Saturday, 19 August 2017 12:35

የሙያ ስነምግባር (ETHIS)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   የህክምና ባለሙያዎችን የሙያ ስነምግባር በሚመለከት ለዚህ እትም ማብራሪያቸውን እንዲሰጡን የጋበዝናቸው ዶ/ር ሙኒር ካሳ የጽንስና ማህጸን ህክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ዶ/ር ሙኒር እንደሚሉት ከሆነ አንድ ሐኪም ወደህክምና ሙያ ከመግባቱ በፊት በተወሰኑ ነገሮች ከእራሱ ጋር መስማማት ይጠበቅበታል፡፡ሐኪም ለማከም የአንድ ሰው ፈቃድ ይፈል ጋል፡፡  በአጠቃላይ ህብረተሰቡም ለእነዚህ ሐኪሞች እውቅና ሲኖራቸው የታመመን ሰው በአስፈላጊው ነገር ሁሉ ማለትም ከቀዶ ሕክምና ጀምሮ መድሀኒት ሰጥቶ እስከማከም ድረስ መፍቀዱን ያሳያል፡፡ ይህም ለምንድነው ተብሎ ሲጠየቅ ህብረተሰቡ እነዚያን ሐኪሞች ጥሩ ስራ ይሰራሉ ብሎ ስለሚያምናቸው ነው፡፡ ነገር ግን ያ እምነት እየተሸረሸረ ከመጣ ሰው ከዘመናዊ ሕክምና እየራቀ ወደባእድ አምልኮና ባህላዊ ሕክምና ይሄዳል፡፡ ለምሳሌ እንደእንግሊዝ ባሉ ሀገራት ህብረተቡ የጤና ተቋሞቻቸውን በጣም ስለሚወዱና ስለሚያምኑ ስለሚያከብሩም ጭምር ሐኪም በሚነግራቸው መመሪያ በሚገባ ምንም ሳያጉዋድሉ ይጠቀማሉ፡፡  ስለዚህ ያንን እምነት እንዲኖር ለማድረግ ሐኪሞች በማህራቸው ተሰብስበው አንድ ሐኪም በራሱና በሕመምተኞች መካከል ያለው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት? በሐኪሞች መካከል ያለው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት? ሐኪሙ በግሉስ ምን አይነት አቋም ይዞ መገኘት አለበት የሚለውን እና የመሳሰሉትን ነገሮች በጥንቃቄ ተመልክተው ህግ ያወጣሉ፡፡ ይህ ነው የሙያ ስነምግባር መመሪያ የሚባለው ብለዋል ዶ/ር ሙኒር ካሳ፡፡
የህክምናው የሙያ ስነምግባር ከወጣ በሁዋላ የሚመጣ አዲስ የህክምና ባለሙያ አሰቀድሞ በእነዚህ መሰረታዊ መርሆዎች ላይ መስማማት አለበት ፡፡ ሲስማማ ብቻ ነው ሐኪም የሚሆ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ የሚስማማ የህክምና ባለሙያ ወደሙያው ከመዝለቁ በፊት ከእርሱ በፊት በቀደሙ ባለሙያዎች የወጣውን እና የጸደቀውን ህግ በመስማማት በማመን ቃል ይገባል። በአሁኑ ጊዜ የአለም የህክምና ማህበር የጄኔቫ ስምምነት የሚባል ሐኪሞች ወደሙያው ከመግባታቸው በፊት የሚገቡዋቸው ቃለ መሀላዎች አሉ፡፡ ከእነርሱም ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
በጽኑ ሁኔታ ሕይወቴን በሙሉ የሰውን ዘር ለማገልገል ማመኔን ‘መስማማቴን ቃል እገባለሁ ይላል፡፡ ይህ ማለት ቀለም ‘ጾታ’ ዘር ‘ሀይማኖት ‘ድንበር ‘ሀብት የመሳሰሉትን ሰውን ከሰው የሚለዩት ነገሮች ሁሉ ሳይከልሉኝ በእኩል ለማገልገል ተስማምቻለሁ፡፡ ለዚህ ተግባር ሕይወቴን አሳልፌ እሰጣለሁ ብሎ ቃል ሲገባ ነው ወደሕክምና ስራው የሚገባው፡፡
