Error
  • The RokSprocket Module needs the RokSprocket Component enabled.
Saturday, 07 April 2012 08:47

ኢትዮጵያዊ መፈክሮች (Mottoዎች)

Written by  ተስፋዬ አለማየሁ
Rate this item
(0 votes)

በዘመን ደግም ይሁን ክፉ፤ብዙ ይሰማል ብዙ ይታያል፡፡ ብዙ ብዙም ይታለፋል፡፡ ብዙም ነገር ይለወጣል- ወይ አሻራው አለያም ጠባሳው ይቀራል፡፡ ባርያ ፍንገላ፣ ጭሰኛ መሳፍንት ነገስታት በየዘመናቸው የራሳቸውን፣ መፈክር እያሰሙ ግባቸውን እያስቆጠሩ አልፈዋል፡፡ በባርነቱ ዘመን “ለገዢዎቻችሁ ተገዙ” መሰለኝ የወቅቱ መፈክር (Motto)፣ በጭሰኛው የንጉሱም ዘመን”የሚወደንና የምንወደው ህዝባችን” ነበር የጊዜው መፈክር(Motto)፣ “የሚወደንና የምንወደው ህዝባችን” እያሉ መሪዎቻችን “የሚወዱትንና ሚወዳቸውን” ህዝባቸውን በፍቅራቸው አስረው፤ በደንብ እና ስርዓታቸው ሸንግለው በግፍ አኑረውታል፡፡ የግፍ ፅዋው ሲሞላ ታዲያ. . . ተራማጆች በቀሰቀሱት አብዮት “አንድነት ሃይል ነው”አሉና ተማሪው፣ ሰራተኛው፣ ወታደሩ… ህብረተሰቡ በሙሉ፤ ተነቃነቀ፡፡

“አቆርቋዥ ይውደም

ያለ ምንም ደም

ኢትየጵያ ትቅደም”ን ዘምረው

ህብረተሰባዊት ኢትዮጵያን መሥርተው አንድ ቋንቋ ተናግረው፣ አንድ ጥይት ተኩሰው፣ አንድ አብዮት አፈንድተው፣ አንድ ትውልድ ፈጅተው፤ በጡጫ እና በግልምጫ ልቀው ከወጡት የወቅቱ መሪ ስም ጋር. . .ወደፊት፣ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!” እያሉ  ይፎክሩ ነበር፡፡ በየመድረኩ በሚደረጉ ህዝባዊ ስብሰባዎችና ንግግሮች ላይም “እናት ሃገር ኢትዮጵያ ወይም ሞት” ፣”ህብረሰባዊነት ይለምልም”፣ “. . . ለኢምፔሪያሊስቶች “

በዚያው ዘመን ታዲያ፣ የጦርነቱ ጫና አይሎ የወቅቱ ወጣት ለወታደርነት ሲታፈስ በፍርሃት ይሁን በወኔ “ይሰጠን ይሰጠን ቺቺ . . .መቺ”(የጎደለውን ሞልታችሁ አንብቡ፤ ቃሉን በአሁኑ ሰዓት መጠቀም የሚያስከፋቸው አይጠፉም እና ትቼዋለሁ)”ይሰጠን ይሰጠን ክላሽ ሰላሳ ጎራሽ” በማለት ዘምረው፣ ፎክረው፣ ሃሩር እና አረር በልቷቸው የቀሩትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ምስጋና ለዘመኑ መሪዎቻችን! ጦርነትን በእኛ ይብቃ ላሉት ይሁንና፤ አሁን ጦርነት ስለሌለ የዚህ ዘመን ወጣቶች ውትድርና ጦርነት እና አፈሳ የለብንም፡ ዘመቻ ግን አለብን፡፡ ለሁሉም ነገር ዘመቻ፡፡ በዚያው ወቅት እናቶች በየቀበሌው ተሰብስበው ልጆቻቸውን ለጦርነት ልከው፣ ስንቅ እያዘጋጁ የላይኞቹን መፈክሮች እና “አብዮቱ አይቀለበስም”፣ “ሞት ለ . . . “ (በተመሳሳይ የጎደለውን ሙሉልኝ) ተጨማሪ መፈክራቸው ነበር፤ አሉ፡፡ የእስካሁኑ የሰማሁት ነው የፃፍኩላችሁ፡፡

