Sunday, 06 August 2017 00:00

“የከሸፉት” 4ቱ የነገስታቱ የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(3 votes)

   ክፍል ፩ – የእነ ዘርዓያዕቆብ ፍልስፍናና የአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት
                                 
      የሀገራችን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ በዋነኛነት የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይሄንንም ዕድል በመጠቀም በአሁኑ ወቅት አውሮፓውያንና ቻይኖች ወደ ሀገራችን በብዛት እየመጡ ይገኛሉ። “አውሮፓውያኖችና ቻይኖች ለኢትዮጵያውያን ሊሰሩ መጡ” የሚለውን ነገር አፄ ኢዛናና አፄ ካሌብ ቢሰሙ እጅግ ያዝኑብናል፡፡ አፄ ኢዛናና አፄ ካሌብ በኖሩበት ዘመን የአክሱም ሥልጣኔ ከቻይናውና ከግሪኮ-ሮማን ሥልጣኔ ጋር ተስተካካይ ነበር፤ የንግድ ግንኙነታቸውንም ሲያከናውኑ የነበሩት በእኩልነት መንፈስ ነበር፡፡ ዛሬ ግን እኛ ወደ ኋላ ተንሸራተን ወድቀን ስንቀር፣ እነሱ ግን ከወደቁበት ዳግም ተነሱ፤ በአንድ ወቅት የኛ ተስተካካይ የነበሩ ሀገሮችም ዛሬ ላይ መጥተው ለኛ እንዲሰሩልን እንለምናቸዋለን፡፡
ከ19ኛው ክ/ዘ ጀምሮ የነገሱት ነገስታት ይሄንን ኋላቀርነታችንን በመገንዘብ፣ ከውድቀታችን እንድናንሰራራና ዳግም ወደ ሥልጣኔም እንድንመለስ የተለያዩ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ ይሄንን ሁኔታችንን ቀድመው የተረዱትና የመጀመሪያውን ሙከራ ያደረጉት ደግሞ አፄ ቴዎድሮስ ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት፣ የኢትዮጵያን ባህላዊ ማህበረሰብ ወደ ዘመናዊ ማህበረሰብነት ለማሸጋገር ከአፄ ቴዎድሮስ (1850) ጀምሮ በየ50 ዓመቱ አራት የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች ሲሞከሩ ቆይተዋል፤

የአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት — ምዕራባዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ሀገር ውስጥ በማምረትና የዕውቀት ሽግግርን ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡
የአፄ ምኒልክ የዘመናዊነት ፕሮጀክት — ምዕራባዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን ዓላማው ያደረገ ነበር፡፡ ሆኖም ግን የሰለጠነ የሰው ኃይል ስላልነበረን አልተሳካም፡፡
የአፄ ኃይለ ስላሴ የዘመናዊነት ፕሮጀክት — የፈረንጅ ትምህርትን በማስፋፋት ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ዓላማውም የሰለጠነ የሰው ኃይል ማግኘት ነበር፡፡
የአብዮቱ (የተማሪዎች) የዘመናዊነት ፕሮጀክት — ይህ ፕሮጀክት ከሀገር ልማድና ባህል በመነቀልና ርዕዮተ ዓለምን ከውጭ በመበደር የተሞከረ ፕሮጀክት ሲሆን ደርግና ኢህአዴግ የዚህ ፕሮጀክት አስፈፃሚዎች ናቸው፡፡ የታሪክ ተመራማሪው ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማሪያም ይሄንን የተማሪዎችን የዘመናዊነት ፕሮጀክት እንዲህ ይሉታል፡-
