Saturday, 19 August 2017 12:36

ቢል ጌትስ የሃብታቸውን 5 % ወይም 4.6 ቢ. ዶላር ለበጎ አድራጎት ለገሱ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ እስካሁን በድምሩ 35 ቢ. ዶላር ለግሰዋል

      የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ የማይክሮሶፍት ኩባንያ መስራች ቢል ጌትስ፣ ባለፉት 20 አመታት ካደረጓቸው የበጎ አድራጎት ልገሳዎች እጅግ ከፍተኛው የተባለውን የ4.6 ቢሊዮን ዶላር ልገሳ ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የ61 አመቱ ቢልጌትስ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን 64 ሚሊዮን አክስዮኖችን ለበጎ አድራጎት መለገሳቸው በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ መደረጉን የጠቆመው ዘገባው፣ ይህ ገንዘብ ባለሃብቱ በአሁኑ ወቅት ካላቸው 89.9 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ሃብት 5 በመቶ ያህል እንደሚደርስም ገልጧል፡፡
ከማይክሮሶፍት ድርሻቸው በተደጋጋሚ ብዙ ገንዘብ ለበጎ አድራጎት በመለገስ የሚታወቁት ቢል ጌትስ፤ በአሁኑ ወቅት በማይክሮሶፍት ኩባንያ ውስጥ ከነበራቸው 24 በመቶ የአክስዮን ድርሻ የቀራቸው 1.3 በመቶ ብቻ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ይሄኛውን ልገሳ ከሰጡ በኋላም ከአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነርነት ዝቅ አለማለታቸውን አመልክቷል፡፡
ቢል ጌትስ እና ባለቤታቸው ሚሊንዳ ጌትስ እ.ኤ.አ ከ1994 አንስቶ ለበጎ አድራጎት ተግባራት የለገሱት አጠቃላይ ገንዘብ 35 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ያለው ዘገባው፣ ቢል ጌትስ ከማይክሮሶፍት ድርሻቸው በ1999 የፈረንጆች አመት 16 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2000 አመት ደግሞ 5.1 ቢሊዮን ዶላር ለተመሳሳይ በጎ አላማ መለገሳቸውንም አስታውሷል፡፡
ቢልጌትስ በአለማችን በዘንድሮው አመት ከፍተኛው የበጎ አድራጎት ልገሳ ነው የተባለለትን ይሄኛውን የገንዘብ ልገሳ ያደረጉት ለየትኛው ፋውንዴሽን ወይም ተቋም እንደሆነ ግልጽ መረጃ አለመኖሩን ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 1115 times