ግራ ዘመሞች ትግላቸውን ከሰፊው ህዝብ ጋር አሳልጠው ከገጠር ወደ ከተማ መሩትና ድላቸውን “ብሶት የወለደው ጀግናው . . . ለሰፊው ህዝብ . . . ተቆጣጥሮታል” አሉ እና ስልጣኑን ግን . . . (ሃያ ዓመት አለፋቸውም አይደል? ይህን በሹክሹክታ ስሙልኝ) እራሳቸው ያዙት፣ አሉ፡፡ ይህም የሰማሁት ነው፡፡

አዲስ ትክክለኛ ዘመቻ በአዲስ የትኩረት አቅጣጫ የጋራ ጠላታችን ድህነት ላይ ጦርነት ታወጀበት፡፡ ድህነት . . .

ያኔ፣ መሪዎቻችን እስኪ ወደፊት ለሃገራችሁ ካሏችሁ ራዕዮች ውስጥ ጥቂቶቹን ሲባሉ…

የአመቱን ቁጥር የተናገሩት መቼም አይዘነጉት፤ በዚህ ዓመት ውስጥ ህዝባችን በምግብ እህል ራሱን ይችላል፤ በቀን ሶስቴ ይመገባል፡፡ ከዚህ ዓመት በኋላ ደግሞ ቅያሪ ልብሶች. . . በፈገግታ ደምቀው ተናግረው ነበር፡፡ ምን ያህሉ ተሳክቶላቸው ይሆን?

“ታግለን ወድቀን ከግፍ አገዛዝ ነፃ አደረግናችሁ” አሉን፡ አሁን ደግሞ በልማት ጎዳና... አዲዮስ ድህነት! አስፎከሩን፡ እኩልነትን አስጨፈሩን፡፡ ህብረ ብሔርነትን አስዘመሩን፡፡ ከመፈቃቀር፣ከመዋደድ እና ከመዋለድ በላይ መቻቻልን አስፎከሩን፡

ዘመን ዘለልን . . . ዘመንን ቆጠርን!

ሽብርተኝነት ይውደም(ይቅርታ ይውደም የሚለው ቃል የቀድሞው ስርዓት አገላለፅ ነው) ይውደም የሚለው እንዋጋለን በሚለው ተተክቶ ከይቅርታ ጋር ይነበብ፣ ጠባብነት ትምክህተኝነትን እንዋጋ፡፡ ቀንደኛ ጠላታችንን ድህነትንም እንዋጋለን፡፡ አንድ ሰሞን ፎክረናል፡፡

አሁንም ዘመንን ዘለልን… በድህነት ላይ እንደፎከርን ምዕተ ዓመቱ መጣ፡፡ ኮሜዲያን ክበበው በአንዱ የቀልድ ሥራው ውስጥ፣ “ከብድር ሳንወጣ ደሞ ልንበደር ሚሊኒየም መጣ” እንዳለው በሚሊኒየሙ ሚሊኒየም ጠጅ ቤት፣ ሚሊኒየም ቁርጥ፣ ሚሊኒየም ኬክ ቤት፣ ሚሊኒየም፣ ሚሊኒየም፣ ሚሊኒየም፣ ሚሊኒየም … ሚሊኒየም ምን ይሁን ምን ሳይገባን፤ የሚሊኒየም ክብረ በዓል ፊት የኮንደሚኒየም ቤት እጣ ካልተሳካላቸው ውስጥም “እኔ እንግዲህ ኮንደሚኒየሙ አልሆነልኝም … እስቲ ምሊኒየሙን ደግም እሞክራለሁ፡፡” ብላዋል አሉ፡፡ እስራ ምዕት ብለን ቦታና ስሙን ቀይረን ፎከርንበት፡፡ በሚሊኒየሙ ላይም ዘመትንበት፡፡

