Sunday, 20 August 2017 00:00

“የጦቢያ ገጣሚያን” በጀርመን - በርሊን

Written by  የአፍታ ቆይታ-ከገጣሚ ምስራቅ ተረፈ ጋር)
Rate this item
(1 Vote)

  ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ 2009 ዓ.ም በጀርመን በርሊን፤ “Wax and Gold” (ሰምና ወርቅ) የተሰኘ ግጥም በጃዝ እና የሙዚቃ ኮንሰርት ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት ላይ ከኢትዮጵያ፣ ከዴንማርክ፣ ከአሜሪካ፣ ከስዊድንና ከሌሎች አለማት የተውጣጡ በርካታ ገጣሚያንና የሙዚቃ ተጫዋቾች፣
በበርሊን ከተማ የኪነ ጥበብ ስራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ከአገራችንም ገጣሚና ጋዜጠኛ ነቢይ መኮንን፣ እውቋ ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ፣ ሙዚቀኛ ጆርጋ መስፍን፣
ገጣሚ ፍሬዘር አድማሱ፣ ሰዓሊ ምህረት ከበደ የዋሸንት ባለሙያው ጣሰው ወንድሙ በርሊን ተገኝተው፣ ለዓለም አቀፍ የግጥምና ሙዚቃ አፍቃሪዎች
ሥራዎቻቸውን በማቅረብ ብዙዎችን ማስደመማቸውን ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡ ቆይታ እንዴት ነበር? ስራቸውንስ ለሌላው ዓለም በምን
ቋንቋ አቀረቡ? ከአዘጋጁ ድርጅት ጋር እንዴት ተገናኙ? ወደፊትስ ምን አስበዋል? በሚሉትና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በቅርቡ ከበርሊን ከተመለሰችው ከገጣሚ ምስራቅ ተረፈ ጋር የአፍታ ቆይታ አድርጋለች፡፡