በ1960ዎቹ የተነሳው ፍፁም በባዕድ አምልኮ ላይ የተመሰረተው አብዮታዊ አመፅ፣ ብሄራዊ ታሪክንና ባህልን እንደ አሮጌ ቁርበት አሽቀንጥሮ እንዲጥል አደረገው፡፡ በዚህም ምክንያት የተማሪዎቹ የዘመናዊነት መንፈስ  በሀገሪቱ ላይ የማይጠገን የታሪክ ውልቃት አስከትሏል፡፡
በሁለት ተከታታይ ክፍል በማስነብባችሁ መጣጥፌ ላይ ከ4ቱ ከከሸፉት የዘመናዊነት ፕሮጀክቶቻችን ውስጥ መጀመሪያ የአፄ ቴዎድሮስን ሙከራ፣ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ የአፄ ኃይለ ሥላሴ የዘመናዊነት ፕሮጀክትን እንመለከታለን፡፡ እግረ መንገዴንም የአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ከ17ኛው ክ/ዘ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ጋር ያለውን የመንፈስ ዝምድና ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
ዘመናዊነት ልማድን በመፈተሽ በዕውቀት (በአመክንዮ) ላይ የተመሰረተ የአኗኗር ዘዴ ነው፡፡ ዕውቀት ደግሞ በተፈጥሮ ላይ የበላይነትን በመቀዳጀት ኑሮን ያሻሽላል፣ በሌሎች ህዝቦች ላይም የበላይነትን ያመጣል፡፡ እንግዲህ የነገስታቱ ጥረት እንደዚህ ዓይነቱን ከፍ ያለ የአኗኗር ዘዴ ለሀገራችን ህዝቦች ለማስለመድ ነበር፡፡
ዘመናዊነት ከልማድ ይልቅ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ኑሮ በመሆኑ፣ ከዓለማዊ ትምህርት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሺ ዓመታት ትምህርት ሲሰጥ የነበረው በገዳማትና በመስኪዶች ሲሆን በይዘቱም ሙሉ በሙሉ ሃይማኖታዊ ብቻ ነበር። አፄ ቴዎድሮስ ግን ከሃይማኖት ተቋማት ውጭ የሆነ ቤተ መፃህፍት መቅደላ ላይ ማቋቋማቸውና ጋፋት ላይም ዘመናዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የዕውቀት የሽግግር ማዕከል በማቋቋም ከመንፈሳዊው ዕውቀት ጎን ለጎን ዓለማዊ ዕውቀትም እንዲስፋፋ ሙከራ አድርገዋል። “የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ከ1947-1983” በሚለው መፅሐፋቸው ውስጥ ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ እንዲህ ይላሉ፡-
ንጉሱም በጋፋት ት/ቤት እንዲከፈት አድርገው፣ ወጣት ኢትዮጵያውያን የቀለምና የሙያ ትምህርት እንዲሰጣቸው አዘዙ፡፡ ሚስዮናውያንም የረሱትን የሳይንስ ትምህርት እየከለሱ፣ ከብዙ ሙከራ በኋላ ንጉሱ የፈለጓቸውን መሳሪያዎች መስራት ጀመሩ፡፡
ይህ ዓለማዊ ዕውቀትንና የትምህርት ማዕከላትን የማስጀመሩ የአፄ ቴዎድሮስ ሙከራ ከፈላስፎቻችን ከዘርዓያዕቆብና ከወልደ ህይወት ጥረት 200 ዓመታት በኋላ የተደረገ ነው፡፡ እነዚህ ፈላስፎች ለኢትዮጵያ ህዝብ ዕድገት የሚጠቅመው ከመንፈሳዊ ትምህርቶች ጎን ለጎን ዓለማዊ ዕውቀትና ትምህርት ሲስፋፋ እንደሆነ ገና በ17ኛው ክ/ዘ ላይ ነው ሲከራከሩ የነበሩት። ለምሳሌ፡- ወልደ ህይወት በሐተታው ምዕራፍ 17 ላይ እንዲህ ይላል፡-
