Saturday, 19 August 2017 12:12

ኢትዮጵያ በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚያረካ ውጤት አላስመዘገበችም

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ለንደን ባስተናገደችው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በ13 የተለያዩ ውድድሮች 46 አትሌቶችን በማስመዝገብ የተሳተፈች ሲሆን የሚያረካ ውጤት አልተመዘገበም፡፡ በሻምፒዮናው የተሳተፉት የኢትዮጵያ አትሌቶች ብዙ ልምድ የሌላቸውና ወጣቶች ስለነበሩ፤ የቡድን ስራ የተጠናከረ ባለመሆኑ፤ የአሯሯጥ ስትራቴጂዎች አለመኖራቸው እና የታክቲክ ጉድለቶች መስተዋላቸው፤ በመሰናክል እና በመካከለኛ ርቀት በተወዳደሩት ቴክኒካዊ ችግሮች በጉልህ መታየታቸው፤  አትሌቶች በመጨረሻ ሰዓት በጉዳትና በተለያዩ ምክንያቶች ተሳትፎ አለማድረጋቸው፤ የተፎካካሪ አገራትን ወቅታዊ ደረጃ ያገናዘበ በቂ ዝግጅት  አለመሰራቱ እንዲሁም በአሰልጣኞች የስራ ድርሻ እና የተሟላ ሃላፊነት ዙርያ ያሉ አወዛጋቢ ሁኔታዎች አጠቃላይ ውጤቱ እንዲወርድ አድርጎታል።
በሴቶች 10ሺ ሜትርና በወንዶች 5ሺ ሜትር ለኢትዮጵያ የተመዘገቡት 2 የወርቅ ሜዳልያዎች ከሁለት ሻምፒዮናዎች በኋላ የተመዘገቡ አዳዲስ ስኬቶች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በሴቶች 10ሺ ሜትር፤ በወንዶች ማራቶን እና በሴቶች 5ሺ ሜትር  3 የብር ሜዳልያዎች በተጨማሪ ተገኝተዋል፡፡ ከሜዳልያ ውጤቶች ባሻገር ደግሞ በ2 አራተኛ ደረጃዎች፤ በ3 አምስተኛ ደረጃዎች፤ በ1 ስድስተኛ ደረጃ፤ በ3 ሰባተኛ ደረጃዎች እንዲሁም በ2 ስምንተኛ ደረጃዎች 11 ዲፕሎማዎች ተመዝግበዋል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው ከቀረበው እስከ 176 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ሽልማት የኢትዮጵያ ድርሻ እስከ 8 ሚሊዮን ብር  ሆኗል፡፡  በሌላ በኩል ከ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኋላ ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የተሳትፎ ታሪኳ ያስመዘገበቻቸው 77 ሜዳልያዎች የደረሱ ሲሆን 27 የወርቅ፤ 25 የብርና 25 የነሐስ ሜዳልያዎች ናቸው፡፡
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በሜዳልያዎች እና እስከ ስምንተኛ ደረጃ በሚመዘገቡ ውጤቶች ስሌት መሰረት በሚወጣው ደረጃ ኢትዮጵያ በ70 ነጥብ  ከአፍሪካ ሶስተኛ ከዓለም 7ኛ ደረጃ አግኝታለች፡፡    አሜሪካ በ10 የወርቅ፤ 11 የብር እና 9 የነሐስ ሜዳልያዎች በ272 ነጥብ  አንደኛ ደረጃ   ኬንያ በ5 የወርቅ 2 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎች በ124 ነጥብ  ሁለተኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡ እንግሊዝ በ2 የወርቅ፤ 3 የብር እና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች 105  ነጥብ፤ ፖላንድ በ2 የወርቅ፤ 2 የብር እና 4 የነሐስ ሜዳልያዎች 86 ነጥብ፤ ቻይና በ2 የወርቅ፤ 3 የብር እና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች 81 ነጥብ እንዲሁም ጀርመን በ1 የወርቅ፤ 2 የብር እና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች 78 ነጥብ በማስመዝገብ ከኢትዮጵያ በፊት እስከ 6ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቅቀዋል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ለኢትዮጵያ ሁለቱን የወርቅ ሜዳልያዎች ያስመዘገቡት በሴቶች 10ሺ ሜትር አልማዝ አያና እንዲሁም በወንዶች 5ሺ ሜትር ሙክታር ኢድሪስ ናቸው፡፡ የሁለቱ  አትሌቶች ድል ከሁለት ሻምፒዮናዎች