Error
  • The RokSprocket Module needs the RokSprocket Component enabled.
Saturday, 07 April 2012 08:53

ቢጫ ለባሾችና ‘ነጭ ለባሾች’ (ቅኔ የለበትም)…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ዝናቡ ትንሽ አቀዘቀዘንማ! ቢያንስ፣ ቢያንስ “ለከርሞ የሚላስ የሚቀመስ ባይጠፋ ምን አለ በለኝ…” ምናምን የሚለውን ‘ሆረር’ ትንሽ እንኳን ቢቀንስልን፡፡

ስሙኝማ…እሁድ ዕለት ትንሽ ዘና አልንማ!

የምር ግን… አንዳንድ ኳስ አገፋፎች ስመለከት ምን አልኩ መሰላችሁ… ልክ እንደ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኝ ‘የኳስ አጨዋወት ቴክኒክ’ ተገኝቷል፡፡ ልክ ነዋ…አላያችኋትም አንዳንዴ ኳሷ ‘በቀላሉ አልገፋም’ እያለች ሾልካ ከተጫዋቾች ጀርባ ስትሄድ!

እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… መቼም የእኛ አገር ነገር፣ ‘ማሟሟቅ’ እንችለበት የለ… የቦሶቻችንን ቡድን የከበበውን ካሜራ ብዛት አያችሁልኝ! እኔማ… አለ አይደል… ቀኑ ‘አፕሪል ዘ ፉል’ ነበር አይደል… ሜሲን፣ ወይ ሮናልዶን የሚመስል ሰው ብቅ ሊያደርጉ ይሆን እንዴ ብዬ ነበር፡፡ ይኸውላችሁ፣ ነገራችን እንዲህ ነው… ሞቅ ባለ ወንበር ወይሞ ዳጎስ ባለ ‘ኪስ’ ዙሪያ የ“እቤን እዩኝ…” ትርምስ፡፡ እናላችሁ ከአንጀቱ በሙያው የሚሮጥ እንዳለ ሁሉ… አለ አይደል… ፈረንጆች “ኋት’ዝ ኢን ኢት ፎር ሚ” የራሳችንን ትርፍና ኪሳራ የምናስብ መአት ነን፡፡

‘አርቲስቶች’ ሆዬ አስተዋሽ አጥተው “አድናቂህ ነኝ…” የለ፣ “ፈርምልኝ…” የለ…“ያ እኮ የእኛ ሰው በአዲስ አበባ ስታዲየም ፊልም ላይ የሚሠራው” ምናምን አይነት መጠቋቆም የለ…መቼም አልዋሽም፣ የአፄ ምኒሊክ ሐውልት ራሱ የሚያውቃቸው የሚመስላቸው ‘አርቲስቶች’ እንደዛ ‘ኢግኖር’ ሲደረጉ ለጥቂት ደቂቃ ቅር አስኝቶኛል፡፡

ስሙኝማ… እንግዲህ በተለያዩ ቦሶች እንበሽቅ የለ… አንዳንዶች ጉዳይ አልጨርስ ብሎ  ያስቸገራቸውን ባለስልጣን እያዩ ምን ይሉ ይመስለኛል መሰላችሁ…“ምነው ወለም ብሎት ሦስት ወር ጄሶ በገባለትና ምክትሉ ጉዳዬን በጨረሰልኝ…” ‘ያልተጻፈ ሲያስነብበን’ እኮ እንዲሁ ነው!

