Sunday, 06 August 2017 00:00

በጓደኞቻቸውና በሙያ አጋሮቻቸው አንደበት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 “ራሱን ለሙያ ታሪክ የፈጠረ ሰው ነው”
(አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ)
ከተስፋዬ ሣህሉ ጋር የምንተዋወቀው ከ65 ዓመታት በፊት ነው፡፡ እሱ ሙዚቀኛም ነው፡፡ ደራሲም ነው፡፡ የምትሃት ትርኢት አቅራቢ፣ ዳንሰኛ፣ ቲያትረኛ፣ ድምፃዊ፣ የመሣሪያ ተጫዋችና የበርካታ ሙያዎች ባለቤት ነው፡፡ በቀብር ሥነስርዓቱ ላይ በተነበበው የህይወት ታሪኩ ቅሬታ አለኝ፡፡ ስለ እሱ ብዙ ያልተባለና ያልተነገረለት ታሪክ አለው፡፡
እኔ ከዓመታት በፊት የህይወት ታሪኩን በ300 ገፆች ፅፌ ለህትመት ዝግጁ አድርጌው ነበር፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ሣይታተም ቀርቷል፡፡ አንድ ቀን ግን እንደሚታተምና አንባብያን እጅ እንደሚደርስ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ተስፋዬ ብዙ ሰው ነው፡፡ በ65 ዓመት የትውውቅ ጊዜያችን የማውቀው ተስፋዬ፤ የብዙ ሙያዎች ባለቤት፣ ሁለገብ አርቲስትና ለሙያው የተሰጠ ሰው ነው፡፡ በቀብር ሥነስርዓቱ ላይ ለህዝብ የተነበበው ታሪክ ግን በጣም ግራ አጋብቶኛል፡፡ ምን ማለት ነው? እስከ ማለት ደርሻለሁ፡፡ ስለ ተስፋዬ ልጆች የቀረበው ታሪክና መረጃ የተሳሰተ ነው፡፡ እሱ ብዙ ሊባልለት የሚገባ ታላቅ የአገር ሀብት ነበር፡፡
“የመጀመሪያው እያጎ እሱ ነበር”
(ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ)
ተስፋዬ ሣህሉ ከአበባ ተስፋዬነቱ፣ ከተረት አጫዋችነቱ በበለጠ ድምፃዊነቱ፣ የአስማት ትርኢት አቅራቢነቱ፣ የመድረክ ተዋናይነቱ፣ የመሣሪያ ተጫዋችነቱ፣ ደራሲነቱና የበርካታ ሙያዎች ባለቤትነቱ ገዝፎ ይታያል፡፡ በመድረክ ላይ ራሱን ለውጦ ሲታይ እጅግ የሚያስደንቅ ችሎታ እንዳለው ያስታውቃል፡፡ በኦቴሎ ቲያትር ላይ የመጀመሪያው እያጎ ሆኖ የሠራው እሱ ነው፡፡ የከርሞ ሰውን የመሰለ የፀጋዬ ገብረመድህንን ተውኔት በመሪ ተዋናይነት ተውኗል፡፡ አባተ መኩሪያ ባዘጋጀው የኤዲፐስ ንጉስ ቲያትር ላይም በተዋናይነት ሰርቷል፡፡ Mid Summer Night Dream በተባለው ላይ የሚገርምና አስቂኝ ተውኔት ላይ አስገራሚ ችሎታውን አሳይቷል፡፡ በአስማት ትርኢት አቅራቢነቱም ይታወቅ ነበር፡፡ ኮሪያም ክራር ይዞ ዘምቷል፡፡ በግል ባህርይው ጨዋ ዲሲፒሊን የነበረው መልካም ሰው ነበር፡፡ ለነገሩ ይህን ያህል ዕድሜ እንዲሁ በቀላል የሚገኝ ነገር አይደለም፡፡
“ሙሉ በኩሉኤ የሆነ ሰው ነው”
 (አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ)
ተስፋዬ የአንድ ሙያ ባለቤት ብቻ አልነበረም፤ሁለገብ ነበር፡፡ ያልሞከረው ሞያ፣ ያልሠራው ነገር አልነበረም፡፡ በእርግጥ ለእኛ በእድሜ ታላቃችን ነው- በጣም የምናከብረው፣ የምንወደው ሰው ነው፡፡ የበርካታ ሙያዎች ባለቤትነቱ  በጣም አስገራሚ ነው፡፡ በትወና ሙያ ቁጥር አንድ አክተር ነው፣ ባህላዊም ዘመናዊም ሙዚቃዎችን ይጫወታል፤ ደራሲ ነበር፣ የአስማት ትርኢቶችንም ይሠራ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ሙሉ በኩሉኤ የሆነ ሰው ነበር፡፡ ቁንፅል ችሎታ አልነበረውም፡፡ ምንም ነገር ሰርቶ ማሳመን የሚችል ታላቅ የሙያ ሰው ነበር፡፡

Read 1275 times