Saturday, 19 August 2017 13:02

የባለስልጣኑ መጨረሻ

Written by  በሚኪያስ ጥ.
Rate this item
(7 votes)

ሥራ አስኪያጁ ናቸዉ፤የወቅቱን ዝርዝር የስራ አፈጻጸም ለወሬ መንታፊዎች እያቀበሉ ይገኛሉ፡፡
ስለ ሰዉየዉ የስራ ሃላፊነትና የኋላ ታሪክ ወደ መጨረሻ  ላይ በዝርዝር እንናገራለን፡፡ አሁን ወደ መግለጫዉ እንለፍ!
‹‹ባ’ሁኑ ዓመት፣መስሪያ ቤታችን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሌቦችን በቁጥጥር ስር አዉሏል፡፡ ‹ሌቦች› ስል፣ያዉ ይገባችኋል ብዬ ነዉ፤‹ሙሰኞች› ላለማለት ፈልጌ ነዉ፡፡ እናም፣እነዚህ ሌቦች መንግስትን ሲመዘብሩ ከርመዋል፡፡ ‹ለመንገድ ስራ› ተብሎ የተመደበዉን- በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ወደ ግል ካዝናቸዉ አስገብተዋል፡፡ በሌላ በኩል…እህህም!...››
ጉሮሯቸዉ ከመግለጫው ለአፍታም ቢሆን አናጠባቸው፡፡ እርሱን ለመሞረድ ደጋግመው፤ ‹‹እህህም…›› ማለት ነበረባቸው፡፡  ይህ ‹‹እህህም››ታ የመሞረድ ብቻ ሳይሆን የጉሮሮ ካንሰር ጭምርም ነዉ፡፡ ህመማቸዉ ሃገር ያወቀዉ ዕዉነታ ከሆነ ሰነባብቷል፤ሰዉዬዉ ‹‹ለህክምና›› ታይላንድ የመመላለሳቸዉ ነገር የአዘቦት ዜና ሆኖ፣ በየመገናኛ ብዙሃኑ ከተዘገበ ዉሎ አድሯል፡፡
‹‹..ይቅርታ! እነዚህ ሌቦችን ለመያዝ የበርካታ ወራትን ጥረት ለመክፈል ግድ ብሎናል፡፡ ምክንያቱም ሃሰተኛ የሂሳብ መረጃ ይጠቀማሉ፣እርስበ’ርሳቸዉ በnetwork የተቆላለፉ ናቸዉ፡፡ በ’ነዚህ ምክንያቶች እነርሱን ለመያዝ በጣሙን ተቸግረን ነበር››
ምላሳቸዉን ልክ እንደ ድመት አቆላምመዉ አወጡና ከንፈራቸዉን ደባበሱ፡፡
‹‹ከሌቦቹ የተገኘዉ ሃብት- ሙሉ በሙሉ- ወደ መንግስት ቋት እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በዚህ ሃሳብ አይግባችሁ! እኛ ለህዝቡ ታማኝ ነንና አትስጉ››
የዉሃ መያዣ ክዳን የሚያህሉትን አይኖቻቸዉን የከለለዉን መነጽር ወደ ዉስጥ ገፋ አደረጉት፡፡ የጉሮሮ ካንሰር ብቻ አይደለም በሽታቸው፡፡ የደም ግፊት ተደምሮባቸዋል፡፡ ሪህም አለባቸው፡፡ አዬ - አለመታደል!
‹‹…አሁን ወደ ሌቦቹና ወደ’ሚሰሩበት መስሪያ ቤት ስም ዝርዝር አልፋለሁ! በትዕግስት አዳምጡኝ!››
የ‹‹ሌባ›› ተብዬዎችን ዝርዝር በተዋረዳቸዉ ልክ ማንበብ ጀመሩ፡፡
የባለስልጣኑ ‹‹ስልጣን›› ሌባና ‹ነዉጠኛ› መንጥሮ አወጥቶ፣ ለ‹‹ህግ›› ማቅረብ ሲሆን በተፈረደባቸዉ ‹‹ሌቦች›› እና ‹‹ነዉጠኞች›› ላይ ‹‹ይቅር›› የማለትና የመፍታት ልዩ ስልጣን አላቸዉ፡፡ እዚህ’ጋ አንዳንድ ሰዎች ጥርጣሬ ይገባቸዋል፤‹‹በ’ዉነት፣እኚህ ሰዉዬ፣ በራሳቸዉ-አስበዉና አመዛዝነዉ ነዉ የሚወስኑት?›› ብለዉ ይጠይቃሉ፤እንደ ሌሎቹ፣እሳቸዉም የ‹‹መናፍስታኑ ተላላኪ›› ላለመሆናቸዉ ማስረጃ ስለሌለ! ‹‹መናፍስታኑ›› አይታወቄ ናቸዉ፡፡ ብዛታቸዉ ‹‹አስራ አምስት ነዉ!›› ይባላል፡፡ ሰዎቹ በግድያ፣ሰዉን እንደ በቅሎ በመስገርና በሌሎችም እኩይ ተግባሮቻቸዉ የዳበረ ዕዉቅና አላቸዉ።