እኔ የምለው… ይሄ የውጪ ኳስ የቴሌቪዥን ‘ሪፕሌይ’ ጉድ አደረገን እኮ…በተሳሳተ የተተረጎመ ሲመስለንስ! ለግንዛቤ ያህል… በቲቪ የምናየው ‘ስሎው ሞሽን’ ጨዋታ የካሜራ ሥራ ነው እንጂ እስካሁን ፊፋ ህግ ውስጥ የለም፡፡ አሀ… ከሁለቱም ወገን አንዳንድ ተጫዋቾች በ‘ስሎው ሞሽን’ ሲጫወቱ የፊፋ አሥራ ስምንተኛው ምናምን ህግ ሊመስል ምንም አልቀረውም ነበራ! እንደውም የእኛዎቹ ቲቪዎች ሪፕሌይ ያልደጋገሙት ‘ስሎው ሞሽን’ ጨዋታን እንዴት እንደገና በ‘ስሎው ሞሽን’ አንደሚያሳዩ ግራ ገብቷቸው ይመስለኛል፡፡ ሀሳብ አለን… ‘ስሎው ሞሽኑ’ ከየቢሮው ተባሮ ይውጣልንና እንዲህ ኳስ ሜዳ ወዳጅነት ጨዋታ ላይ ብቻ ይቅርልን፡፡ (ወዳጄ “ወር ከአሥራ አምስት ቀን ቀጠሩኝ” ነው ያልከኝ!)

ስሙኝማ… ለሌላው ጊዜ ፊፋ ጣልቃ ሳይገባብን እኛው የአገሪቱን ሁኔታዎች ያገናዘቡ ህጎች ብናወጣ አሪፍ ነው፡፡ ለምሳሌ…የቦሶችን ቡድን በሚመለከት በቀረባቸው (‘በል ባላቸው’) ጎል ላይ እንዲያገቡ ቢፈቀድ! አሀ… ልክ ነዋ…እኛ ስንት ነገር “በል ስላለው ነው እንዲህ የወሰነብኝ…” እያልን እንበሳጭ የለ! ስለዚህ ‘በል ሲል’ አስቀድመው የሚታዩት ምልክቶች ምን እንደሆኑ እኛም ስለምናይ የቀረበው ጎል ላይ አግብተው ለቡድኑም ባይሆን ለግላቸው ለእሱ ይቆጠርላቸውማ!

ቅሬታ አለን… ደህና ታክል የሌለበት፣ “ቁርጭምትሚቴን!” ብሎ ተጫዋች ሜዳ ላይ የማይንፈራፈርበት፣ ለኳስ ሲዘሉ ክርን ምናምን የሌለበት ኳስ ትንሽ ፓሺኑ ቀነስ አለብን ልበል! አሀ…የፈለገ ወዳጅነት ቢሆንስ! (እንደውም ዘንድሮ ‘ደመ መራራነት’ የሚብሰው ወዳጅነቱ ቅርብ ነው በሚባልበት ሆኗል፡፡)  እኔማ በቃ “ካልጠገቡ አይሰበሩ…” የምትለዋን ተረት ለመጠቀሚያ የሚሆን ነገር ስላጣሁ እንዳልተመቸኝ ብደብቅ ጡር ይሆንብኛል፡፡

ስሙኝማ… እግረ መንገዴን ተቀይረው ገብተው ብዙም ሳይቆዩ ተቀይረው የወጡት… ምክንያቱ አልተገለጸልንም! …ግን የ‘ትንፋሽ እጥረት’ ሊሆን ይችላል ብለን እንጠረጥራለን፡፡ እናላችሁ… ህዝቤም እኮ “ከዚህ ላይ ይህን ያህል አምጣ፣” “ከዚያች ላይ ይህን ያህል አምጣ፣” ሲባል እንዲሁ ‘ትንፋሽ እንደሚያጥረው’ ግንዛቤ ይግባልንማ!

ስሙኝማ…ምን ግራ ገባህ አትሉኝም…ይሄ የማልያ ቀለም አመራረጥ! የቦሶቻችን ማሊያ አሪፍ ነው፡፡ (አንድዬ ቀለሞቹ የያዙትን መንፈስ በዛው ይበልጥ ጠለቅ አድርጎ ያስርጽልንማ!) የ‘አርቲስቶች’ አረንጓዴ ጣል ያለበት ነጭ ማሊያ ለአጠራር አስቸገረንማ! ቦሶችን “ቢጫ ለባሽ” ማለት ይቻላል… ‘አርቲስቶቹን’ ግን “ነጭ ለባሾች” ስንል ቀይ መብራት ምናምን ጥሰን እንዳንሄድ ብዬ ነዋ! ለነገሩ እነሱ በመረጡት ቀለም እኛ ምን አገባን! ነጭ መረጡ… “ነጭ ለባሾች” ተባሉ፡፡ ‘ፉልስቶፕ!’

