Saturday, 19 August 2017 12:45

ዳሽን ባንክ፣ በባንኩ ሀዋላ ለሚጠቀሙ እድለኞች ሽልማት ሰጠ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 ባለ 1ኛ ዕጣ፣ 700 ሺህ ብር የሚያወጣ ኒሳን ተሸልሟል
                        
       ከግል ቀዳሚ ባንኮች አንዱ የሆነው ዳሽን ባንክ በባንኩ በኩል ከውጭ የሚላክላቸውን ገንዘብ ለሚቀበሉ እድለኞች ሽልማት ሰጠ፡፡ ለ3ኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ሽልማት መርሃ ግብር፤ አንደኛ ዕጣ የወጣለት ባለ ዕድል፣ ከ640-700 ሺህ ብር ግምት ያላት ኒሳን አሚራ የቤት አውቶሞቢል ተሸላሚ ሆኗል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት ለማሳደግ ከውጭ የሚላክላቸውን ገንዘብ ከዳሽን ባንክ እንዲወስዱ ማበረታቻ ሽልማቶችን በማዘጋጀት መስራት ከጀመረ ወዲህ በባንኩ ላይ ከፍተኛ ለውጦች መምጣታቸውን ያስታወቁት የባንኩ ማርኬቲንግ ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አለባቸው፣ ባንኩ ይህን መነሻ በማድረግ የሽልማቶቹን አይነትና ብዛት ለማሳደግ መወሰኑንና በዚህ ዙር ለአንደኛ ባለዕጣ መኪና መሸለሙን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ረፋድ ላይ በፍሬንድሺፕ ሆቴል በተካሄደው የሽልማት ስነ ስርዓት ባለ 1ኛ ዕጣ በጋምቤላ ክልል የፊኚዶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪና በጅማ ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዲግሪ የሊደርሺፕ ተማሪ የሆኑት አቶ ኦኬሎቻም አዲዮር የኒሳን አሚራ የቤት አውቶሞቢል አሸናፊ ሆነዋል፡፡ የሁለተኛ እጣ 12 ባለዕድሎች እያንዳንዳቸው ዘመናዊ ማቀዝቀዣ፣ 12 የ3ኛ እጣ ባለእድሎች ለእያንዳንዳቸው ኖት ቡክ ላፕቶፕ ኮሚፒዩተሮችን ለ24 የ4ኛ እጣ ባለዕድሎች ሶላር ፓኔሎች ሸልሟል፡፡
ተሸላሚዎቹ ከመጋቢት 18 ቀን 2009 እስከ ሰኔ 17 ቀን 2009 ዓ.ም በባንኩ በኩል ከውጭ የተላከላቸውን ገንዘብ የተቀበሉ እድለኞች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ አብዛኞቹ ተሸላሚዎች በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ቅርንጫፎች ገንዘብ የተቀበሉ ሲሆኑ የአንደኛ እጣ ባለዕድል ብቻ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን አቶ ሙሉጌታ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ባንኩ በ2016/17 የበጀት ዓመት ከሀዋላ፣ ከካርድ ክፍያ፣ ከስዊፍትና መሰል አገልግሎት 600 ሚ. ዶላር ማስገባቱ በዕለቱ ተገልጿል፡፡ ከ28 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ያለው ዳሽን ባንክ፤ ቅርንጫፎቹን ከ304 በላይ ማድረሱንና ከ1.5 ሚ. በላይ ደንበኞች ማፍራቱን የማርኬቲንግና ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬከተሩ ገልፀዋል፡፡ በሽልማት ስነ-ስርአቱ ላይ በብሔራዊ ሎተሪ የፈቃድ መስጠት ከፍተኛ ኦፊሰር ወ/ሮ ስምረት ገዛኸኝ፣ የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሄኖክ ከበደ እና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡

Read 1382 times