ልማታዊነት ሌላኛው መፈክር፡፡ ልማታዊ ጋዜጠኛ፣ልማታዊ ምሁር፣ ልማታዊ ባለሃብት፣ የልማት አርበኛ በሰፊው ተፈጠሩ … ለቀጣይ የሃገሪቱ የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ሲባል (ቋንቋውን አሰካካሁት)፡፡ ወጣቱ፣ ገበሬው፣ ምሁሩ፣ ባለሀብቱ በልማታዊነታቸው ተሸለሙ፡፡ ከወጣቶቹ ውስጥ ግን እኔ አልተሸለምኩም፤ ምክንያቱም መንግስት በፈጠረው ምቹ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቼ ወጣቱን በማስተባበር እና በማደራጀት መንግስት በተለመው ትክክለኛ የልማት አቅጣጫ እና ስትራቴጂ ውስጥ በጉልህ እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድ የተሰጠኝን ሃላፊነት ያለኝን አቅም ሁሉ አሟጥጬ በመጠቀም ረገድ በሰፊው ተሳትፊ ስላልነበርኩ መሰለኝ፡፡ እንጂ እኔም እኮ ግን ልማታዊ ወጣት ነኝ፤ ስራዬን በአግባቡ እየሰራሁ ነው፡፡ እኔ እንደገባኝ ልማታዊነት ስራን በአግባቡ መስራት ነው፡፡ (ግን ቀበሌ ለጉዳዬ ካልሆነ በስተቀር ማቶስቶስ አልወድም፡፡)  ከኔ ለየት ያላለ የአንድ ገበሬን ሃሳብ ለካፍላችሁ እና ወደ ጉዳዬ ልሂድ፡፡ የራሳቸው ራዲዮ በየአስራ አምስት ቀኑ፣ ይህን የልማት ጀግና አርበኛ የሜዳይ ሽልማት ታስደምጣቸዋለች፡፡

አንዱ የልማት አርበኛ ከዚህን ያህል ሄክታር ይህን ያህል ኩንታል ባለፈው ዓመት አግብቻለሁ፤ በዚህ የምርት ዘመን ደግሞ በእጥፍ እንደማመርት . . (ቁጥሩ ስለሚያስደነግጥ ይቅርብን) መንግስት  የፈጠረው ትክክለኛ እና ምቹ የልማት. . . (አልጨርሰውም፤ ምክንያቱም አትጨርሰው ይቅር ሰልችቶናል ትሉኛላችሁ ወይም ደግሞ ኢሬቴድን አዲስ ዘመንን ጨምሮ እንደ ሚዲያ ዳሰሳው ልዳስሰው አልፈልግም፡፡ የምፈራው ግን የእንጀራ ገመዴ ጎትቶ እዚያ እንዳይከተኝ ነው፤ እኔንም እንደ “ልማታዊ”ጋዜጠኛ...እንዳትስቁብኝ አደራ፤ፀልዩልኝ፡፡) በጅምር የተውነውን የልማት አርበኛ ንግግርም አብራ ታስደምጣቸዋለች፡፡ እናም ገበሬው የልማት አርበኛውን ጥሩ ጥሩ ተሞክሮዎች ማሳቸው ላይ ሞክረው የተባለው ምርት አልገኝ ሲል፤ አይ በቃ ወይ እኔ ልማታዊ ግብርናን በአግባቡ እና በትክክለኛው መንገድ አላከናወንኩም ወይ ደግሞ፣ በእኛ ቀዬ መንግስት የቀየሰው ትክክለኛ እና ምቹ የልማት . . . .ገና አልደረሰም፡፡ ብለዋል፡፡ አሉ፡፡

