Sunday, 20 August 2017 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን ወርቁ
Rate this item
(4 votes)

   “ጅማ ነቄ ብላለች”
                           
        ማሰብ የጀመረች ከተማ … ጅማ
.. እንዳኮረፍሽ እንዳትቀሪ
ሳቅ በዋዛ አይገኝም፣
አንቺ ባትመጪ እኔ አልሄድም
‹ፍቅር ሞተ› አይሰኝም፡፡
በድኔ እንጂ አብሮኝ ያለ
ምስኪን ልቤ እዛው ቀርቷል፣
ድም! ድም! ባለ ቁጥር
እዚህ ስቅ፣ ስቅ ይለኛል፡፡
“ሄሎ ጅማ!”
ዝም
“የኔ ቆንጆ”
ሳቀች፡፡
“አለሽ?”
“በደንብ ነዋ!”
“መኖርሽን እንዴት አወቅሽ?”
“ስለማስብ”
“እ…”
“cogito ergo sum”
ጅማ በሯን ዘግታ፣ ቄጠማዋን ጎዝጉዛ፣ እጣኗን አጢሳ፣ ቡናዋን አፍልታ ፈርሻለች፡፤ … “ዱአ” ነገር!!
በኋላ ቀር አስተሳሰብ፣ በኋላ ቀር “ባህል”፣ ወግና ልማድ በተተበተበ ማህበረሰብ ውስጥ ቀና ብለው የሚራመዱ ወይ በራሳቸው የቆሙ አስተዋይ ግለሰቦች ብቅ፣ ብቅ በሚሉበት ጊዜ “አፈንጋጭ፣ ከጊዜው የቀደመ” ከመባል አልፎ፣ መጥፎ ስም እየተለጠፈባቸው እንዲጎዱ፣ እንዲገለሉ ሲደረግ እንደታየው፣ ዝነኛና የነቁ ከተሞችን የሃሜት  “ታፔላ” በመለጠፍ፣ ለሌሎች ዕኩዮቻቸው የሚደረግ የ “ሀሳብና የማቴሪያል ድጋፍ በመንፈግ፤ ኢንቨስትመንት የመሳብ ነፃነት በማሳጣት እንዲሁም ነዋሪዎቻቸው ለከተማቸው ትልቅነት እንዳይተጉ ፍትሃዊ የአስተዳደር ስርዓትን በማስተጓጎልና ዕድገታቸው እንዲጫጫና እንዲጓተት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተፅዕኖ ሲደረግ እናውቃለን፡፡
“…. ይቺን ይቺንም ያላወቀ፣
በሞተ ፈረስ ካልሆነ .
መቼም በተስፋው አልዘለቀ፡፡”
ያለው ማ ነበር?
የዚህ ከንቱ “ሤራ” ሰለባ ከሆኑ የአገራችን ከተሞች አንዷ ጅማ ናት፡፡ ጅማን ለምን “defame” ማድረግ አስፈለገ? ወይም እነሱ እንደሚሉት ጅማ ለምን “cornered” ሆነች?
“… አሮጌው ባዲስ እንዲተካ
አዲሱ አሮጌ ይሆናል፣
ይህ የማይቀር ጉዳይ ሁኖ
ቀን በቀን ይገለበጣል፡፡”
የተባለውን ዘንግተውት፡- ጅማ ስትደበዝዝ እነሱ ሊደምቁ፣ ጅማ ስትጨልም እነሱ “ቦግ” ሊሉ፣ ጅማ ወደ ኋላ ስትቀር እነሱ አድገውና ሰልጥነው ሊስቁባት፣ ሊዘባበቱባት በመፈለጋቸው ነው፡፡ … ምክንያቱም፡-
ጅማ በአስፋልት መጥረጊያ በሚፀዱ ጎዳናዎቿ የሌዬኔን አይስክሬም እየላሰች፣ አፕሏን እየገመጠች እንደ ለንደኑ ሪቨር ቴምስ በልቧ መሃል በሚያቋርጠው አዌቱ ወንዝ መናፈሻ ሽር ብትን የምትል፣ ዕንቅልፍ ያልነበራት፣ ሮማንቲክ ከተማ መሆኗ፣ ዛሬ የ “ልባችን ደረሰ” ብለው ለሚያስቡ “ባላገሮች” ቅናት ነበር፡፡
ጅማ አውሮፕላን ብርቅ በነበረበት ጊዜ “አለም አቀፍ” አውሮፕላን ማረፊያ ነበራት፡፡ ያኔ ከጥቂት ያገራችን ከተሞች በስተቀር በሌሎች ብዙ ቦታዎች የሚኖሩ አጎቶቻችን አክስቶቻችን ከፍታ ቦታ ላይ እየወጡ “ይኸ አሞራ ነው፣ ይኸ “አየር” ነው” እያሉ ውርርዶሽ ይጫወቱ ነበር፡፡ ጅማ የራሷን አውሮፕላን ለመግዛት፣ ብር በጆንያ ሞልታ፣ ንጉሡን ለማስፈቀድ አዲስ አበባ ብትመጣ “…. እ..ከ..ከ..ከ..ከ እንዴት ጠገብሽ፣ ዛሬ አውሮፕላን ልግዛ ያልሽኝ ነገ አዌቱ ላይ የሚንሸራሸር “መርከብ” እፈልጋለሁ ልትይ ነው” ብለው “ተቆጡ” (ቀለዱ) … “… ለማንም ብሩን እንፈልገዋለን… ጆንያሽን ግን ውሰጂ፣ ጆንያ ለቡና መሰብሰቢያ እንጂ ለብር ማስቀመጫ አይሆንም፡፡ ለብሩ ባንክ እናቋቁምልሻለን፡፡” ብለው አሰናበቷት። እንዳትሉም የራሳቸው ሱቆች፣ ሆቴሎች፣ ፀጉር ማስተካከያ ቤቶች፣ የፎቶግራፍ ስቱዲዮዎች፣ የጦር መሳሪያ መሸጫዎችና የመሳሰሉትን ያካተተ ሁለት ትልልቅ ባንኮች ተቋቋሙ፡፡ .. የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና አዲስ አበባ ባንክ፡፡
