Sunday, 27 August 2017 00:00

ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ

Written by 
Rate this item
(13 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሽማግሌ ንጉሥ፤ በአንድ አገር ይኖር ነበረ፡፡ ንጉሡ አንድ ልጅ አለው፡፡ ይህ ልጅ ከዕውቀት ዕውቀት የሌለው፣ ከልምድ ልምድን ያላገኘ፣ በዕድሜውም ገና ለጋ ነበረ፡፡ ሆኖም የዕለት ሰርክ ምኞቱ፣ የአባቱን ዙፋን ወርሶ፣ በምቾት ተንደላቆ መኖር ነበር፡፡ ስለዚህ መኝታ ቤቱን ይዘጋና ነጋ ጠባ እንዲህ ሲል ይፀልያል፡-
“አምላኬ ሆይ፣ እስከ መቼ አልጋ - ወራሽ እየተባልኩ እቀመጣለሁ? ያረጀውን አባቴን ከዚህ ዓለም በቶሎ አሰናብትልኝ!”
ይሄን የሁልጊዜ ፀሎቱን እየደጋገመ ጮክ ብሎ ይፀልየዋል፡፡ አንድ ቀን በአጋጣሚ አባት የልጁን ፀሎት ሰማ፡፡
“ይህን ልጅ ከእንዲህ ያለ ቀቢፀ - ተስፋ ልገላግለው የምችለው እንዴት ነው?” እያለ ይጨነቅ ጀመር፡፡
ከብዙ ማውጣት ማውረድ በኋላ አንድ ዘዴ ታየው፡- አምላክን መስሎ፣ ፀሎቱን የሰማው አስመስሎ መልስ መስጠት፡፡
በዚህ መሠረት፣ አንድ ማታ ከልጁ መኝታ ጀርባ ተሸሽጎ እንዲህ አለው፡-
“ልጄ ሆይ! ፀሎትህን ሰምቻለሁ፡፡ ከእንግዲህ አባትህ ብዙ ዕድሜ አይኖረውም፤ ዙፋኑን ለመጨበጥ ተነሳ!”
ዕውነትም አባት ከዚያች ማታ ጀምሮ አልጋ ላይ ዋለ፡፡ ሆኖም አባት መታመሙን አገር ሁሉ ሰማ፡፡ የውስጥ ቦርቧሪዎች፣ የውጭ ወራሪዎች አገሪቱን አደጋ ላይ ጣሏት፡፡ ይንጧት ጀመር፡፡ ጊዜ ያመቻቸው የመሰላቸው ሁሉ ተረባረቡ፡፡ ልጅየው የሚያደርገው ጠፋው፡፡
ጭንቅ በጭንቅ ሆነ! ስለዚህ አምላክን ተማጠነ፡-
“አምላኬ ሆይ! በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠላት ተነሳብኝ፡፡ ምን እንደማደርግ ግራ ገባኝ፡፡ እባክህን መንገዱን ምራኝ?” አለ፡፡
ይህን ፀሎት የሰማው አባት፣ በአምላክ ተመስሎ፤ እንዲህ አለው፡-
“ፈጥነህ ወደ አባትህ ሂድ፡፡ ምክሩንም ጠይቀው፡፡ መዳኛህ የእርሱ ምክር ነው። እስትንፋሱ ሳያበቃ፣ የዕድሜ ፀጋውን አግኝ፡፡ በጭንቅ ሰዓት ምን ዓይነት ብልህነት ሊኖርህ እንደሚገባ ጠይቀውና የሚልህን በጥሞና አዳምጥ፡፡”  
ልጁ እየሮጠ ወደ አባቱ ሄደና፤ “አባቴ ሆይ፤ ምክርህን እሻለሁ፡፡” አለው፡፡
አባትየውም፤
“በመጨረሻ ወደ እኔ መጣህን? አሁንም አልረፈደም! አበክረህ አድምጠኝ” አለና ጀመረ፡፡ “በመጀመሪያ፤ በመከራህ ሰዓት የቅርብ ሰው እንደሚያስፈልግህ አስታውስ፡፡ ስለዚህ የቅርብህን ሰው አታርቅ! ለውርስ ብለህ የአባትህን ሞት ለማኝ አትሁን፡፡ ተጣጥረህ በግንባርህ ወዝ በልፅግ እንጂ የምኞት አቋራጭ መንገድ ለማግኘት አትፍጨርጨር!