በኋላ ለኢትዮጵያ የተመዘገቡ አዳዲስ ታሪኮች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በ10ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድ የያዘችው፤ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሆነችው አልማዝ አያና የዓለም ሻምፒዮንነት ክብር መጨመሯ ትልቅ አድናቆትን አትርፎላታል፡፡ በ5ሺ ሜትር ወንዶች ደግሞ ሙክታር ኢድሪስ በሁለት ዓለም ሻምፒዮናዎች እና በሁለት ኦሎምፒኮች በእንግሊዛዊው ሞ ፋራህ ተነጥቆ የነበረውን ክብር ሊመልስ ችሏል፡፡
ከወርቅ ሜዳልያዎቹ ባሻገር የተገኙትን3 የብር ሜዳልያዎችን በሴቶች 10ሺ ሜትር ጥሩነሽ ዲባባ፤ በወንዶች ማራቶን ታምራት ቶላ እና በሴቶች 5ሺ ሜትር አልማዝ አያና አስመዝግበዋቸዋል፡፡ አልማዝ አያና በ5ሺ ሜትር በአጨራረስ ጉድለት እና በታክቲካዊ መዘናጋት የብር ሜዳልያ ከወሰደች በኋላ በሻምፒዮናው ሁለት ሜዳልያዎችን በማስመዝገብ ከፍተኛውን ውጤት ስታዝመዘግብ፤ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ በሻምፒዮናው ታሪክ 6ኛዋን የሜዳልያ ክብር በብር ሜዳልያ በማግኘት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት ልትይዝ ችላለች፡፡
በወንዶች 800 ሜትር መሐመድ አማን ከሁለት የማጣርያ ውድድሮች በኋላ ለፍፃሜ በመድረስ 6ኛ ደረጃ ያገኘ ሲሆን  በሴቶች ደግሞ ሃብታም አለሙ ግማሽ ፍፃሜ ማህሌት ሙሉጌታ እና ኮሬ ቶላ በመጀመርያው ማጣርያ ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በ1500 ሜትር በመጀመርያው ማጣርያ ሳሙኤል ተፈራ በ31ኛ ደረጃ ሲወድቅ፤ ታሬሳ ቶሎሳ ውድድሩን በማቋረጥ ጫላ ረጋሳ ከእነጭራሹ ሳይሰለፍ ቀርቷል፡፡ በሴቶች ደግሞ የቀድሞ ሻምፒዮን የነበረችው ገንዘቤ ዲባባ ሁለት የማጣርያ ውድድሮችን በማለፍ ለፍፃሜ ቀርባ በ12ኛ ደረጃ መጨረሷ ያልተጠበቀ ነበር፡፡ በሱ ሳዶ እና ጉድፍ ፀጋዬ በግማሽ ፍፃሜው እንዲሁም ፋንቱ ወርቁ በመጀመርያው ማጣርያ ተሳትፏቸው ተወስኗል፡፡
በወንዶች 5ሺ ሜትር ሙክታር ኢድሪስ የወርቅ ሜዳልያውን መውሰዱ አስደናቂው ድል ነበር፡፡ የቡድን ስራ ወሳኝነት በተንፀባረቀበት በዚህ ውድድር ዮሚፍ ቀጀልቻ በ4ኛ ደረጃ እንዲሁም ሰለሞን ባረጋ በ5ኛ ደረጃ ጨርሰዋል፡፡ የዳይመንድ ሊግ አሸናፊው ሐጎስ ገብረህይወት በጉዳት ሳይሳተፍ መቅረቱ የሚጠቀስ ነው፡፡  በሴቶች 5ሺ ሜትር የገንዘቤ ዲባባ አለመሳተፍ የታክቲክ ችግር ፈጥሯል፡፡ ባለፉት ሁለት ሻምፒዮናዎች የነበረው የውጤት የበላይነት እና የወርቅ ሜዳልያ ስኬት ተነጥቋል፡፡ ያለፈው ሻምፒዮንነቷን ማስጠበቅ ያልቻለችው አልማዝ አያና የብር ሜዳልያ ስትወስድ ሰንበሬ ተፈሪ በ4ኛ ደረጃ  እንዲሁም ለተሰንበት ግደይ በ11ኛ ደረጃ ከሜዳልያ ውጭ ሆነዋል፡፡
በወንዶች 10ሺ ሜትር ጀማል ይመር 5ኛ፤ አባዲ ሃዲስ 7ኛ እንዲሁም አንድአምላክ በሃይሉ 10 ደረጃ ነበራቸው፡፡ በሴቶች ደግሞ አልማዝ አያና የወርቅ ሜዳልያውን ስትጎናፀፍ ጥሩነሽ ዲባባ የብር ሜዳልያ አግኝታ ዴራ ዲዳ 14ኛ ደረጃ ነበራት፡፡
በወንዶች ማራቶን ታምራት ቶላ የብር ሜዳልያውን ሲወስድ ፀጋዬ መኮንን 19ኛ ደረጃ አግኝቶ የማነ ፀጋዬ ውድድሩን ሳይጨርስ አቋርጦ ወጥቷል፡፡ በሴቶች በኩል ሹሬ ደምሴ 5ኛ፤ ያለፈው ሻምፒዮን ማሬ ዲባባ 8ኛ፤ ብርሃኔ ዲባባ 10ኛ እና አሰለፈች መርጊያ 12ኛ ደረጃ አግኝተዋል፡፡ በወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ተስፋዬ ዲሪባ ለፍፃሜ በመብቃት በ7ኛ ደረጃ ሲጨርስ ታፈሰ ሰቦቃ እና ጌትነት ዋሌ ማጣርያውን አላለፉም፡፡   በሴቶች ደግሞ እቴነሽ ዲሮ በግማሽ ፍፃሜ ተሳትፎዋ ሲወሰን፤ ሶፍያ አሰፋ በመጀመርያው ማጣርያ ወድቃ ብርቱካን ፈንቴ ደግሞ በግማሽ ፍፃሜው በጉዳት ምክንያት ሳትሰለፍ ቀርታለች፡፡ በሴቶች የ20 ኪሜትር የርምጃ ውድድር  የኋላዬ በለጠው በ44ኛ ደረጃ ስትጨርስ አስካለ ቲኬሳ አልተሳተፈችም፡፡

Read 1456 times