ትምህርትን በመማር ደካማ አትሁን፤ በመላ የህይወት ዘመንህም አትተዋት፡፡ … በአንድ ትምህርት መኖርም ትዕቢተኛ ስለሚያደርግ ብዙ ሙያዎችን እንድታገኝበት ትምህርት የተባለውን ሁሉ ተማር፡፡ ልክ ንቦች የተለያዩ መዓዛ ያላቸውን አበቦች እየቀሰሙ ጣፋጭ ማር እንደሚሰሩ ሁሉ፣ አንተም ከተለያዩ ትምህርቶች ሁሉ ጥበብን ሰብስብ፡፡
ፕ/ር አንድሪያስ፡- The Uniqueness of Modernity በሚለው ትምህርታቸው ላይ አፄ ቴዎድሮስን የመጀመሪያው “ዘመናዊ” ንጉስ ይሏቸዋል፤ ምክንያታቸው ደግሞ “የዘመናዊነት መገለጫዎች” ንጉሱ ላይ ስለሚንፀባረቅባቸው ነው፡፡ ፕ/ር አንድሪያስ ለዚህ አባባላቸው ሁለት ነገሮችን እንደ ማሳያ ይጠቅሳሉ፡-
የመጀመሪያው፣ ንጉሱ ሃይማኖት በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ቦታ ይጠይቃሉ፡፡ ተፅዕኖውም እንዲቀንስ ይታገላሉ፡፡ ሁለተኛ፣ ንጉሱ የራሳቸውን ዘመንና ህዝብ ከሌላው ዓለም ህዝብ ጋር ማነፃፀራቸው ነው፡፡ የራስን ህዝብ ከሌላው ጋር ማነፃፀር በቅድመ ዘመናዊነት ጊዜ አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ንፅፅር የተጀመረው በአፄ ቴዎድሮስ ነው፡፡ በዚህም ንጉሱ በህዝቡና በሀገራቸው ኋላቀርነት አብዝተው ይበሳጩ ነበር፡፡
በርግጥም የአፄ ቴዎድሮስ ብስጭት ልኬት አልነበረውም፤ ንጉሱ ለእንግሊዟ ንግስት ቪክቶሪያና ለራሳም (የቪክቶሪያ መልዕክተኛ) በተደጋጋሚ የፃፉት ደብዳቤ ላይ ለዘመናዊነት ያላቸውን ጥማት ሲገልፁ፡- “እኛ በድንቁርና የታወርን እውሮች ነን፤” በማለት ነበር። አፄ ቴዎድሮስ በተለያየ ጊዜ ከተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች ውስጥ የህዝባቸውን ድንቁርናና ኋላ ቀርነት እንዲህ በማለት ሲገልፁት ነበር፡-
ጥር 1858 — “የኢትዮጵያ ሰዎች ድንቁርናችንንና እውርነታችንን ሳይሰሙት አይቀሩም፤”
መጋቢት 1858 — “አሁንም እኔ የምፈልገው እውር ነኝና አይኔ እንዲበራ ጥበብ ነው፡፡”
ሚያዚያ 1858 — “የኢትዮጵያ ሰዎች እውር ነንና አይናችንን ያብሩልን፣ እግዚአብሔር በሰማይ ያብራልዎ!!”
ሚያዚያ 1859 — “ከብት አለመፈለጌ ክብር (ሀብታም) ሁኜ አይደለም፡፡ እውር አህያ ነኝና ለጥበብ አይኔን ትከፍቱልኝ ብዬ ነው እንጂ በእግዚአብሔር ኃይል፡፡”
መቼም በኢትዮጵያ የነገሥታት ታሪክ ውስጥ እንደ አፄ ቴዎድሮስ የሚያስቆጭም ሆነ የሚያሳዝን ንጉስ የለም፡፡ አፄ ቴዎድሮስ የአንድ ሀገር መሪ ሆነው ሳለ፣ የመሪነት ክብራቸው ሳያስጨንቃቸው ራሳቸውን “እውር”፣ “ደንቆሮ” እና “አህያ” እያሉ ለውጭ መንግስታት ደብዳቤ መፃፋቸው፣ የህዝባቸው ኋላ ቀርነት ምን ያህል እንደሚያበሳጫቸውና ሀገራቸውንም ወደ ድሮው ገናናነቷ ለመመለስ የነበራቸውን የሚያንዘፈዝፍ ቁጭት ያሳያል፡፡
አፄ ቴዎድሮስ ከዚህም አልፈው አውሮፓውያን ሰራተኞችን በከፍተኛ ደሞዝና የኑሮ አበል ጎንደር ላይ አቀማጥሎ ለማኖር ቆርጠው መነሳታቸውን፣ በ1858 በማርቲን ፕላውደን በኩል በመላው አውሮፓ የበተኑት ክፍት የሥራ ማስታወቂያ ያስረዳል፡-
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ፣
የእግዚአብሔር ፍጡር ባሪያው የዳዊት የሰለሞን ልጅ፤ ንጉሰ ነገስት ቴዎድሮስ ዘኢትዮጵያ፤
