Saturday, 19 August 2017 13:08

ኤልቪስ ከሞተ ከ40 አመታት በኋላ 27 ሚ. ዶላር ገቢ አግኝቷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ባለፈው አመት 1 ሚሊዮን ኮፒ አልበም ተሸጦለታል

       ታዋቂው የሙዚቃ አቀንቃኝ ኤልቪስ ፕሪስሊ፤ ከዚህ አለም በሞት ከተለየ ባለፈው ረቡዕ 40 አመት እንደሞላው ያስታወሰው ቢቢሲ፣ ድምጻዊው ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 ብቻ 27 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ማግኘቱንና በአመቱ አንድ ሚሊዮን ያህል አልበሞች እንደተሸጡለት ዘግቧል፡፡
በተወለደ በ42 አመቱ እ.ኤ.አ በ1977 በልብ ድካም ከዚህ አለም በሞት የተለየው ኤልቪስ ፕሪስሊ፤ ዛሬም ድረስ ዝናው የማይቀዘቅዝ ዘመን አይሽሬ ድምጻዊ ነው ሲል የዘገበው ሎሳንጀለስ ታይምስ በበኩሉ፣ የሙዚቃ ስራዎቹም በዩቲዩብ ድረገጽ፣ ከ2.8 ቢሊዮን ጊዚያት በላይ እንደታዩለት አስታውቋል፡፡ ወደ ሙዚቃው አለም ከገባበት ጊዜ አንስቶ በድምሩ 197 ያህል የጎልድ፣ የፕላቲኒየምና የዲያመንድ ሽልማቶችን ያገኘው ኤልቪስ፣ በፖፕ የሙዚቃ ታሪክ ይህን ያህል ሽልማት በማግኘት ዛሬም ድረስ የሚስተካከለው ድምጻዊ እንደሌለም ዘገባው አመልክቷል፡፡ በስሙ የተለያዩ ተቋማትና የመዝናኛ ስፍራዎች እንደተቋቋሙለትና በመቶ ሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚያንቀሳቀሱ የጠቆመው የቢቢሲ ዘገባ በበኩሉ፣ ከእነዚህም መካከል በአሜሪካ ሜምፊስ የሚገኘውና በአመት ግማሽ ሚሊዮን ያህል ጎብኝዎችን በማስተናገድ ለኢኮኖሚው 150 ሚሊዮን ዶላር ያህል የሚያበረክተው ግሬስላንድ የተባለው መዝናኛ ስፍራ እንደሚጠቀስ አመልክቷል፡፡ የኤልቪስ አድናቂዎች ማስታወሻዎቹንና በስሙ የሚመረቱ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመሸጥ ዳጎስ ያለ ገቢ እያገኙ እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፣ የኤልቪስ ጌጣጌጦች፣ መጽሄቶች፣ መጽሃፍት፣ ቲሸርቶችና መነጽሮች በአለማቀፍና አገር አቀፍ ጨረታዎች በከፍተኛ ዋጋ እንደሚሸጡም አመልክቷል፡፡
ታዋቂው አለማቀፍ አጫራች ተቋም ኤቤይ፣ ደምበኞቹ ከኤልቪስ ፕሪስሊ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ቁሳቁሶችና ማስታወሻዎች ለመግዛት ያላቸው ፍላጎት ካለፉት ሶስት ወራት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ያስታወቀ ሲሆን በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በእያንዳንዱ ሰዓት 12 ያህል ከኤልቪስ ጋር ግንኙነት ያላቸው እቃዎችን መሸጡን አስታውቋል። ኤቤይ በአሁኑ ወቅት 70 ሺህ ያህል የኢልቪስ ማስታወሻዎችንና ከእሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለገዢዎች ማቅረቡንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1166 times