Sunday, 20 August 2017 00:00

በአማራና በደቡብ፣753 የመንግሥት አመራሮች በሙስና ተፈርዶባቸዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

ከ3 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተመላሽ ተደርጓል
እስከ 17 ዓመት የሚደርስ እስራት ተፈርዶባቸዋል

ሊጠናቀቅ ጥቂት ሳምንታት ብቻ በቀረው 2009 ዓ.ም ብቻ፣ በደቡብና በአማራ ክልል፣ 753 የመንግስት አመራሮች፣በሙስና ክስ ተመስርቶባቸው፣ ጥፋተኛው ሆነው በመገኘታቸው፣ እስከ 17 ዓመት በሚደርስ እስራት መቀጣታቸው የተገለጸ ሲሆን  ከ3 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብም ተመላሽ በመደረጉ፣ ከምዝበራ ማዳን እንደተቻለ፣ ከክልሎቹ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡  
በአማራ ክልል በዓመቱ ውስጥ የመንግስትን ሀብት ያለ አግባብ መዝብረዋል ተብለው ለፍ/ቤት የቀረቡ 320 የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ከ3 ወር ቀላል እስራት እስከ 14 ዓመት ድረስ እንደተፈረደባቸው የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡ ጥፋተኛ ከተባሉ አመራሮች መካከል ከ200 ሺህ እስከ 350 ሺህ ብር መቀጮም እንዲከፍሉ የተወሰነባቸው እንዳሉ  ታውቋል፡፡ የተመዘበረ 14.5 ሚሊዮን ብር የመንግስት ገንዘብና ከ9400 ካሬ ሜትር በላይ መሬት ተመላሽ መድረጉንም የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጠቁሟል፡፡ በዚህ የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ፣ 186 መኖሪያ ቤቶች፣9 ድርጅቶችና 17 ተሽከርካሪዎች ጉዳያቸው እስኪጣራ  መታገዳቸውም ተነግሯል፡፡
መረጃ የተጣራባቸውን የመንግስት ባለስልጣናት ሁሉ በየደረጃው ተጠያቂ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ያስረዱት የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ም/ኃላፊ አቶ ፀጋዬ በቀለ፤ በህገ ወጥ የትምህርት ማስረጃ በየመንግስት መስሪያ ቤቱ በተቀጠሩ ግለሰቦች ላይም ማጣራት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የደቡብ ክልል መንግስት፣ 413 የመንግስት አመራሮችን በሙስና ጉዳይ ፍ/ቤት አቅርቦ፣ ከ3 ወር እስከ 17 ወር እስራት የተፈረደባቸው ሲሆን ከ105 ሺህ እስከ 3 መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ማስቀጣቱንም አስታውቋል፡፡ 291 ሚ. 299 ሺ 512 ብር ደግሞ ከመዝባሪዎች ማስመለሱን አስታውቋል - የክልሉ መንግስት፡፡ አንድ ሚሊዮን ካሬ ሜትር የከተማ ቦታም ተመላሽ ማስደረጉን የጠቆመው የክልሉ መንግስት፤በገጠርም 10ሺህ ሄክታር መሬት አስመልሻለሁ ብሏል፡፡

Read 3375 times