አቶ ፍላጥንን በአይሮጳ ልኬ ሰድጀዋለሁ፡፡ ብልህ ሰራተኛ ፈልጌያለሁ፡፡ ወደኔ የሚመጣን ሰራተኛ ሁሉ በደስታ እቀበላለሁ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እኖራለሁ ካለም ደስ አሰኝቼ አኖረዋለሁ፤ ብልሀቱንም አስተምሮ ወደ ሀገሬ እመለሳለሁ ቢል ደመወዙን ሰጥቼ ደስ አሰኝቼ እሰደዋለሁ፡፡ በእግዚአብሔር ኃይል የእግዚአብሔር እምነት ይሁንብኝ፡፡
አፄ ቴዎድሮስ አላወቁም እንጂ አይን የሚያበራ ዕውቀትስ፣ በሀገራቸው ልጆች ሀገራቸው ላይ ከ200 ዓመታት በፊት ተጀምሮ ነበር፡፡ አፄ ቴዎድሮስ፣ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት ስለሚባሉ ፈላስፎች ቢሰሙ ኖሮ፣ አውሮፓውያንን ያን ያህል መለማመጥ አያስፈልጋቸውም ነበር፡፡
የአፄ ቴዎድሮስን የዘመናዊነት መንፈስ የፈጠረው ራሳቸውን ከአውሮፓውያን ጋር ማነፃፀራቸው ነው። ሆኖም ግን ፕሮጀክታቸውን የሚያስቀምጡበት የባህል መሰረት ስላልነበረን፣ የንጉሱ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ሊሳካ አልቻለም፡፡ ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ፤ የአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት የተጨናገፈበትን ምክንያት ሲጠቅሱ እንዲህ ይላሉ፡-
ከዘመነ መሳፍንት የወረስነው ማህበራዊና ፖለቲካዊ መዋቅር አፄ ቴዎድሮስን ብዙም ሊያራምዳቸው አልቻለም፡፡ በመሆኑም፣ ንጉሠ ነገሥቱ የጀመሯቸው ወታደራዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ መሰረት ስላልነበራቸው አየር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡
ሆኖም ግን አፄ ቴዎድሮስ የገጠማቸው ችግር ፕ/ር ባህሩ ከሚሉት “የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ መሰረት ማጣት” የጠለቀ ነው — ራሱ ኢኮኖሚውና ቴክኖሎጂው የሚቆምበት ሌላ መሰረት ይፈልጋልና። አፄ ቴዎድሮስም ያጡት ያንን “መሰረታዊ” የሆነ መሰረት ነው፤ እሱም የባህል መሰረት ነው — የሰውን ልጅ ማዕከል ባደረጉ ዓለማዊ ዕውቀቶች የበለፀገና በፍልስፍና የበራየ የባህል መሰረት፡፡ አፄ ቴዎድሮስ መጨረሻ ላይ እንግሊዞች ሲመጡባቸው የተናገሩትም ይሄንኑ ነው፡-
ያገሬን ህዝብ ገብር ብለው፣ ሥርዓት ያዝ ብለው ተጣላኝ፤ እናንተ ግን በሥርዓት የተመራ ህዝብ ስላላችሁ አሸነፋችሁኝ፡፡
ዘመናዊነት ራሱን የቻለ “ሥርዓት” ይፈልጋል፤ ዘመናዊነትን ለመቀበል በሥርዓት ተገርቶ የተዘጋጀ (Disciplined) ህዝብ ይፈልጋል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ፤”ያገሬን ህዝብ ሥርዓት ያዝ ብለው ተጣላኝ” ያሉት በህዝቡ ውስጥ ዘመናዊነትን መሸከም የሚችል የባህል መደላድል ገና ስላልተፈጠረ እንደሆነ ስለገባቸው ነው፡፡
በመሆኑም አፄ ቴዎድሮስ ይበልጥ ሲያስቸገራቸው የነበረው የዘመናዊነት ፕሮጀክቱ ሳይሆን ፕሮጀክቱን የሚያስቀምጡበት መሬት ነበር የቸገራቸው፤ ፕሮጀክቱን ለማስቀመጥ የሚያስፈልገውን የባህል መሰረት ለማስተካከል፣ ከካህናቱና ከህዝቡ ጋር መታገሉና መጣላቱ ነበር ይበልጥ ያስቸገራቸው፡፡
የአፄ ቴዎድሮስን የዘመናዊነት ፕሮጀክት ሊሸከም የሚችለው ነባሩ ሀገራዊው ልማድ ሳይሆን የእነ ዘርዓያዕቆብ የስነ ሰብዕ (Humanities) ትምህርት ብቻ ነበር፡፡ የፈላስፎቻችን ጥረት ለዘመናዊነት ተመቻችቶ የተገራ ማህበረሰብና ባህል መፍጠር ነበር፡፡