       ጀርመን ተጋብዛችሁ ግጥም በጃዝ የማቅረብ ትግበራ እንዴት ተጀመረ?
ጀርመን አገር አንድ “ኤክስፐርመንት” የሚባል በኪነ-ጥበብ ላይ የሚሰራ ድርጅት አለ፡፡ ዋናው ባለቤቱ ታዋቂ አርክቴክት ነው፡፡ እዚህ ካሉ አርቲስቶች ጋር ይሰራል፡፡ ስራዎቻቸውን ወደ አገሩ እየወሰደ ለማሳየትም ይጥራል፡፡ አንድ ቀን በሆነ አጋጣሚ የእኛን ግጥም በጃዝ ተመለከተና በጣም ወደደው፡፡ ይሄ ሁሉ ተመልካች ያለው ግጥም በጃዝ አይተን አናውቅም በሚል አድናቆት ቸሩት። ከዚህ በፊት ሰዓሊ ምህረት ከበደ አብራቸው በስዕሉ ዘርፍ ትሰራ ነበር፡፡ በዚህስ አብረን ለምን አንሰራም የሚል ሀሳብ አመጡ፡፡ ምናልባትም ሀሳቡን ያነሳችው ምህረት ትመስለኛለች፡፡ ከዚያ በኋላ ግንኙነቱ ተጀመረ። ያው ዘንድሮ እነሱም እየመጡ እኛም እየሄድን ስንሰራ፣ ለአምስተኛ ጊዜ ነው፡፡ እኛም ጀርመን ስንሄድ፣ ለሁለተኛ ጊዜያችን ነው፡፡
በዚህ ግጥም በጃዝ ኮንሰርት ላይ ከተለያዩ ዓለማት፣ ገጣሚያንና ሙዚቃ ተጫዋቾች ይመጣሉ፤ ግጥማችሁን እንዴት ነው የምታቀርቡት?
ትክክል ነው፤ ከበርካታ አገራት እንደኛው ገጣሚዎችና ሙዚቀኞች በዝግጅቱ ላይ ይታደማሉ፡፡ እኛ ግጥማችንን የምናቀርበው ግን በአማርኛ ነው፡፡ ግጥሞቻችን ወደ እንግሊዝኛና የተለያዩ ቋንቋዎች ይተረጎማሉ፡፡ ከታዳሚው ጋር ተግባብተን፣ በጣም ወደውን ትልቅ ሀገራዊ ስራ ሰርተን ነው የመጣነው፡፡ ዝግጅቱ በጣም ስለተለመደ ትኬት ራሱ ቶሎ ነው የሚያልቀው፡፡
ምን አይነት ይዘት ያላቸው ግጥሞችን ነው ያቀረባችሁት?
ማህበራዊና አገራዊ ሀሳብ ያላቸው፣ ፍቅርን የሚሰብኩ ግጥሞች ተመርጠው ነው የቀረቡት። በሙዚቃ፣ በድራማና በዋሽንት ነው ግጥሞቻችን ታጅበው፣ አገራችን ስትተዋወቅ የነበረው፡፡ ከዚህ ዋሽንት ተጫዋቹ ጣሰው ወንድምም አብሮን ተጉዞ ነበር፡፡ በጣም የተቀናጀ እጅግ ማራኪ ስራ ነው አቅርበን የመጣነው፡፡
በዝግጅቱ ላይ የዴንማርክ፣ የስዊድን፣ የአሜሪካና የሌሎችም አገራት አርቲስቶች ተሳትፈዋል፡፡ አጠቃላይ ቆይታችሁ ምን ይመስል ነበር? ከሌሎች አገራት ገጣሚዎች ጋር የነበራችሁ መስተጋብርስ?
ቆይታችን ለ15 ቀን ያህል ነበር፡፡ ወጪዎቻችን በእነሱ ነው የተሸፈኑት፡፡ እንደሄድን የግጥም መረጣ ስራ ነው የተከናወነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ወደ እንግሊዝኛና ወደ ጀርመንኛ እንዲተረጎሙ ማድረግ ሌላው ስራችን ሲሆን እነዚህን ግጥሞች ለእነሱ ማስጠናትና ማለማመድ፣ እኛም የእነሱን ወደ አማርኛ መተርጎም ዋና ዋናዎቹ ተግባሮቻችን ነበሩ፡፡ በዚህ ሂደትና ከሙዚቃ ጋር በመለማመድ፣ ስምንት ዘጠኝ ቀናት ወስዶብናል፡፡ እንደ ሆያ ሆዬ ያሉ ባህሎቻችንን የሚያስተዋውቁ ዘፈኖች፣ ሌሎችንም በደንብ ስናጠና ቆይተናል፡፡ መድረክ ላይ ስናቀርብ ለምሳሌ ሆያ ሆዬ ስንል፣ ሁሉም ታዳሚ ሆ ብሎ ይቀበለን ነበር፡፡ እኛ እንዲሉ እያደረግን ነበር የምናቀርበው፡፡የሚገርምሽ ከአንድ አገር የሄድነው እኛ አምስት ስለነበርን ቁጥራችን ህብረታችንን፣ ተቀባይነታችንን፣ በጣም አጉልቶልን ነበር፡፡ ሌሎቹ ከየአገራቸው አንድ አንድ ሆነው ነው የመጡት፡፡ ተፅዕኖ የፈጠርነውም እኛ ነን፡፡ ከሆያ ሆዬ በተጨማሪ ሌሎችንም የአገር ዜማዎች ስንጫወት፣ ቋንቋውን ባያውቁትም በጣም ተደስተው ነበር፡፡