አባትህ መመኪያህ ነው፡፡ አባትህ ማዕረግህ ነው፡፡ አባትህ ማስፈራሪያህ ነው፡፡ አባትህ የኋላ ታሪክ ያለው ስለሆነ፤ ባላንጣዎችህ ሁሉ በእሱ ዐይን ስለሚያዩህ፣ እሱ በመኖሩ እንደተከበርክ ትኖራለህ! ድንበርህን አይሻገሩም! አጥርህን አይነቀንቁም! አጋር - አልባ አድርገው አያዩህም! አባትህ ከአልጋ በዋለ ማግሥት፣ በአልጋው ዙሪያ የሚያሴሩትን የወዳጅ ጠላቶች አስተውል፡፡ ከሀሰተኛ ወዳጆች ይልቅ ዕውነተኛ ጠላቶች ያጠነክሩሃል። ቁርጥህን አውቀህ፣ አንጀትህን አስረህ እንድትጓዝ ያደርጉሃል፡፡ ህዝብህን አትናቅ፡፡ አዳምጥ፡፡ በራስህ ተማምነህ፣ በሁለት እግርህ ቆመህ፣ አገርህን በትክክል እንድትመራ፣ የህዝብ ፍቅር ያስፈልግሃል! የህዝብ ድጋፍ ያስፈልግሃል!!” አለው፡፡
ልጅየው ምክሩን ከሰማ በኋላ ወደ ፀሎት ቤቱ ገባና፤
“አምላኬ ሆይ! አባቴን አቆይልኝ! የህዝብን ፍቅርም እንዳገኝ እርዳኝ” ሲል ፀለየ!!
*      *     *
ያለ አበው ምክር፣ ያለ ህዝብ ድጋፍ የትም አይደረስም! የህዝብ ምሬት መጠራቀም የለበትም! “ሳይቃጠል በቅጠል” የሚለውን ብሂል አለመርሳት ተገቢ ነው፡፡ በትንሽ በትልቁ አለመረበሽ፣ አለመሸበር ትልቅ ጥበብ ነው! ትዕግስት ማጣትና ፈጥኖ ወደ እርምጃ መሄድ አደገኛ ነው፡፡ “ችኩል ጅብ ቀንድ ይነክሳል” የሚለውን ተረት ከልብ ማስተዋል ነው፡፡ ከዚህ አልፎ ማስፈራራት ቅኝቱን የለወጠ እለት፣ ለአንባ-ገነንነት ቦይ ይቀዳል። ዲሞክራሲን ያቀጭጫል፡፡ “ስለ ዲሞክራሲ ማዳነቅና ህዝቡን ፀጥ ማሰኘት ቧልታዊ ድራማ ነው፡፡ ስለ ሰብአዊነት እያወሩ ህዝቡን ግን መቃወም ሐሳዊነት ነው” ይለናል፤ ፖል ፍራየሬ የተባለው የፖለቲካ ፀሐፊ፡፡ የቀን ትጋትም ሆነ የሌሊት መልካም እንቅልፍ የሚገኘው አገር ሰላም ስትሆን ነው፡፡ አገርን ሰላም ለማግኘት ህዝባዊ ተሳትፎን ማጎልበት ግድ ነው፡፡ የአበው ምክርና የአዲስ ትውልድ ቅንጅትና ውህደት ከሌላ ወደመጣንበት እንመለስና፣ የውሃ ቅዳ ውሃ መልስ አታካች ሂደት መጫወቻ እንሆናለን! “መካር የሌላው ንጉሥ” የምንለውን ያህል፣ የተሳሳተ መካሪ እንደሚያቀልጠንም እናስብ! እርቅና መግባባት ከብዙ ጣጣ ያድናል፡፡ ሆድ ለሆድ ሳንቻቻል፣ አብረን እየተራመድን ነው ብንል፣ የለበጣ መንገድ ይሆናል፡፡ መንገዱ የአገራችንን ችግር ያህል ረጅም ነው!
አገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሙያዊ ብቃትን ትሻለች፡፡ ህንፃና መንገድ ብንሰራም የሰው ኃይላችን ያልሰለጠነ ከሆነ  ዋጋ የለንም፡፡ የሰው ኃይላችን አደረጃጀት የተሳካ እንዲሆን ለሰው ብቃት የምንሰጠው ክብር እጅግ ወሳኝ ነው! ቀና ውድድር እንጂ የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ መቀናናት ውስጥ ከገባን፤ ውለን አድረን መናናቅና መደፋፈ ርጋ እንደርሳለን፡፡ መከቧርን፣ አለቃን ማክበርን፣ አመራርን ማክበርን፣ ሥርዓትን ማክበርን፤ አዋቂን ማክበርን፣ ለሚበልጡን ቅድሚያ መስጠትን እንተውና ትልቅና ትንሽ ይጠፋል፡፡ ሥርዓተ-አልበኝነት ይስፋፋል፡፡ የላቀውን ማኮሰስ፣ በስሜት ብቻ መነዳት፣ በጊዜያዊ ሞቅ ሞቅ ብቻ ዘራፍ ማለት ይከተላል፡፡ “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” ይኼው ነው፡፡
Read 5302 times