Saturday, 19 August 2017 12:49

“ፕራክቲሲንግ አርክቴክቸር” ጉባኤና ኤግዚቢሽን ዛሬ ይጠናቀቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር ያዘጋጀውና ትላንት በተባበሩ መንግስታት የስብሰባ አዳራሽ የተከፈተው “Practicing Architecture” የተሰኘ ጉባኤና ኤግዚቢሽን ዛሬ ይጠናቀቃል፡፡ ማህበሩ የዓለምና የአፍሪካ አርክቴክቶች ማህበር አባል ሲሆን ከነዚህ ማህበራት ጋር የተለያዩ ግንኙነቶችን በመፍጠር፣ የአርክቴክት ሙያ በአገራችን እንዲዘምን እየተጋ  መሆኑ ተገልጿል፡፡
ማህበሩ የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት ከሚያደርጋቸው ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች አንዱ ዓመታዊ የሆነውን ጉባኤና ኤግዚቢሽን በቋሚነት ማዘጋጀት ሲሆን የዘንድሮውም “ፕራክቲሲንግ አርክቴክቸር” በሚል መሪ ቃል፣ ለ19ኛ ጊዜ መካሄዱን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በጉባኤው ላይ ሁለት ዋና ዋና የመወያያ ርዕሶች የተዘጋጁ ሲሆን ርዕሰ ጉዳዮቹም “Practicing as a Young Architect” እና “Architecture and Project Delivery Standards”   የተሰኙ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከውይይቶቹም በተጨማሪ በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች፤ ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁ ሲሆን በሙያቸው የላቀ አበርክቶ ላሳዩ ባለሙያዎችም ሽልማት እንደሚበረክት ታውቋል፡፡ ማህበሩ በዘንድሮው ጉባኤው፣ የአርክቴክቸር ሙያ ሂደት ውስጥ በአገራችን የህንፃ ግንባታ ላይ የሚገጥሙ ችግሮችንና መልካም አጋጣሚዎችን በመለየት፣ የሙያው ባለቤቶችና ባለድርሻ አካላት የሚመክሩበትና ወደተሻለ አሰራር የሚራመድበትን ሀሳቦች በማሰባሰብ፣ ከሚመለከታቸው አስፈፃሚ የመንግስት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለተግባራዊነቱ ጥረት የሚደረግበት መድረክ እንዲሆን መታሰቡም ተገልጿል፡፡ ዛሬ በሚጠናቀቀው ጉባኤ ላይ በርካታ አርክቴክቶች፣ ተጋባዥ የኮንስትራክሽን ዘርፍ የሙያ ማህበራት፣ የመንግስትና የግል ተቋማት ተወካዮች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተወካዮችና የዓለም አርክቴክቶች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንደተሳተፉበት ማህበሩ ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር፣ በ1984 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ላለፉት 25 ዓመታት በአገሪቱ የህንፃ ግንባታና የከተማ ልማት ላይ ሙያዊ አስተዋፅኦ ሲያበርክ ቆይቷል፡፡

Read 1125 times