Saturday, 12 August 2017 00:00

የድርቅ ተረጂዎች ቁጥር ወደ 8.5 ሚሊዮን አሻቀበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

· ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለመጠጥ ውሃ እጥረት ተጋልጠዋል
· ችግሩን ለመቋቋም 1.25 ቢ. ዶላር ያስፈልጋል

ባለፈው ሚያዚያ 7.8 ሚሊዮን የነበረው የድርቅ ተረጂዎች ቁጥር በአሁን ወቅት ወደ 8.5 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለአዲስ አድማስ በሰጠው መረጃ የጠቆመ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት በበኩሉ፤በሀገሪቱ 10.5 ሚሊዮን ሰዎች ለከፍተኛ የመጠጥ ውሃ እጥረት ተጋልጠዋል ብሏል፡፡
በሀገሪቱ የድርቅ ተረጂዎች ቁጥር ማሻቀቡ የታወቀው በበልግ አብቃይና በአርብቶ አደር አካባቢዎች ከግንቦት 15 እስከ ሰኔ 15 2009 ዓ.ም በተደረገ ጥናት መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
የወቅቱ የዝናብ ሁኔታ፣ የእርሻ እንቅስቃሴ፣ በማሳ ላይ ያለ የሰብል ሁኔታና የምርት ግምትን ጨምሮ የግጦሽና የውሃ አቅርቦት፣ የእንስሳት አቋምና ጤና እንዲሁም የእርዳታ አቅርቦቱን መሰረት በማድረግ፣ የዳሰሳ ጥናቱ መካሄዱን የጠቆመው ኮሚሽኑ፤ በተገኘው ውጤትም ቀደም ሲል 7.8 ሚሊዮን የነበረው የተረጂዎች ቁጥር ወደ 8.5 ሚሊዮን ማሻቀቡ መረጋገጡን ገልጿል፡፡ እነዚህ ዜጎችም ለቀጣዩ አምስት ወራት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል፡፡
በዚህ የዳሰሳ ጥናት፤ የበልግ ዝናብ መዛባት፣ የመኖና የግጦሽ እጥረት እንዲሁም የምርት መቀነስና የውሃ እጥረት ለተረጅዎች ቁጥር ማሻቀብ ምክንያት እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የተባበሩት መንግስታት፣ የሠብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት፤ በጥር 2009 ዓ.ም የተረጅዎች ቁጥር 5.6 ሚሊዮን እንደነበር፣ በሚያዚያ ወደ 7.8 ሚሊዮን ማደጉን፣ አሁን ደግሞ ወደ 8.5 ሚሊዮን ማሻቀቡን ጠቁሞ፣ አለማቀፍ ተቋማት ለችግሩ ተገቢውን ትኩረት አለመስጠታቸው  አሳሳቢ ነው  ብሏል፡፡ 376 ሺህ ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ በአስቸኳይ ይፈልጋሉ ብሏል - ሪፖርቱ፡፡ 10.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለመጠጥ ውሃ እጥረት መጋለጣቸውን የጠቆመው ይኸው ሪፖርት፤ 2.25 ሚሊዮን አባወራዎች ለከብቶቻቸው አስቸኳይ መኖ እንደሚፈልጉ አስታውቋል፡፡
 ችግሩን ለመቋቋም 1.25 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ያለው የተባበሩት መንግስታት፤ 3.6 ሚሊዮን ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶችም በከፍተኛ የምግብ እጥረት ውስጥ ናቸው ብሏል - በሪፖርቱ፡፡ በእርዳታ አሰጣጡ ላይ ከደቡብ ሱዳን የሚፈልሱ ስደተኞች መጠን መጨመር ተግዳሮት መፍጠሩንም ጠቁሟል፡፡  
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜቲሪዎሎጂ ትንበያን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ 1.5 ሚሊዮን ዜጎች በክረምቱ የጎርፍ አደጋ የተጋረጠባቸው ሲሆን  እስካሁንም 5 መቶ ሺህ ያህሉ በጎርፍ ምክንያት ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ይጠቁማል፡፡ ከ8.5 ሚሊዮን የድርቅ ተረጂዎች በተጨማሪ፣ በሀገሪቱ 4 ሚሊዮን የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተረጂዎች እንዳሉ ተመልክቷል፡፡   

Read 1301 times