የምር ግን… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… መጀመሪያ ‘አርቲስቶች’ ቢያንስ ወደ ባንዲራ የተጠጋ ቀለም ያልለበሱት ነገርዬው እንዴት ነው… የእነሱ ‘ፓትሪዮቲዝም’ ምናምን ጥያቄ ውስጥ ገብቷል እንዴ! ስጋት ገባና… ወይስ ነገርዬው “እናንተ ከሁሉም ትለምዳላችሁ” ነው! ደግሞላችሁ…ሌላ ነገር፣ ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር ካሜራዎቹ አንድም ጊዜ የ‘አርቲስቶቹን’… አለ አይደል… ‘ክሎዝ አፕ’ ነገር ያለማሳየታቸው…ብቻ እኛ ደስ ያላሉን ነገሮች እንዳሉ ግንዛቤ ይግባልንማ!

ስሙኝማ… ጨዋታ መሆኑ ካልቀረ ሀሳብ አለን…ለወደፊት ‘አርቲስቶች’ እርስ በእርስ ይጋጠሙልን፡፡ ለአንድ ወር ያህል ከንፈር የምንመጥበትም ቂ…ቂ… የምንልበትም እናገኝ ነበራ! የሚያሳስበን ነገር ቢኖር የአምቡላንሶች እጥረት ሊፈጠር መቻሉ ነው፡፡ አንድ፣ ሁለቱ ‘አርቲስቶች’ የሄሊኮፕተር አምቡላንስ ባያስፈልጋቸው ነው!

እናላችሁ… በአሁኑ ጊዜ በ‘አርቲስቶች’ መንደር ያለውን የእርስ በእርስ መናናቅና… አለ አይደል… “እሱ ብሎ የፊልም ጽሁፍ ጸሀፊ…ማመልከቻ እንኳን ከፍሎ ሲያጽፍ አናውቀውምና ነው!”፣ “አይ ኢትዮጵያ፣ እሷም ፊልም ዳይሬክተር ትባል! እንዲህ ይቀለድብን እንጂ!” ማለት በበዛበት እርስ በእርስ ሲጫወቱ ለአንዳንዶቹ ቀይ ካርድ ማሳየት ብቻ ሳይሆን ኳስ ሜዳ ዝር እንዳይሉ መተማመኛ ማስፈረም ባያስፈልጋቸው ነው! (ስሙኝማ… የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… የማልያ ‘ንክኪ’ ቀይ እንደሚያሰጥ በቀደም ለመጀመሪያ ጊዜ አየን፡፡ ምነዋ ነገርዬው ሀሳብ የማይጥል! አሀ… ለ‘ንክኪ’ ቀይ የሚሰጥ ከሆነማ…ብቻ ተዉት!)

በነገራችን ላይ… የ‘አርቲስቶቹን’ ሀኪሞች በተግባር ወይም የቡድን ወንበር ላይ ተቀምጠው ባለማየታችን ቅር ብሎናል፡፡ ካሜራዎቹ እነሱን የመሰሉ አሪፎች ማግኘት አቅቷቸው ነው!… ይሄ ነጭ ማሊያ እንዴት እንደጎዳን አያችሁልኝማ!

እግረ መንገዴን…ከቢጫ ለባሾቹ ለብሔራዊ በድን ቢያንስ አንድ ተጫዋች በቋሚነት፣ አንድ በተጠባባቂነት መጠቆም ይቻላል፡፡ “ባሉበት ወንበር እናቆያቸው ወይስ ወደ ብሔራዊ ቡድን እንላካቸው…” የሚል ‘ኦፒኒየን ፖል’ ምናምን ይካሄድልንማ!

