Sunday, 27 August 2017 00:00

በአማራ ክልል በ“አተት” ወረርሽኝ፣ የ42 ሰዎች ህይወት አልፏል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

ወረርሽኝ፣ የ42 ሰዎች ህይወት አልፏል
“በሽታውን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ከ100 ሚ. ብር በላይ ያስፈልጋል”
የክልሉ ጤና ቢሮ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የድጋፍ ጥሪ አቅርቧል
   በአማራ ክልል ከየካቲት ወር ወዲህ በተከሰተው የአተት ወረርሽኝ፣ የ42 ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡ የወረርሽኙ መነሻዎች የፀበል ቦታዎችና ሰፋፊ የእርሻ ልማት ጣቢያዎች እንደሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በአማራ ክልል በ8 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 50 ወረዳዎች ላይ በሽታው የተስፋፋ ሲሆን  በ47 ወረዳዎች ያህል የወረርሽኙ መነሻዎች የፀበል ቦታዎች እንደሆኑ መታወቁን ለአዲስ አድማስ ያስረዱት የክልሉ ጤና ቢሮ፣ የህብረተሰብ የጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ኃላፊ አቶ ተ/ሃይማኖት ገ/ህይወት፤ ከበሽታው ተጠቂዎች መካከልም 98 በመቶ የሚሆኑት በፀበል ቦታ የነበሩና የቀን ሰራተኞች እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡   
በበሽታው በስፋት ከተጠቁ አካባቢዎች መካከል የሰሜን ጎንደር፣ የደቡብ ጎንደርና የምዕራብ ጎጃም ዞኖች እንደሚገኙበት የጠቀሱት አቶ ተ/ሃይማኖት፤ ምስራቅ ጎጃም- አዊና ዋግህምራ ወረዳዎች ላይም መጠነኛ ስርጭት እንዳለ ተናግረዋል፡፡  የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ለሰፋፊ የእርሻ ጣቢያዎች የውሃ ማከሚያ ኬሚካሎች እየቀረቡ ነው ያሉት የጤና ቢሮ ሃላፊው፤ በፀበል ቦታዎች ግን ከእምነት ጋር በተገናኘ፣ ፀበሉን በኬሚካል ማከም ስለማይቻል፣ ስርጭቱን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል፡፡
በሽታውን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ተ/ሃይማኖት፤ ለዚህም የክልሉ ጤና ቢሮ፣ በፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል፣ አለማቀፉ ህብረተሰብ ድጋፍ እንዲያደርግለት ጥሪ ማቅረቡን አስታውቀዋል፡፡ በአሁን ወቅት የክልሉ መንግስት በሽታውን ለመቆጣጠር ከሚያደርገው ጥረት ጎን፣ ዩኒሴፍና አለማቀፉ ጤና ድርጅት (WHO) መሰለፋቸውም ታውቋል፡፡ ክልሉ የድጋፋቸውን መጠን በቁጥር ለይቶ ባይገልጽም፡፡   

Read 3312 times