Saturday, 05 August 2017 12:05

አሜሪካ ስደተኞችን በዲቪ ዕጣ ሳይሆን በችሎታ ለመቀበል አስባለች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 አዲሱ አሰራር የህጋዊ ስደተኞችን ቁጥር በግማሽ ይቀንሳል ተብሏል

      ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ባለፈው ረቡዕ በይፋ ድጋፋቸውን የሰጡት አዲሱ የአገሪቱ የህጋዊ ስደተኞች አቀባበል ስርዓት ረቂቅ አዋጅ፣ የሴኔት ድጋፍ አግኝቶ የሚጸድቅ ከሆነ፣ አሜሪካ የዲቪ ሎተሪ ዕድለኞችን ከመላ አለም መሰብሰቧን ትታ፣ በተለያዩ መስፈርቶች የላቀ ውጤትና ችሎታ እንዳላቸው የተረጋገጡ፣ የተመረጡ ስደተኞችን ብቻ በመቀበል የመኖሪያ ፈቃድ መስጠት እንደምትጀምር ተዘግቧል፡፡
ኤንቢሲኒውስ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ ዕድልን ሳይሆን ችሎታን መሰረት ያደረገ የስደተኞች አቀባበልን ተግባራዊ ለማደረግ ታስቦ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ፤ በየአመቱ በህጋዊነት ወደ አሜሪካ የሚገቡ የተለያዩ የአለማችን አገራት ስደተኞችን ቁጥር በመጪዎቹ አስር አመታት ጊዜ ውስጥ በግማሽ ሊቀንስ ይችላል ተብሏል፡፡
አዲሱ አዋጅ በሴኔት ጽድቆ እንደ ህግ በስራ ላይ የሚውል ከሆነ፣ ስደተኞችን የምትቀበለውና የመኖሪያ ፍቃድ የምትሰጠው በዕጣ እና በኮታ ወይም በዘመድ አዝማድ መጠራራት ሳይሆን የተለያዩ መስፈርቶች ተጠቅማ እየገመገመች ነው ያለው ዘገባው፤ከእነዚህ መስፈርቶች መካከልም የስደተኞቹ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ፣ የትምህርት ደረጃና ዕድሜ እንደሚገኙበት አመልክቷል፡፡
ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በቅጡ መደገፍ የሚያስችላቸውን አካላዊ ብቃት መያዝና፣ በኢኮኖሚው ውስጥ የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክት ክህሎት ባለቤት መሆንም፣ በህጋዊነት ወደ አሜሪካ የሚገቡ የተለያዩ አገራት ስደተኞች፣ ከሚገመገሙባቸውና የመኖሪያ ፈቃድ ከሚያገኙባቸው ሌሎች መስፈርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
ሲኤንኤን በበኩሉ፤ ስደተኞችን ለመቀበልና የመኖሪያ ፈቃድ ለመስጠት መስፈርት የሚደረጉ መመዘኛዎችን በተመለከተ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዝርዝር ዘገባ፣ ዕድሜው ከ26 እስከ 30 የሆነ፣ የሌሎች አገራት የመጀመሪያ ወይም የዶክትሬት ዲግሪ ያለው እና የእንግሊዝኛ ችሎታው እጅግ ከፍተኛ የሆነ ስደተኛ፣ ወደ አሜሪካ የመግባትና የመኖሪያ ፈቃድ የማግኘት እድሉ እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡
የኦሎምፒክ ሜዳይ ባለቤቶች ወይም የኖቤል ሽልማት ተሸላሚዎች የሆኑ የሌሎች አገራት ስደተኞችም፣ ከሌሎች በተለየ ወደ አሜሪካ የመግባትና የመኖሪያ ፈቃድ የማግኘት እድላቸው ከፍ ያለ እንደሚሆንም ዘገባው ገልጧል፡፡
በየአመቱ የመኖሪያ ፈቃድ የሚሰጣቸውን ስደተኞች ቁጥር 50 ሺህ ለማድረስ ያለመውና ባለፈው የካቲት ወር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰምቶ ሲያወዛግብ የነበረው ረቂቅ አዋጁ፤ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባለፈው ረቡዕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በእጅጉ እንደሚደግፉትና ለተግባራዊነቱ እንደሚሰሩ በይፋ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ እንደገና የውዝግብና የውይይት አጀንዳ መሆን መጀመሩንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ናሽናል ኢሚግሬሽን ፎረም የተባለው የአገሪቱ ቡድን በበኩሉ፤ በመጪዎቹ 3 አመታት ጊዜ ውስጥ የ7.5 ሚሊዮን ሰራተኞች ዕጥረት እንደሚገጥማት በተነገረላት አሜሪካ፤ከፍተኛ የሰራተኛ የሰው ሃይል ምንጭ የሆነውን የህጋዊ ስደተኞች ፍሰት የሚገታውን ይህን አዋጅ ማጽደቅ፣የአገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ የሚጎዳ አደገኛ እርምጃ ነው ማለቱን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል። ረቂቅ አዋጁ ከፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኞች ከፍተኛ ትችት እየተሰነዘረበት ነው ያለው ዘገባው፤ ረቂቅ አዋጁ እንደታሰበው በምክር ቤት ጸድቆ ስራ ላይ የመዋል ዕድሉ እጅግ ጠባብ ነው እየተባለ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡

Read 3331 times