በነገራችን ላይ ቢጫ ለባሾች… አንድ ሁለት ተጫዋች ከሸወዱ በኋላ ኳስ የሚነጠቁት ለምን እንደሚመስለኝ ታውቃላችሁ…ብዙ ጊዜ መሸወድ የሚቻለው አንድ ሁለቴ ብቻ ነዋ! አሀ… ዘንድሮ ‘ነቄ’ ለማለት ጊዜ አይፈጅማ! አንድ ጊዜ ቅዝምዝሙ አቅጣጫውን ካየን ብንሸወድም በፈቃደኝነት (በአቅም ማነስ ማለትም ይቻላል) ይሆናል፡፡

እኔ የምለው… የምር ግን ቢጫ ለባሾች በራቸውን በንቃት መጠበቅ አለመቻላቸው አሳስቦናል፡፡ ‘አርቲስቶች’ እንደልብ ተመላለሱበት እኮ! (“አይደለም የኳስ ሜዳ በር… ዘንድሮ ለብዙዎቻችን ዝግ ሆነው የቆዩ በሮች ለ‘አርቲስቶች’ እንደልብ ክፍት እየሆኑ ነው…” የምትሉ ሰዎች ‘ኤቪደንሳችሁን’ ቴክስት አድርጉልኝማ!) እናላችሁ… በሚቀጥለው ጊዜ የቦሶቻችን ግብ ወይ ጠበብ እንዲልላቸው፣ ወይም ቢያንስ ግማሹ ላይ የግቢ አይነት የብረት አጥር እንዲደረግላቸው በዜግነት መንፈስ ሀሳብ እናቀርባለን፡፡

እናላችሁ…የበር ነገር ካነሳን አይቀር… ለምንድነው የደንብ ማስከበር ተወካዮች በተከላካይ ቦታ ያልተሰለፉት! ልክ ነዋ… እንደ ባለስልጣን የሚያደርጋቸው ደንብ ማስከበሮች መአት አሏ! ልጄ…ኳሱ እንኳን ባይቻል… የመጥረጊያ ስባሪም ቢሆን ይዞ “በዚች በኩል ውልፍት እላለሁ ብትል ዶሮ ጠባቂ ነው የማደርግህ፣” ቢሉ ‘አርቲስቶቹ’ ከራሳቸው ፔናልቲ ክልል አይወጧትም ነበር፡፡ (እኔ የምለው…አንዳንድ ‘አርቲስቶች’ እንደ መጋጨት ምናምን ስትሞክሩ አየን ልበል! ሳይፈረምላችሁ የከረመ ደብዳቤ አለ…ወይስ ባላንስ መጠበቅ አቅቷችሁ ነው?)

በነገራችን ላይ… ሳልረሳው ስታዲዮሙ ገና መአት ያልሞላ ቦታ እያለውም “35 ሺህ ሰው…” እንደሚይዝ ያወቅሁት ገና በቀደም ነው! ይሄን ያህል ከኢንፎርሜሽን ርቄያለሁ ማለት ነው! ቂ…ቂ…ቂ… ደግሞላችሁ… ከተለያዩ አቅጣጫዎች ይነገሩ በነበሩት ነገሮች አላስፈላጊ ቅጽሎች ትንሽ የበዙ አልመሰላችሁም! (ወዳጄ ‘አስተዛዛቢ’ የሚለውን ቃል ነበር የተጠቀምከው?) ያውም በ‘ላይቭ’ ስርጭት!

