Sunday, 06 August 2017 00:00

በ150 ሚሊዮን ዶላር\ በነጃሺ ትልቅ ሪዞርት ሊገነባ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

 ነጃሺን ለመጎብኘት 200 ሺህ ናይጀሪያዊያን ተመዝግበዋል
                             
      ኦክሎክ ጀነራል ትሬዲንግ ከናይጀሪያዊ ባለሀብት ጋር በመተባበር፣በታሪካዊው ነጃሺ መስጊድ አቅራቢያ፣ በ150 ሚ. ዶላር ትልቅ ሪዞርት ሊገነባ ነው፡፡ 5 ሺህ አልጋዎች ይኖሩታል ለተባለው ለዚህ ዓለም አቀፍ ሪዞርት፤ የትግይ ክልል መንግስት 180 ሺህ ሄክታር መሬት ለባለሀብቶቹ መስጠቱንም የኦክሎክ ጀነራል ትሬዲንግ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አህመዲን መሀመድ ተናግረዋል፡፡
የዛሬ ሳምንት በአዜማን ሆቴል ሁለቱ ባለሀብቶች የሪዞርቱን ግንባታና ዝርዝር ሁኔታ በተመለከተ የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ ሲሆን በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ፣ የተለያዩ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ባለሀብቶችና የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ኦክሎክ ጀነራል ትሬዲንግ ከዚህ በፊት ቱሪዝም ላይ ያለውን ሥራ ለማዘመንና ተገቢውን አገልግሎት ለቱሪስቱ ለመስጠት መጀመሪያ የታክሲ አገልግሎት ደረጃ መሻሻል አለበት በሚል አቫንዛ “V8” ታክሲዎች ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት ለመንግስት ጥያቄ ማቅረቡን አቶ አህመዲን ገልፀዋል፡፡
ናይጄሪያዊው ባለሀብት ነጃሺ መስጊድን የሚጎበኙ 200 ሺህ ናይጄሪያውያንን ቀድሞ መመዝገቡን የገለፁት አቶ አህመዲን፤ ጎብኚዎቹ ከመምጣታቸው በፊት የታክሲና የሪዞርት ጉዳይ መቅደም እንዳለበትና ሪዞርቱ ከ2 ወር በኋላ ግንባታ እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡  
 በቱርክ ኢስታምቡል ውስጥ 20 ሺህ የቱሪስት ታክሲዎች እንዳሉ የጠቆሙት ባለሃብቱ፤ታክሲዎቹም ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸውን ገልጸው፣ ”ከእነሱ ጋር ስንነፃፀር እኛ ምንም የለንም” ብለዋል፡፡
ነጀሺ መስጊድ አጠገብ የሚገነባውን ሪዞርት በተመለከተም በመጀመሪያው ዙር 500 አልጋዎች ይገነቡና ቀስ በቀስ 5 ሺህ አልጋዎች ይኖሩታል ያሉ ሲሆን በቅርቡ ቱርክ በነበሩበት ጊዜ የቱርክ የእስልምና ም/ቤት ዋናው ኃላፊ “ከቱርክ በየዓመቱ 300 ሺህ ሀጃጆች መካ ይሄዳሉ፤ ሀጃጆቹ ሲሄዱ ወይ ሲመለሱ ነጃሺን ቢጎበኙ በቂ መስተንግዶ ታቀርባላችሁ ወይ?” ብለው መጠየቃቸውን ገልፀው፣ በአሁኑ ዓመት ባይደርስ እንኳን በቀጣዩ ዓመት የመጀመሪያውን 500 አልጋ አዘጋጅተን ጎብኚዎችን እንቀበላለን ብለዋል፡፡
ነጃሺ ላይ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ አገሪቱ ላይ የቱሪስት ፍሰትን ለመጨመር ቅድሚያ መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ ያሉት አቶ አህመዲን፤ አስፈላጊዎቹን ካሟላን ከቻይና ብቻ በየዓመቱ ለጉብኝት ከሚመጣው 60 ሚሊዮን ህዝብ የተወሰነውን ማስገባት እንችላለን ብለዋል፡፡ አክሎክ ጀነራል ትሬዲንግ በአፍሪካ ትልቁን “ህዳሴ ግራንድ ሞል” በ3 ቢ. ብር ለመገንባት፣ አክሲዮኖችን ሸጦ እየጨረሰና ቦታ እየመረጠ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ 

Read 1740 times