Saturday, 26 August 2017 11:46

የፀጥታው ም/ቤት ቀጣይ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያ፤ በኤርትራ ላይ አዲስ የውሳኔ ሃሳብ ታቀርባለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

ከመስከረም ጀምሮ ለአንድ ወር የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት ፕሬዚዳንትነትን ቦታ ከግብፅ የምትረከበው ኢትዮጵያ፤ በኤርትራ ጉዳይ፣ አዲስ የውሳኔ ሃሳብ ይዛ እንደምትቀርብ  ይጠበቃል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን በሠጠው ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ የም/ቤቱን የፕሬዚዳንትነት ቦታ ከመረከቧም በተጨማሪ የፀጥታው ም/ቤት አባል ሃገራት፣ መደበኛ ስብሰባቸውን ጳጉሜ 2 እና 3 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚያደርጉም አስታውቋል፡፡  
ኢትዮጵያ የፀጥታው ም/ቤት የፕሬዚዳንትነት እድሉን ተጠቅማ፣ በኤርትራ ጉዳይ እንዲሁም በሶማሊያና የደቡብ ሱዳን ወቅታዊ የሠላም ሁኔታ ላይ አዳዲስ የውሣኔ ሃሳቦችን ታቀርባለች ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ተናግረዋል፡፡
“የኤርትራ መንግስት በትርምስ ሃይልነቱ እንደቀጠለበት ነው፤ ምንም አይነት የባህሪ ለውጥ አላመጣም” ያሉት አቶ መለስ፤ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በኤርትራ ጉዳይ ላይ  አዲስ የውሣኔ ሃሳቦችን የምታቀርበው ብለዋል፡፡
እስካሁን ኢትዮጵያ የፀጥታው ም/ቤት አባልነቷን በመጠቀም፣ የኤርትራ መንግሥት የተጣለበትን ማዕቀብ በመጣስ፣ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ማጋለጧን እንዲሁም ገምጋሚ ቡድን ወደ ኤርትራና አካባቢው ተጉዞ አስፈላጊውን ማጣራት እንዲያደርግ ያቀረበችው ሃሳብ በም/ቤቱ አባላት ተቀባይነት ማግኘቱን ቃል አቀባዩ አውስተዋል፡፡
የፀጥታው ም/ቤት፤ አስራ አምስቱ አባላት ጳጉሜ 2 እና 3 በአዲስ አበባ በሚያካሂዱት ስብሰባ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተገናኝተው፣ በአህጉሪቱ ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩም ተጠቁሟል፡፡

Read 2563 times