እንግዲህ ፈላስፎቹ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት እጅግ አስፈላጊ ሆነው የሚመጡት እዚህ ጋ ነው። እነዚህ ፈላስፎች ሲታገሉ የነበሩት በኋላ ላይ አፄ ቴዎድሮስ የሚፈልጉትን የባህል መሰረት አስቀድሞ ለማንጠፍ ነበር - በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ማህበረሰብን ለመፍጠር፡፡ ለምሳሌ አፄ ቴዎድሮስ ከተቸገሩበት ነገር አንዱ፡- የእጅ ሙያን እየናቁና የአንድ ጭቃ ሹም ወታደር እየሆኑ፣ በገበሬው ትከሻ ላይ ያለ ስራ መኖር ነው፡፡ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት፣ ይሄ ነገር እንዲቀር፣ ከአፄ ቴዎድሮስ 200 ዓመት ቀድመው ሲያስተምሩ ነበር፣ እንዲህ በማለት፡-
ደግሞም በዚህ ዓለም ሕይወታችንንና ኑሯችንን እንድንንከባከብ የፈጣሪ ፍላጎት ነው፡፡ እሱ ፈጣሪያችን፣ ንብረታችንን በዕውቀታችንና በሥራ እንድናሳምረው ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ለዚህ የሚሆን ልቦናና ችሎታ ሰጥቶናልና። ስለዚህም የእጅ ሥራን መስራት የፈጣሪ ፈቃድ ነው፤ ምክንያቱም ያለ ተግባረ ዕድ ለሕይወታችን የሚያስፈልገንን ማግኘት አንችልም። (ሐተታ ዘርዓያዕቆብ ምዕራፍ 8)
ወልደ ህይወትም በሐተታው ምዕራፍ 18 ላይ እንዲህ ይላል፡-
የእጅ ሙያን ውደድ እንጂ የጉልበት ስራ ለባሮች ነው አትበል፤ ቀጥቃጭነትና ግንበኝነትም ለመሳፍንት ልጆች አይገባም አትበል፡፡ ... ደግሞም ሥራን ትግል አታድርገው፤ ነገር ግን ሥራህ ላይ የተለያዩ ፈጠራዎችን እየጨመርክበት፣ ድካምህን ቀንስ፣ ጥቅምህንና ትርፋማነትህንም ከፍ አድርገው፡፡
መቼም ይሄ ትምህርት፣ የእጅ ሙያን እያንቋሸሽን ለዘመናት ማረሻዎቻችንን መቀየር ላቃተንና በምግብም ራሳችንን መቻል ላቃተን፣ ለእኛ ትልቅ መልዕክት ነው፡፡ ትምህርቱ ሁልጊዜ የሥራ መሳሪያዎቻችንን እንድናሻሽልና በቴክኖሎጂም ይበልጥ እየተራቀቅን እንድንሄድ የሚያሳስብ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፤ “መክሸፍ አንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በሚለው መፅሐፋቸው ላይ “የሥራ መሳሪያዎቻችንን ሳንቀይር ስንት ዘመናት አለፉ?” እያሉ ትውልዱን ከመውቀሳቸው 350 ዓመታት በፊት በአንድ እንፍራንዛዊ ፈላስፋና መምህር የተፃፈ ትምህርት ነው።
አፄ ቴዎድሮስ እንደዚህ ዓይነቶቹን ባህሉን የሚያስተካክሉና ህዝቡንም ለዘመናዊነት የሚያዘጋጁ መምህራንን ነበር ያጡት፡፡ የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት ፍልስፍና ቢቀጥልና ፈላስፎቹ የሚያልሙትን ዓይነት ማህበረሰብ ቢያንስ እነሱ በኖሩበት ጎንደር ላይ ቢፈጥሩ ኖሮ ያለ ምንም ጥርጥር የአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ይሳካ ነበር፡፡ እኛም ልክ እንደ ዛሬው፣ ንጉስ በተቀያየረ ቁጥር አብሮ የሚቀየር፣ የዘመናዊነት ፕሮጀክት መሞከሪያ አንሆንም ነበር፡፡
ከአዘጋጁ፡- (ጸሃፊው “የፍልስፍና ፩ እና ፪” መፅሐፍት፣ ደራሲ ሲሆን በኢ-ሜል አድራሻው  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡)

Read 2028 times