Sunday, 20 August 2017 00:00

“አፋን ኦሮሞ” ተጨማሪ የሀገሪቱ የስራ ቋንቋ እንዲሆን እየጣርኩ ነው- ክልሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

“አፋን ኦሮሞ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ነው”
   የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፤ “አፋን ኦሮሞ” የሀገሪቱ ተጨማሪ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ተግቶ እየሰራ መሆኑን፣ የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ አስታውቀዋል፡፡
የኦሮሞ ህዝብ በተደጋጋሚ “አፋን ኦሮሞ” የሀገሪቱ ተጨማሪ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ጥያቄ እያቀረበ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አዲሱ፤ የክልሉ መንግስትም ይኼን ከግንዛቤ በማስገባት ቋንቋው የፌደራል መንግስቱ ተጨማሪ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ “አፋን ኦሮሞ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ነው” ያሉት አቶ አዲሱ፤ ቋንቋው ከኦሮሚያ ክልል ወጭ ባሉ ሌሎች ክልሎችም በስፋት እንደሚነገር አብራርተዋል፡፡
በሃረሪ ክልል ከሃረሪ ቋንቋ ጋር እኩል የስራ ቋንቋ መሆኑን እንዲሁም በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የስራ ቋንቋ እንደሆነ  የጠቆሙት ሃላፊው፤የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ለአፋን ኦሮሞ በቴሌቪዥንና በሬድዮ የአየር ጊዜ መድቦ፣ ቋንቋው እንዲያድግና የህዝቦች ትስስር እንዲጠናከር በማድረግ ገንቢ ሚና በመጫወት ላይ ነው ብለዋል፡፡  ቋንቋውን ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚጎራበቱት፡- ሲዳማ፣ የም፣ ከፋ፣ቀቤና፣ ዳውሮ፣ ሃዲያ ቡርጂ፣ ጌዲኦና ኮንሶ፤ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ለመግባቢያነት እንደሚጠቀሙበት የጠቀሱት አቶ አዲሱ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በትግራይ (ራያ አካባቢ)፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ያሉ ህዝቦችም ቋንቋውን በእለት ተእለት ኑሮአቸው፣ ለመግባቢያነት በስፋት ይጠቀሙብታል ብለዋል፡፡ ቋንቋው በከፍተኛ መጠን ማደጉን የገለጹት አቶ አዲሱ፤በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች የሚነገር መሆኑ የህዝቦችን ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ መስተጋብሮች የበለጠ ያጠናክራል ብለዋል፡፡


Read 3912 times