Sunday, 20 August 2017 00:00

በቤተ ክርስቲያኒቱ ሆስፒታል፣ ምዝበራ ፈጽመዋል የተባሉ ተባረሩ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

• ሆስፒታሉ በአገልግሎት ጥራት መጓደል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል
• ቅዱስ ሲኖዶስ፤ ሆስፒታሉ እንደ አዲስ እንዲደራጅ ትእዛዝ ሰጥቷል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ብቸኛ ሆስፒታሏን በአግባቡ መቆጣጠርና ማስተዳደር ባለመቻሏ ለከፍተኛ ምዝበራ መጋለጡን በሆስፒታሉ ላይ የቀረበ ሪፖርት ያረጋገጠ ሲሆን፤ ቋሚ ሲኖዶስ፤ ምዝበራ ፈጽመዋል የተባሉ ሐኪሞችና የአስተዳደር ሠራተኞች ተባርረው፣ ሆስፒታሉ እንደ ዐዲስ እንዲደራጅ ወስኗል፡፡  
በቤተ ክርስቲያኗ ገንዘብ ከ23 ዓመት በፊት የተቋቋመው የምግባረ ሠናይ ጠቅላላ ሆስፒታል፤ በቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ትኩረት ተነፍጎት በመቆየቱ ለግለሰቦች ምዝበራና መጠቀሚያ ውሏል፤ ይላል - የምርመራ ሪፖርቱ፡፡
ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ባለፈው ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ፤ በሆስፒታሉ ውስጥ አላግባብ የሚፈጸም የደመወዝ ክፍያን ጨምሮ በሆስፒታሉ ላይ ከፍተኛ ብክነትና ምዝበራ እየተፈጸመ መሆኑን ከሪፖርቱ መረዳቱን በመግለጽ፣ ምዝበራ ፈጽመዋል ያላቸውን የሕክምና ባለሞያዎችና ሌሎች ሠራተኞች  የሥራ ውላቸው ተቋርጦ እንዲሰናበቱ ትእዛዝ ሰጥቷል። ሆስፒታሉም የቤተ ክርስቲያኒቱን ማኅበራዊ ተልእኮ ለማሳካትና ሥራንና ሠራተኛን ለማገናኘት በሚያስችል መልኩ ዳግም እንዲደራጅ ወስኗል፡፡  
ሆስፒታሉ፣ በቂ ካፒታልና በጀት ሳይኖረው፣ የጡረታ ጊዜያቸው ያለፈ የአስተዳደር ሓላፊዎች ለራሳቸው ከፍተኛ የደመወዝ ጭማሪ በማድረግ፣ የሕክምና ባለሞያዎችን ሲበድሉ መቆየታቸውም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡ አሠራሩ የዘመድ አዝማድ በመሆኑም ተመሳሳይ የሞያ አገልግሎት በሚሰጡ ሐኪሞች መካከል ከፍተኛ የደመወዝ ልዩነት መኖሩን የሚጠቅሰው ሪፖርቱ፤ ሙሉ ጊዜያቸውን በሆስፒታሉ ተቀጥረው የሚሠሩ አንድ ሐኪም በወር 31 ሺሕ 943 ብር ሲከፈላቸው፣ በሳምንት ለተወሰኑ ቀናት ብቻ በትርፍ ጊዜያቸው የሚሠሩ ሌላ ሐኪም በአንጻሩ፣ 75 ሺሕ 169 ብር እንደሚከፈላቸው ይገልጻል፡፡
የሠራተኛ ቅጥርና ዕድገት ከሕግና መመሪያ ውጪ፣ ያለውድድርና ማስታወቂያ፣ በሥራ ሓላፊዎች የግል ይኹንታ ብቻ እንደሚፈጸም በሪፖርቱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ለሠራተኞች ተገቢው ሞያዊ ክብር ሳይሰጥ መቆየቱና የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ ተጠቁሟል። ለማጣራቱና ርምጃው መነሻ የሆነውን አቤቱታ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ያቀረቡት እማሆይ ምስጢረ ሥላሴ ከበደ፣ በነርስነት እያገለገሉ በትርፍ ጊዜያቸውና በግል ጥረታቸው ተምረው በጤና መኮንነት ተመርቀው የሞያ ፈቃድ ቢያገኙም፣ መድቦ ሊያሠራቸው አለመቻሉ በማሳያነት ቀርቧል፡፡ “የጤና መኮንነት የሞያ ሥራ ፈቃድ በሆስፒታሉ ውስጥ የሥራ መደብ ስለሌለው መድበን ልናሠራቸው አልቻልንም፤” በማለት ሥራ አስኪያጁ የሰጡት ምላሽም፣ ተገቢነትና ፍትሐዊነት የጎደለው ነው፤ ተብሏል፡፡ ሆስፒታሉን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ የሚቆጣጠር ሥርዓት ባለመዘርጋቱ፣ የሥራ አመራር ቦርዱም ተገቢ ክትትል ባለማድረጉ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ብቸኛ ሆስፒታል የመዘጋት አደጋ ላይ እንደጣለውም ታውቋል፡፡
በአጠቃላይ የሆስፒታሉ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ በጡረተኞች እጅ ከመውደቁ የተነሳ ከተቋማዊ ዕድገት ይልቅ የግለሰቦች ጥቅም እንዲንሰራፋ ዕድል መክፈቱን የሚገልጸው ሪፖርቱ፤ ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች ባለማሟላትና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉም  ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው ይጠቁማል፡፡ ማስጠንቀቂያውን ተከትሎ፣ ሆስፒታሉ ከተሰጠው ቀነ ገደብ በፊት ጉድለቱን ለማሟላት ያደረገው ጥረት እንደሌለና አፋጣኝ የእርምት ርምጃ መውሰድ ካልተቻለ፣ ቤተ ክርስቲያኗ ብቸኛ ሆስፒታሏን የማጣት አደጋ ተጋርጦባታል፤ ይላሉ - ምንጮች፡፡
አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት፣ ምንም እንኳን ርምጃው የዘገየ ቢሆንም፣ ቋሚ ሲኖዶሱ ሪፖርቱ በደረሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ “ምዝበራ ፈጽመዋል፤ ለሆስፒታሉ ዕድገት ማነቆ ሆነዋል፤” በሚል የተጠቆሙትና የተጠረጠሩት ሥራ አስኪያጁ፣ የፋይናንስ መመሪያ ሓላፊው፣ የንብረትና የሰው ኃይል መምሪያ ሓላፊው እና የትርፍ ጊዜ ተቀጣሪ ጡረተኛ ሐኪሞች በሙሉ የሥራ ውላቸው ተቋርጦ፣ ሆስፒታሉ በሞያ ብቁ በሆኖ ባለሞያዎች በድጋሚ እንዲደራጅና እንዲመራ መወሰኑ ትልቅ ርምጃ ነው፡፡ አሁንም ግን ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓትና ማኔጅመንት ማበጀት የግድ መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡

Read 4086 times