በዝግጅቱ ላይ ሀበሾች ነበሩ?
በብዛት ሌሎች ዜጎች ናቸው የታደሙት፡፡ ሀበሾች ዘገዩ መሰለኝ ትኬት አላገኙም፡፡ በጣም ጥቂት ሀበሾች ናቸው የታደሙት፡፡ ከሀበሾቹ ይልቅ ከመቀመጫቸው እየተነሱ አድናቆት ሲቸሩን የነበሩት ሌሎች ዜጎች ናቸው። በጣም ደስ የሚል ስራ ነው የሰራነው፡፡
ከአዳራሽ ውጭ ታዳሚውን ስታገኙ አቀባበሉ ምን ይመስል ነበር?
አንዳንዶቹ ምን አሉ መሰለሽ? የምትሉትን ነገር ትርጉሙ ባይገባንም፣ ከቅንጅታችሁ ከምታደርጉት ነገርና ፊታችሁ ላይ ከሚታየው ስሜት የተነሳ እናለቅስ ነበር ብለውናል፡፡ በተለይ ስለ ባንዲራ በህብረት የሰራነው ነገር ነበር፡፡ ባንዲራ ባንይዝም በምልክት እንሰቅል ነበር። ስንሰቅል የሁላችንም አይን ወደ ባንዲራው ይሰቀላል። ስለ ባንዲራ በእንግሊዝኛ፣ በጀርመንኛ በሌላም ቋንቋ ተደርጎ ሁሉም ስሜቱን የገለፀበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ዜማ የፈጠርንበት ትርኢት ሁሉ ነበር፡፡ በኳየር ታጅበን፣ አንድ ግጥም እናነባለን፡፡ ከዚያ ለምሳሌ “ኻርት” የሚለውን ቃል አንድ ሰው “ኸርት” ሲል፣ ሌላው ሁለት ጊዜ “ኸርት ኸርት” ይላል፡፡ ሌላው ሶሰት ጊዜ፣ ሌላው አራት ጊዜ… ሲለው የሆነ የራሱ ዜማ ይፈጥር ስለነበር፣ ሁሉም ነው የተደሰተው፡፡ መሀል ገብተን “አበባየሁሽ” “ሆያሆዬ” እያልን፣ አቅላቸውን ነው ያሳጣናቸው፡፡ አይተውት የማያውቁት ትርዒት፣ በጣም የድራማ ይዘት ያለው ስለነበር መቼ ነው ዳግማችሁ የምትመጡት በማለት መጠየቅ ደረሱ፡፡ ይሄን ነገር ቦታው ላይ ሆነሽ ካላየሽው ለመግለፅ ራሱ ይከብዳል፡፡
ምን ያህል ትርኢቶችን አቀረባችሁ?
13 ያህል ትርኢቶችን አቅርበናል፡፡ ሁሉም የተለያዩና ማራኪ ነበሩ፡፡
ስለዚህ በቆይታችሁ ደስተኛ ነበራችሁ ማለት ነው?  
እኛም በጣም ደስተኛ ነበርን፣ እነሱም በጣም ተደስተው ነበር፤ ለዓመት የሚረሱን አይመስለኝም፡፡
ቀጣዩስ ጉዞ ደግሞ መቼ ነው?
በቀጣይ እነሱ ናቸው፤ ተረኞቹ፤ ይመጣሉ፡፡ በየዓመቱ ነው የሚካሄደው፤ አንዳንዴ በሁለት ዓመቱ ይካሄዳል፡፡ ከአመት በኋላ ሲመጡ እኛ እዚህ አዘጋጅተን እንጠብቃቸዋለን፡፡ እዚህ ሲመጡ ምን እናደርጋለን መሰለሽ… ሊታይልን ይገባል የምንላቸው ቦታዎች በመምረጥ፣ እዛ ቦታ ላይ ሄደን ነው ስራውን የምንሰራው።
በዚህ በኩል ከዚህ ቀደም የሰራችሁት ስራ አለ?
አዎ! ከዚህ ቀደም ከብሔራዊ አስጎብኚ ድርጅት (NTO) ጋር በመሆን ዝግጅቱ አዋሽ ፓርክ እንዲሰራ ተደርጓል፡፡ የውጭ ዜጎች ስለ አዋሽና በአዋሽ ስላሉ ነገሮች እንዲያውቁና እንዲጎበኙ ዕድል አግኝተዋል፡፡ እዛ ቦታ ለሁለት ቀን ነው የቆየነው፤ የምናድረው ድንኳን ውስጥ ነበር፤ በዚህ ዝግጅት የውጭዎቹን ጨምሮ ወደ 50 ሰው ተሳትፏል፡፡ አስጎብኚ ድርጅቱ ትራንስፖርት ምግብና ሌሎችን አስፈላጊ ነገሮች በማቅረብ ትልቅ ስራ ተሰርቷል። በቀጣይም ሲመጡ፣ የትኛውን ቦታ እናስጎብኝ የሚለው ላይ ተመካክረን እናዘጋጅና ታሪክንም ቅርስንም ባህልንም አናስተዋውቃለን፡፡
አዲሱ “ጨው በረንዳ” የግጥም መፅሀፍሽ እንዴት ነው?
በጣም አሪፍ ምላሽ እያገኘሁበት ነው፡፡ ሰው እየገዛ እያነበበ፣ አስተያየት እየሰጠኝ ነው፡፡ እኔ እንደዚህ ነኝ? እንድል አድርጎኛል፡፡ በጣም ደስተኛ ነኝ፣ አመሰግናለሁ!

Read 1498 times