ይህን የተማርኩትን ሙያ ሕሊናዬና ክብሬን በማይነካ ሁኔታ የሰውንም ክብር በማይነካ ሁኔታ ታካሚውን አገለግላለሁ ብሎ ቃል ሲገባ ነው ወደሙያው የሚቀላቀለው፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ ከባዱና ዋነኛው ደግሞ የህመምተኛዬን ጤና በማንኛውም ሁኔታ አስቀድማ ለሁ የሚለው ነው፡፡  ለምሳሌም ሐኪሙ ይህን ቃል ሲገባ በእሳቤው ውስጥ መግባት ያለበት በእኔ በእራሴ ሕይወትና ጤና ላይ እንኩዋን አንድ ነገር ቢፈጠር ቅድሚያ የምሰጠው የሕመም ተኛዬን ጤናና ሕይወት ማዳን ነው የሚለውን ቃል ሲገባ ነው አንድ ሐኪም ወደሙያው ሊቀላ ቀል የሚችለው፡፡ ስለዚህም አንድ ሰው ሐኪም ሲሆን ለማገልገል የሚመጣው እራሱን ሳይሆን ሌላውን ታካሚውን ወይንም ሕመምተኛውን ነው፡፡ ይህንን ቃሉን ሲያፈርስ ግን የሙያ ማህበሩ ተነጋ ግሮ ‘ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ‘የማይሻሻልና ህብረተሰቡን በትክክል የማያገለግል መሆኑ ሲረጋገጥ ለሙያው ብቁ አይደለም ብለው ሊያስወግዱት የስራ ፈቃዱንም ሊነጥቁት ይገባል፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን የሚፈጽም ማህበር በተደራጀ መልክ የለም፡፡ ወደፊት ግን የሙያ ማህ በራቱ ይጀምራሉ ብለን እንጠብቃለን። የሙያ ማህበራቱ ይህንን እርምጃ ቢወስዱ ሐኪሞቹ በህብረተሰቡ ዘንድ ተአማኒነትን እንደሚያተርፉ እሙን ነው ብለዋል ዶ/ር ሙኒር ካሳ፡፡
የሙያ ስነምግባር ደንብ በኢትዮጵያ ያለው አንድ ነው፡፡ እሱም የኢትዮጵያ ሐኪሞች ማህበር ያወጣው ነው። ነገር ግን የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች የሙያ ስነምግባር መመሪያ የላቸውም፡፡ ስለዚህም አሁን ከአሜሪካው የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ኮሌጅ እና ከአለምአቀፍ የስነተዋልዶ ጤና ስልጠና ማእከል በሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለመስራት ዝግጁ ነን ፡፡ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች የስነ ምግባር መመሪያ በሐኪሞች ማህበር በፊት ከተዘጋጀው በጣም የሚለይ ነው፡፡ የዚህም ምክንያቱ ጽሁፉ ሲጀምር ታሳቢ የሚያደርገው ሐኪሙ በስነምግባር ዙሪያ ምን አይነት ችግር አለበት? ከሚለው ስለሚነሳ ነው፡፡ ስነምግባር ማለት ለአንድ ሐኪም የትኛው ትክክል ነው ?የትኛው ነው መሰራት ያለበት? የሚለውን እና መሰል ነገሮችን የሚነግረው ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆን አንድ ምሳሌ አለ አሉ ዶ/ር ሙኒር፡፡
አንዲት ሴት ለመውለድ ወደሐኪም ቤት  ትመጣለች፡፡ ሴትየዋ በሐኪምዋ ስትታይ ደም ከሌላ ሰው ሊሰጣት ይገባል፡፡ እስዋ ግን በእምነትዋ ምክንያት ደም ከሌላ ሰው መውሰድ እንደማትፈልግ ለሐኪምዋ ትገልጻለች፡፡ ሐኪምዋ ግን ይህች ሴት ደም ካላ ገኘች መሞትዋ መሆኑን ስለሚያውቅ ይጨነቃል፡፡ ስለዚህ ከምትሞት ደም መውሰድ አለባት ብሎ ቢወስን እስዋ ደግሞ ደም ባለመውሰድ ብትሞት በእምነትዋ የምታው ቀውንና አገኛለሁ ብላ የምትጠብቀውን የዘላለም ሕይወት ሊነፍገኝ ነው ብላ ትቃወማለች፡፡ ምን ማድረግ ነው ያለበት? እንደዚህ ያሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሐኪሙ የሚመራበት የስነምግባር መመሪያ ሊኖረው ይገባል።
