Sunday, 20 August 2017 00:00

ቅዱስ ሲኖዶስ፤ የተሳሳተው የትግርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዳይሠራጭ አገደ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“በትግራይ በሃይማኖት ምክንያት የማይግባባ ማኅበረሰብ እየተፈጠረ ነው” /ምእመናን/

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ግድፈት አለበት በሚል በመቐለ ከተማና አካባቢዋ ሊቃውንትና ምእመናን ተቃውሞ የቀረበበት የትግርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዳይሠራጭ ያገደ ሲሆን፤ አተረጓጎሙና ይዘቱ በሊቃውንት ጉባኤ እንዲመረመር አዘዘ፡፡
የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በ2007 ዓ.ም. ያሳተመው የትግርኛ ትርጉም፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊትና ወንጌላውያን ኅብረት አብያተ ክርስቲያናት በጋራ ያሳተመችው ቢኾንም፤ ትግራይን ጨምሮ በማንኛውም አህጉረ ስብከት እንዳይሠራጭ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ለማኅበሩ ማስታወቁ ተገልጿል፡፡
የቋንቋ አጠቃቀም፣ አተረጓጎምና ይዘት፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሊቃውንት ጉባኤ እንዲመረመር ትእዛዝ የሰጠው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ “ውጤቱ ታይቶ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ኅትመቱ የታገደ መኾኑ እንዲታወቅ ለሚመለከተው ኹሉ ይገለጥ፤” ሲል ወስኗል፡፡
መጽሐፍ ቅዱሱ በትግርኛ ቋንቋ መተርጎሙ፣ ለኅብረተሰቡ አስፈላጊ እንደኾነ ቢታመንበትም የተዛባ መኾን እንዳልነበረበት በአቤቱታቸው የተቹት ሊቃውንቱና ምእመናኑ፤ በመላው ትግራይ መለያየትና ሁከት እየፈጠረ እንደኾነና ወደ ወረዳዎች የተበተነው የኅትመቱ ቅጅ እንዲሰበሰብ ወይም ማስተካከያ ደብዳቤ ወደ ኹሉም ወረዳዎች እንዲጻፍ፣ ካለፈው ግንቦት ጀምሮ ሲጠይቁ ቆይተዋል፤
ከ92 በመቶ በላይ የክልሉ ሕዝብ፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ በኾነበት፣ አተረጓጎሙ ለሌሎች የክርስትናው እምነቶች አስተምህሮ እንዲመችና መሠረታዊ ዶክትሪኗን በሚፃረር መልኩ መታተሙ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ከማኅበሩ ከምትጠቀም ይልቅ የምትጎዳበት እያመዘነ እንደመጣ ያመለክታል፤ ብለዋል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍቱን በጥንቃቄ የሚመረምር የሊቃውንት ጉባኤ በሀገርና በአህጉረ ስብከት ደረጃ ማጠናከርና ራሱን የቻለ የዲጅታል ኅትመት ተቋም እንድታቋቁምም ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ምእመናኑ፣ በመቐለ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅና በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን የእምነት ነጻነት እየተጋፉ ነው፤ ያሏቸው የሌሎች ቤተ እምነቶችና ምልምሎቻቸው ድርጊት ሳቢያ፣ “በሃይማኖት ምክንያት የማይግባባ ማኅበረሰብ እየተፈጠረ ነው፡፡ ይህም ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ለአገርም አለመረጋጋት የሚፈጥር ነው፤” ብለዋል ምእመናኑ፡፡ መቐለንና አካባቢዋን ጨምሮ ኵሓ፣ ፈለገ ዳዕሮ፣ ሓውሰዋ፣ ደንጎላትና ሌሎች የደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎች ችግሩ እንደሚታይባቸው ጠቅሰው፣ ሊወሰዱ ይገባሉ ያሏቸውን የጥንቃቄ ርምጃዎችም በአቤቱታቸው አመልክተዋል፡፡
መንፈሳዊ ኮሌጁ፣ ችግሩ ባለባቸው ደቀ መዛሙርት ላይ፣ ካለፈው 2008 ዓ.ም ጀምሮ የሚወስደውን የመለየትና የማጥራት ርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል፤ በተማሪዎች ምልመላ ጥንቃቄ እንዲደረግ፤ አስተዳደሩና መምህራኑም በጥልቀት እንዲጤኑ የሚሉት፣ በመፍትሔነት ከዘረዘሯቸው ተግባራት ይገኙበታል። የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና ሀገረ ስብከቱም፣ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡና ይህን አስመልክቶም በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ቀደም ሲል የተላለፉ ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲደረጉላቸው ምእመናኑ ጠይቀዋል፡፡

Read 2186 times