…ዝርዝሩን ማንበባቸዉን ቀጥለዋል፡፡
እያነበቡ ሳለ፣መሃል ላይ አንድ አስደንጋጭ ነገር ገጠማቸዉ፤የራሳቸዉን ስም ባለማመን ስሜት አነበቡት-ሳያስተዉሉ፡፡
ወሬ አነፍናፊውም (ጋዜጠኛዉ)፣ ሰዉየዉም ተፋጠጡ፡፡
‹‹እንዴት እርስዎ ሌባ - አሳሪ ሆነዉ፣‹ሌባ› ሊባሉ ይችላሉን?›› አንዱ ወሬ አነፍናፊ፡፡
መልስ የለም!
‹‹ዘራፊዎችን ‹አስይዘናል› እያሉ፣እርስዎ እንዴት ዘራፊ ይሆናሉ?›› ሌላኛዉ ደገመ፡፡
መልስ የለም!
‹‹ያሳዝናል!...እንደዚህ ወራዳ ኖረዋል?›› ምስል-ቀራጩ፣ ጣቶቹን አጣጥፎ በምልክት እየሰደባቸዉ፡፡
አሁንም መልስ የለም!
ደም ግፊታቸዉ እየጨመረ መጣ፤አይናቸዉ በዉጋት ተሰበቀ፡፡ በወዝ ያጌጠዉ ወፍራም- ድፉጭ ፊታቸዉ በላቦት ተጥለቅልቆ ታየ፡፡
የካሜራዉና የጋዜጠኞቹ አይን እርሳቸዉ ላይ ተተክሏል- መልስ ፈልጎ፡፡
ባለስልጣኑ እንኳን መልስ ሊሰጡ ራሳቸዉንም መቆጣጠር አልቻሉም፡፡
ደም ግፊታቸዉ በአስደንጋጭ ፍጥነት እየጨመረ ነዉ፡፡
‹‹እነዚህ ሰዎች አልፈለጉኝም ማለት ነዉ›› በለሆሳስ ለራሳቸዉ አነበነቡ፡፡
እንዳልተፈለጉ ገባቸዉ፡፡
ልጓም-የለሹ ደም ግፊት አሸነፋቸዉ፣ሰዉነታቸዉ መዝለፍለፍ ጀመረ፡፡
‹‹..ኡፍፍፍፍ!...›› ሁሉም ነገር በአይናቸዉ ዙሪያ ይሽከረከራል፡፡
‹‹ክቡርነትዎ!...ክቡርነትዎ!›› ወሬ ሞጭላፊዎቹ አምባረቁባቸዉ፡፡
ሰዉየዉ አይሰማቸዉም፤ግን የጆሯቸዉ ታምቡር ላይ ‹‹ክቡርነትዎ›› ያናጥራል፡፡
‹‹ክቡርነትዎ!...ክቡርነትዎ!››
ጨለማ- አስፈሪ ጨለማ ዋጣቸዉ፤አይኖቻቸዉ ተከደኑ፡፡
…ከሳምንት በኋላ፣ከሰጠሙበት የሰመመን ዓለም ወጡ፡፡ በሰዉ ጥርቃሞ ተሞልቷል- ቤቱ፡፡
አዲስ ሆነባቸዉ፡፡
‹‹የት ነዉ ያለሁት?›› ራሳቸዉን ጠየቁ፡፡
አሁንም- አሁንም ክዳን መሳይ ዓይኖቻቸዉን ያሻሉ፤የሚያዩት ተዓምር ሆኖባቸዉ፡፡
ክፍሉ ጭልጭልታ ብርሃን በምትለግሰዉ አምፖል ሰበብ፣ግማሽ የጨለማ ከልና ግማሽ የብርሃን ጥለት ለብሷል፡፡ ወጣትና ሽማግሌ ሁሉ በየፍራሻቸዉ ተቀምጠዉ ያወጋሉ፡፡ አንዳንዱ ሸረኛ ፈገግታዉን ወደ’ርሳቸዉ ሲተኩስ፣ሌላኛዉ ደግሞ ዛቻ የተቀላቀለበት ጥቅሻ ይጠቅሳቸዋል፡፡
ግራ ተጋቡ፡፡
‹‹ኧረ፤ የት ነዉ ያለኹት?›› ልባቸዉን ጠየቁ፡፡
አይናቸዉን ሲያንቆራጥጡ፣አጠገባቸዉ የተቀመጠ ሸምገሎ አገኙ፡፡
‹‹አባት፤አሁን ያለኹት የት ነዉ?›› ጠየቁ፡፡
‹‹እስር ቤት ነዉ ያለኸዉ!›› መለሰላቸዉ፤በሻከረ ድምጽ፡፡
የ‹‹አንተ›› መባል ድንጋጤ አናወጣቸው፡፡
‹‹አንተ ተባልኩ?›› ተናደዱ፣‹‹እኔን ‹አንተ›?››
ግራ ገብቷቸዉ፣አሁንም አይናቸዉን አንቆራዘዙ፡፡ ሁሉም እንደ ቅድሙ ተቀምጦ፣ወሬዉን ይከካል፡፡
ድካም ቢጤ ተሰማቸዉና ጋደም አሉ፡፡
‹‹እፎይ!›› ተነፈሱ በረዥሙ፡፡
ለካ፣‹‹እፎይ›› ማለታቸዉ ሲተረጎም፣‹‹እነሆ ሩጫዬን ጨርሼያለሁ!›› እንደ ማለት ኖሯል?...
እዛዉ እንደተንጋለሉ አሸለቡ!!

Read 4041 times