አሁንም ዘመን ተሻገርን፤ የአምስቱ አመት የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ፡፡ እሱን ተከትሎ ብዙ የተባለለት የአባይ ግድብ (አሜን፤ ለግድቡ) አንድ በፌስ ቡክ ላይ ያየሁት “ከቢዮንሴ ናይት” ክለብ ቀጥሎ “አባይ ግድቡ ጠጅ ቤትን” ነው፡፡ ከህዳሴው ግድብ  በፈትም ሆነ በኋላ የሰለቸኝ፣ ለጆሮዬ አኞ የሆነው መፈክር ግን የአምስቱ አመት የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ነው፡፡ ከላይ እስከ ታች የመንግሰት ሹማምንት በሙሉ ይህን ቃል የረሳ . . . ብለው  የተማማሉት ምን ነገር እንዳላቸው እንጃ (በዚህ ሁኔታ በየቤታቸው ከየቤተሰባቸው ጋር ላለማለታቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡) “ታላላቅ” ሹማምንቱ “ታላላቅ” የልማት ፕሮጀክታቸውን፤ “ንዑሳን” ባለስልጣናቱም እንደ ስልጣናቸው አነስ ያሉትን  ሲመርቁ ወይ ደግሞ የመሰረት ድንጋይ ሲያስቀምጡ ከሚሉት መሃል “...ይህ ፕሮጀክት መንግስት በአምስቱ አመት የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ካስቀመጣቸው ዋነኛ አጀንዳዎች...”የመግቢያ አረፍተ ነገራቸው ነው፡፡ ከልማታዊ አንቀሳቃሾቻችን እና ተንቀሳቃሾቻችን በተጨማሪም በስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ስፖርተኞቻችን እና የስፖርት ጋዜጠኞቻችንም “...ይህ ስፖርታዊ ውድድር መንግስት በአምስቱ አመት የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ካስቀመጣቸው...” ማለታቸው ተለመደ፡፡ የሚገርመኝ ነገር ይህ መንግስት የሚባለው ምንድነው? ማነው? ባለስልጣኖቻችን “መንግስት” የሚሉት ሲከሱም፣ ሲወቅሱም፣ ሲመርቁም ሆነ ሲራገሙ “...መንግስት...” እያሉ የሚሸሸጉበት መከለያቸው፤ አቋራጭ ማምለጫቸው፤ የነሱ ስብስብ መሆኑን ረስተውት ነው? ወይስ ሌላ ከእነሱም ከእኛም እውቅና ውጪ የሆነ …አለ ይሆን?

ይህም መንግስት እኔን በቀጣይ በአምስት አመቱ የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በልማታዊ ወጣትነት እንደሚሸልመኝ ተስፋ አለኝ፡፡

ሁሉም ነገር ለአምስት አመቱ የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ይሁንና፡፡ አንድ ስጋት ግን አለኝ፤ የመንግስት ሌቦች ግቤን እንዳያደንቅፉት፡፡ ቢሆንም ግን እነዚህን የመንግስት ሌቦችንም ቢሆን መንግስት በእንጭጭነታቸው ከምንጫቸው የሚያደርቅ የመፍትሄ ሃሳብ አስጠንቶ ጨርሶ በቅርቡ ተግባራዊ ስለሚያደርግ ዕቅዴ፣ ከስጋት በዘለለ ምንም እንከን እንደማይገጥመው ተስፋ አለኝ፡፡ ከእዚሁ ከአምስቱ አመት የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ሳንወጣ፤ የእቅዱን ይፋ መሆን ተከትሎ በየቦታው የተሰቀሉት የ”እነሱ እስኪደርሱ እኛን ተመልከቱ” ፎቶግራፎች የተገባውን የተስፋ ቃሉን ሳይጠብቁ፣ የታቀዱትም ሳይደርሱ እነሱ እራሳቸው ቀድመው በተፈራራቂ የአየር ለውጥ ከመወየባቸውም ባሻገር በንፋስ ጎብጠው ተስፋችንን ይዘው በመጥፋት ላይ ይገኛሉ፡፡

የምንኖረው በተስፋ ነው፡፡ ይህ የይሆንልናል ተስፋም እንዳይጠፋ እነዚህን ፖስተሮች የተከላችሁም ያስተከላችሁም፣ ሁላችሁም በተስፋ ስንጠብቅ፣ በተስፋ ስንኖር . . . አደራ እንዳትረሷቸው፡፡ ፎቶዎቻቸው ጥለዋቸው የጠፉ ፕሮጀክቶችን አንዱን እንኳ ከመሬት ሳናይ፤ የአፈፃፀም ችግር የአቅም ምናምን ሰበባ ሰበቦች ሌላ ስንት አመት ያስጠብቁን ይሆን?

ሁሉም ነገር ወደ ትራንስፎርሜሽን እና እቅዱ!!! ከመንግስት ጋር . . .

 

 

Read 1767 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 08:52