እኔ የምለው… ‘አርቲስቶች’ የእውነት አሸነፍን ብላችሁ ‘ሲፕ’ ምናምን ስትሉ አምሽታችሁ እንዳይሆን! እንደሱ ካደረጋችሁ… የምር በፊልሙ ዘርፍ ልክ እንደ ሮማንቲክ ኮሜዲ “ፉትቦል ኮሜዲ” የሚል ዘርፍ ይጨመርልንማ! ያልተመጣጠነ ነገር ነዋ! ቢያንስ ብዙዎቻችሁ ገና ከድራፍት ሳትወጡ!…ልጄ፣ እንዴት ‘እንደሚፈላና እንደሚንተከተክ’ የት ታውቁታላችሁ! ለግንዛቤ ያህል… … አለ አይደል… “ሬድ፣” “ብላክ፣” “ብሉ፣” “ጎልድ፣” እየተባለ አብዮትም ባይሆን ‘ድሪንክዬው’ በቀለም ወደሚገለጽበት መደብ ስትደርሱ ያኔ ይገባችኋል፡፡

እኔ የምለው…ቡድኖቹ ሜዳ ከመግባታቸው በፊት የኃይል ሰጪ ስቴሮይድ ምናምን ምርመራ ተደርጓል እንዴ! አሀ…ህጉ ይፈቅዳላ! ምንም የላቦራቶር መሣሪያ፣ ‘ስቱልና ዩሪን ቴስት’፣ የደም ሳምፕል ቅብጥርስዮ አያስፈልግም፡፡ ምርመራው እንዴት መሆን ነበረበት መሰላችሁ…እያንዳንዱን ተጫዋች ጠጋ እንዲል አድርጎ “እስቲ ተንፍስ” ማለት፡፡ ‘ጉልበት ሰጪ’ ምናምን የምትደረግበትን ዘዴ አቋራጯን መች አጣናት! ስሙኝማ… የአንዳንድ ‘አርቲስቶችን’ ጥድፊያ ተመልክተንና ስምንት ሰዓት ማለፉን አይተን ለምን “ሰዓት ረፍዶባቸው ይሆናል…” ብለን ለምን እንዳላሰብን አይገርማችሁም! ቂ…ቂ…ቂ…

እኔ የምለው… ኳሷ ሆነ ብላ እግራቸውን እየፈለገች ለነካቻቸው ተጫዋቾች አድናቆታችን መግለጽ ያስፈልጋል፡፡ አሀ፣ ልክ ነዋ…ልጄ “እስኪ ኳሳን አምጪልኝ…” ተብላ በውስጥ ስልክ የምትጠራ ኤክስኪዩቲቭ ሴክሬተሪ በሌለችበት ኳሷ ‘የልብ አውቃ’ ሆና በ‘ራሷ ተነሳሽነት’ መምጣቷ የማያስደንቅንማ!

እግረ መንገዳችንን…የዕለቱ አርቢትር ከአቅም በታችም ከአቅም በላይም ለሚጫወተው ቀይ ምናምን ብሎ ነበር፡፡ ለነገሩ ሁለቱም አልገጠሙትም፡፡ ይልቁንስ…ሜዳ ሲገባ ግን ‘አቅም ሳይኖራቸው’ ለሚጫወቱት የካርድ አይነት ያለመወሰኑ… አለ አይደል… “ወይ ቀድሞ አለማዘጋጀት” አሰኝቶናል! እኔ የምለው… ካርድ ሲወጣባችሁ ኳስ መምታት ምናምን አይነት ‘ፕሮቴስት’ ያሳያችሁት “ከአንጀታችን ነበር…” ብላችሁ ሲገርመን መስከረም እንዳይጠባ! እኔ ‘ሪኸርሳል’ ነው ባይ ነኝ፡፡ እናማ… በቢጫ ለባሾቹና በነጭ ለባሾቹ ግጥሚያ ዘና ብለነል፡፡ ለወደፊቱ በተለይ በቅርብ በተገኘው ግብ ላይ ማግባትና የቢጫ ለባሾች ግብ… አለ አይደል… ወይ እንዲጠብ ወይ የኢ.ሲ.ኤ. የአጥር በር  በውሰት እንዲገጠምለት ሀሳብ እናቀርባለን፡፡ የኳስ ሜዳው በር ጠቦ የየመሥሪያ ቤቱ በር ለሁላችንም እንደልብ ወለል ብሎ ተከፍቶ ያሳየንማ!

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

 

Read 2428 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 09:04