ጅማ በአንበሳ የከተማ አውቶብሶች ስትንሸራሸር፣ ከሁለት የአገራችን ከተሞች በስተቀር ሌሎቹ በጋሪና በእግር፣ በአህያ፣ በበቅሎና በፈረስ ነበር አደባባዮቻቸውን የሚያደምቁት፡፡ ጅማ የለስላሳ መጠጥ (ተፈሪ ሻረው አረንቻታ) ፋብሪካ በነበራት ጊዜ ከጥቂት “ከተማዎች በስተቀር በሌሎች ብዙ ቦታዎች የሚኖሩት ዘመዶቻችን አረቄና ጠላ ነበር የሚጠጡት፤ … ግፋ ቢል ጠጅ፡፡
ጅማ ሁለት ሲኒማ ቤቶች (ሲኒማ ኢትዮጵያ፣ ሲኒማ ጅማ ወይም (ቀ.ኃ.ሥ) እና ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ (ጊቤ) ሲኖራት፣ በሌሎች ብዙ ቦታዎች እንኳን ሲኒማ ሊታይ የእድርና የመሳሰሉት ስብሰባ እንኳ የሚደረገው ሜዳ ላይ፣ ዛፍ ጥላ ስር ነበር፡፡ … ግፋ ቢልም የት/ቤት አዳራሽ ውስጥ!!
በነዚህ የሲኒማ ቤቶችና አዳራሾችም አሉ የሚባሉት የሙዚቃ ባንዶችና የቴአትር ክለቦች ምርጥ ሲምፎኒ ሙዚቃዎችንና ቴአትሮችን በየጊዜው እያቀረቡ ሲያስደስቷት ብር ብቻ አልነበረም አሸክማ የምትሸኛቸው … የመኪና ቁልፍም ትሸልማቸው ነበር፡፡ … እነ መሃሙድ ይመስክሩ!!
ጅማ በናይት ክለቦቿ፣ በሻይ ቤቶቿ፣ በት/ቤት ክበቦቿ፣ በእነ ጀምስ ብራውን፣ ዊልሰን ፒኬት፣ ፍራንክ ሴናትራ፣ ጂም ሪቭስ፣ አሪታ ፍራንክሊን፣ ኤዲት ፒያር፣ ኤታ ጄምስና በመሳሰሉት ሙዚቃዎች ታንጎና ማሪንጌ፣ ትዊስትና ቯልስ፣ ጀርክና… ዘሆርስ በምትጨፍርበት ጊዜ ዛሬ የሚሳደቡት ዘመዶቻችን ለአዝማሪ ግጥም እየሰጡ ነበር የሚዝናኑት፡፡
ጅማ ከት/ቤት መፃሕፍ ቤቶቿ (School libraries) በተጨማሪ የህዝብ (Public) መጽሐፍት ቤትና አሜሪካን መጻሕፍት ቤቶች ነበሯት፡፡ ጅማ፤ ኒውስዊክ፣ ታይምስ፣ አፍሪካን ኮንፌደንሻልና ኢኮኖሚስት በምታነብበት ጊዜ፣ በሌሎች ብዙ ከተሞች ከአዲስ ዘመን፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ወይም ኢትዮጵያን ሄራልድ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም።
ጅማ አለማቀፋዊ መንፈስ ያላት ከተማ ናት፡፡ ነዋሪዎቿም የከተማዋ ጌጦች ናቸው፡፡ የማንኛውም አገር ዜጋ ብትሆን፣ እዛው ተወልደህ እዛው ብታድግ፣ ቅድም ከአውቶብስ ወይ ከአውሮፕላን ወርደህ ብትቀላቀል … ልዩነት የለውም፡፡ … አንዴ እግርህ መሬት ይርገጥ ብቻ!!
“ከተማ ሲያረጅ ጅማን ይመስላል” እያሉ የሚያሽሟጥጧት፣ እንደ ጅማ ኋላ ያስቀረኝ እያሉ የሚማማሉባት፣ ወገባቸውን ይዘው እየተንጠራሩ የሚዘንጡባትና “cornered” አረግናት እያሉ የሚዘባበቱባት ስልጡን መሳይ “ባላገሮች”፣ ያኔ “ፋራዎች” ነበሩ፡፡
ጅማ ዛሬ “ነቄ” ብላለች፣ በራሷ መቆም ጀምራለች፣ የሌለ ነገር አትጠብቅም (no more ‘waiting for godot’)፤ አዳዲስ የእግር ኳስ ክለቦች አደራጅታለች። ጅማ አባቡናና ጅማ ከነማ፣ ተስፋ የሚጣልባቸው ቡድኖች ናቸው። ለአደረጃጀቱና ለአሰልጣኞቹ ምስጋና ይድረስ፡፡ በሆቴል ኢንዱስትሪውም ትልልቅ ፕሮጀክቶች ብቅ፣ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በEBS የተመለከትነው ሲኒማ ቤት ያለው ሆቴል እልልል! ያሰኛል፡፡ በእርግጥ ጅማ “ማሰብ” ጀምራለች፡፡ “ከመቅረት መዘግየት” (Better late than never) ይባላል፡፡

Read 1617 times