ከላይ የተጠቀሰውን አይነትና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ለመመለስ መሰረታዊ የማይጣሱ ደንቦች ምንድናቸው? የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
በበሽተኛውና በሐኪሙ መሐከል ምን አይነት ግንኙነት መኖር አለበት የሚለው አንዱ ነው፡፡ ይህ ቃለ መሐላ የተፈጸመበትና የበሽተኛዬ ደህንነት ከሁሉ ነገር ይበልጣል የሚለውን የሚመለከት ነው፡፡
ሌላው …ስለራሱ በሽታና ስለደህንነቱ የሚወስነው ማነው? በሽተኛው ነው ወይንስ ሐኪሙ ነው? የሚ ለው ነው፡፡ ሐኪሙ መረጃ እና አማራጮችን መስጠት እንጂ መወሰን አይችልም፡፡ ስለዚህም የበሽተኛው መብት የማይደፈርና የማይገሰስ ነው፡፡
ቀጣዩ ፍትህ ነው፡፡ ፍትህ ማለት ሰውን ከሰው አላበላልጥም፡፡ ሐኪሙ ከበሽተኛ ጋር ባለኝ ግንኙነት ሁሉንም ሰው እኩል አክማለሁ ብሎ ማለት አለበት፡፡
የእራሱ የሃኪሙ ጸባይን በሚመለከትም ምግባሩ ምን ይመስላል? እንዴትስ ሊሰራ ይገባል? የሚለውን ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ሐኪም ምንጊዜም መዋሸት የለበትም፡፡
ሐኪም ታካሚውን መጥቀም አለበት፡፡ ሐኪም በሽተኛውን የሚጠቅም ነገር ባያደርግ እንኩዋን ጉዳት የሚያመጣ ነገር ግን አያደርግም፡፡
ሐኪሞች በየጊዜው እያነበቡ እራሳቸውን በእውቀት እየገነቡ በየጊዜው ከሚነደፈው የሳይንስ መርሐ ግብር ጋር እራሳቸውን ማዛመድ አለባቸው፡፡
ሌላው የጥቅም ግጭትን ማስወገድ ነው፡፡ አንድ ሐኪም ታካሚውን ወደሌላ ላቦራቶሪ ወይንም ክሊኒክ እንዲሄድ ሲመክር በግልጽ እዚያ ብትታከም ወይንም ምርመራህን ብታሰራ ጥሩ ቦታ ነው፡፡ በእርግጥ እኔ ኮሚሽን አገኝበታለሁ ወይንም አላገኝትም ብሎ መናገር መቻል አለበት፡፡ ይሁን እንጂ ሐኪም እንደዚህ ያለ የጥቅም ግጭት የሚፈጥር ነገር ውስጥ ከጅምሩም መግባት የለበትም ተብሎ ይታመናል፡፡
እንደማህጸንና ጽንስ ሐኪምነት ሴቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ጉዳት ይበልጥ መረዳትና መመስከር ስለሚቻል ሐኪም ብቻ መሆን ሳይሆን ስለሴቶቹ ችግር በአደባባይ ማስረዳት ወይ ንም መመስከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ችግሩን በውል ስለሚያውቁትና በተጨባጭ መረጃ በማስደገፍ ማስረዳት ሰለሚችሉ ተደማጭነታቸው ከፍተኛ ስለሚሆን ነው፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች አብዛኛው የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች በአለም ዙሪያ የሚመሩበትና የሚከተሉት መሰረታዊ መርሆዎች ስለሆኑ በኢትዮያም እንዲዘጋጅ የታቀደው የጽንስና ማህጸን ህክምና የስነምግባር መመሪያ ከዚህ የዘለለ አይሆንም እንደ ዶ/ር ሙኒር ካሳ ማብራሪያ።
የሙያው ስነምግባር ቢቀረጽ በዋነኛነት አንድ የማህጸን ሐኪም ርህራሔ በተሞላበት መንፈስ ታካሚውን እንዲረዳ ያስችለዋል፡፡

Read 1402 times