቸው። በሌላ በኩል በቀነኒሳ ዙሪያ ሊጠቀስ የሚችለው መፅሐፍ “Kenenisa Bekele” በሚል ርዕስ የሩጫ ዘመኑ ታሪክ አሀዛዊ መረጃዎችና ስታስቲኮች የተጠናቀሩበት በኤምሪ ክሪስ ፒል የተዘጋጀ ነው፡፡  
በክብር ሽልማት
በዓለም አትሌቲክስ ልዩ የክብር ሽልማቶችን በመጎናፀፍ አሁንም ኃይሌ ቀዳሚ ሆኖ ቢጠቀስም ሁለት ጊዜ የዓለም ኮከብ አትሌት የተባለው ቀነኒሳ ነው፡፡ በኦሎምፒኳ ከተማ ሉዛን ውስጥ  86 ዓመታት እድሜ ያለው በ‹ዘ አሶሴሽን ኢንተርናሲዮናሌ ዴላ ፕሬስ ስፖርትስ›  ልዩ ክብር ሽልማት፤ በስፔን ትልቅ ክብር የሚሰጠውን‹ፕሪንስ ኦስተሪዬስ አዋርድስ ፎር ስፖርትስ› በስፖርት የሰው ልጅን የላቀ ብቃት እና ችሎታ ያሳደገ አትሌት በመባል ከስፔን ንጉሳውያን ቤተሰብ እጅ የተቀበለው ሽልማት እንዲሁም በዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር በ2006፤2007 እና 2008 እኤአ የዓለም ምርጥ አትሌት ተብሎ ተሸልሟል፡፡
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ2004 እና በ2005 እ.ኤ.አ በኣለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የዓመቱ ኮከብ አትሌት በመባል ከፍተኛውን ሽልማት አግኝቷል፡፡

Read 6306 times