Saturday, 12 August 2017 00:00

15 ኩባንያዎችና የ210 ባለስልጣናትና ባለሀብቶች ንብረት ታግዷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(28 votes)

ፖሊስ የሙስና ተጠርጣሪዎችን ንብረት እያሳገደ መሆኑን ለፍ/ቤት አስረዳ

ከሙስና ጋር በተያያዘ የ15 ኩባንያዎችና የ210 ባለስልጣናትና ባለሀብቶች ንብረት መታገዱ የታወቀ ሲሆን ትናንት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉትን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙን ጨምሮ የታሳሪዎች ቁጥር 54 ደርሷል፡፡
ከታገዱት ኩባንያዎች መካከል አሰር ኮንስትራክሽን፣ ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን፣ ዲኤምሲ (DMC) ኮንስትራክሽን፣ የማነ ግርማይ ኮንስትራክሽን (GYB)፣ ቲና ኮንስትራክሽን፣ ትራንስ ናሽናል ኮምፒውተር ትሬዲንግ፣ ሃይሰም ኢንጅነሪንግ አክሲዮን ማኅበር፣ ከማኒክ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር እና ጆንግ ሊንግ ኢንተርናሽናል ኢንጅነሪንግ ይጠቀሳሉ፡፡  በሌላ በኩል በሙስና ተጠርጥረው በመጀመሪያው ቀን ከታሰሩት መካከል ፖሊስ በ37 ቱ ላይ በ14 ቀን ውስጥ ያደረገውን ምርመራ ለፍ/ቤት ገልፆ፣ ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው የጠየቀ ሲሆን ከወንጀሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ንብረቶች እያሳገደ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ፖሊስ ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ከጠየቀባቸው ምክንያቶች ውስጥ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የሚገኙ ምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ ሰነዶችን ለማሰባሰብ፣ ተጠርጣሪዎች ከገቢያቸው በላይ ያፈሯቸውን ንብረቶች ለማሳገድና የማጣራት ስራ ለማከናወን፣ እንዲሁም ዝርዝር የኦዲት ሪፖርትና የባለሙያ ምስክር ቃል ለመቀበል መሆኑ ተገልጿል፡፡  ከወንጀሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እንዲሁም ከተጠርጣሪዎች መኖሪያ ቤት በብርብራ የተያዙ ሰነዶችን በመለየት  ለፎረንሲክ ምርመራ በመላክ ውጤቱን የመቀበል ስራ እንደሚቀረውም ፖሊስ አስታውቋል፡፡ በሌሎች ሀገራት የሚገኙ የተጠርጣሪዎች ንብረትን በተመለከተ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል መረጃዎችን የማሰባሰብ ተግባርም እንደሚቀረው ለፍ/ቤቱ አስረድቷል፡፡
ተጠርጣሪዎችም፤ አስቀድሞ የተሰጠው የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ በቂ መሆኑን በመጠቆም፣ አብዛኞቹ መረጃዎችም በራሱ በመንግስት ተቋማት የሚገኙ በመሆኑ ፖሊስ ተጨማሪ ቀን ሊፈቀድለት አይገባም የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ጉዳያቸውን በውጪ ሆነው እንዲከታተሉም ጠይቀዋል- ተጠርጣሪዎቹ፡፡
ፍ/ቤቱም የዋስትና መብት ጥያቄውን ውድቅ ያደረገ ሲሆን ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የ14 ቀን ቀጠሮ ፈቅዷል፡፡ ፖሊስ በቀጣይ ቀጠሮ የእያንዳንዱን ተጠርጣሪ ተሳትፎና ጉዳት በዝርዝር እንዲያቀርብም ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የፖሊስ የምርመራ ውጤትን ለመስማት ከነሐሴ 8 እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል፡፡

Read 6494 times