Sunday, 20 August 2017 00:00

ኢትዮ ዩናይትድ በዓለም አቀፍ የቴኳንዶ ሻምፒዮና ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

  ኢትዮ-ዩናይትድ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አሶሴሽን 8 ክልሎችና ከ70 በላይ ክለቦች  የሚሳተፉበት ልዩ ሻምፒዮና ከዛሬ ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ያካሂዳል፡፡
የኢትዮ-ዩናይትድ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አሶሴሽን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው የቴኳንዶ ሻምፒዮናው ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ የሚወክሉ ስፖርተኞች የሚመለመሉበት እና ዝግጅት የሚያደርጉበት ይሆናል፡፡ በመስከረም ወር መግቢያ ላይ በሰሜን ኮርያ በሚካሄደው ኢንተርናሽናል የቴኳንዶ ሻምፒዮና ላይ እንድትሳተፍ ኢትዮጵያ መጋበዟን በመግለጫው ላይ የጠቀሱት ማስተር አብዲ በወጣቶች ስፖርት አካዳሚው በሁለት ቀናት በሚደረገው ልዩ ሻምፒዮና ብቁ ስፖርቶችን ከመምረጥ ባሻገር በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ተሳትፎ የሚያጠናክሩ ስራዎች እናከናውናለን ብለዋል፡፡
ማስተር አብዲ እንደተናገሩት በሰሜን ኮርያ በሚካሄደው ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ ከ50-100 የሚደርሱ የቴኳንዶ ስፖርተኞች፣ አሰልጣኞች፣ ደጋፊዎች እና የሚዲያ ባለሙያዎች ማሳተፍ ትችላለች፡፡ በሰሜን ኮርያ ከሚዘጋጀው ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ሻምፒዮና ባሻገር ወደዚያው በሚደረግ ጉዞ በቻይና  በህንድ ከተሞች በቴኳንዶ ስፖርት ዙሪያ ስልጠናዎች የልምድ ልውውጥ መድረኮች እንደሚኖሩም ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ወጣቶች የስፖርት አካዳመ በሚደረገው የቴኳንዶ ሻምፒዮና የበጎ አድራጎት ተግባር እንደሚከናወኑም ማህበሩ ገልጿል፡፡ ማህበሩ የአልባሳት፤ የማማያ ቁሳቁስ ችግሮች ያሉባቸውን ለመደገፍ በአገር አቀፍ ደረጃ መንቀሳቀሱን ያመለከተው ማህበሩ ከ500 በላይ የቴኳንዶ ስፖርተኞችን በማስተባበር የተሰባሰቡ ርዳታዎችን ሙዳይት ለተባለ የግበረሰናይ ተቋም እንደሚያበረክት አስታውቋል፡፡
ከተመሰረተ ከ25 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን ኢትዮ ዩናይትድ ቴኳንዶ አሶሴሽን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት የ62 ዓመቱ  ማስተር አብዲ ከድር ሲሆኑ በቴኳንዶ ስፖርት ውስጥ ከ46 ዓመት በላይ ቆይተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና  የሚሰጠውን 8ኛ ማዕረግ ዳን በማግኘት በአፍሪካ እና በኢትዮጵያ የመጀመርያውና ብቸኛው ናቸው፡፡ በኢትዮ ዩናይትድ አሶሴሽን ስር ብቻ ከ30 ሺ በላይ ሰልጣኞች መኖራቸውን የሚናገሩት ማስተር አብዲ ፣ በመላው የኢትዮጵያ ክልሎች ከ60 በላይ እውቅና የተሰጣቸው ክለቦች በስፖርቱ እንደሚንቀሳቀሱ በከፍተኛ ደረጃ በተስፋፋበት የአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 200 ክለቦች እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ዓለም አቀፉ ኢንተርናሽናል የቴኳንዶ ስፖርት ፌዴሬሽን 60ኛ ዓመቱን ሲያከብር ከ185 አገራት ለተውጣጡና ከ20 ዓመት በላይ በስፖርቱ ላሳለፉ አንጋፋ ባለሙያዎች የወርቅ ሽልማት በመስጠት ሲያመሰግን ማስተር አብዲ ሽልማታቸውን በቡልጋርያ እንደተቀበሉ ይታወሳል፡፡

Read 2212 times