Sunday, 06 August 2017 00:00

የሰይጣን ማመልከቻ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(15 votes)

 በንዴት የተጻፈ የሚመሥል፣ አልፎ አልፎ የእምባ ጠብታ ምልክቶች ያሉበት ማልከቻ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ተቀምጧል፡፡ ፊርማው ሙንጭርጭር ነው፡፡ ብሦት ያለበት ይመስላል፡፡
አንዴ ማመልከቻውን አየና፣ ከዙፋኑ መግቢያ ፊት ከቆመው ሊቀ መልዐክ ወዲህ ያለውን ሚካኤልን ተመለከተ፡፡ ሚካኤል ጦረኛ ነው፡፡ ሦስቱ ሊቀ መላዕክት፣ በስልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ፣ ሊሲፈር የሙዚቃው ዘርፍ ኃላፊ ሲሆን ሚካኤል እንዲሁ ሲሦውን ይዞ የሚመራው የጦር ኃይል ያለው ነው። ገብርኤል ሲሦስውን ይዞ፣ ዋና ሥራው ብሥራት ነጋሪ ነው፡፡
ታዲያ ትዝታም አላቸው፡፡ ሰይጣን አምጾ ከወደቀ በኋላ ገብርኤል የዳንኤልን የፀሎት መልስ ይዞ ሲሄድ፣ ሊሲፈር የአየር ለይ ሰራዊቱን አሰልፎ፣ ለሃያ አንድ ቀናት ተዋግቶት ነበር፡፡ በኋላ ነገሩ እየከረረ ሲመጣ፣ ሚካኤል ከእነ ሠራዊቱ ተልኮ፣ የሰይጣንን ኃይል ድባቅ በመምታት፣ ለገብርኤል ፋታ ሰጠውና፣ የዳንኤልን የፀሎት መልስ አድርሶ ተመለሰ፡፡
ዛሬም ሚካኤል፤ በሉሲፈር ማመልከቻ ደስተኛ አይደለም፤ ተቆጥቷል፡፡ በዚያ ላይ ፀባዩን ያውቃል። ያኔም እንደነርሱ የአእላፋት ሰራዊት አለቃ ሳለም አይረካም፡፡ ሙዚቀኛ ስለሆነ ይቅበጠበጣል። በማይገባ ቦታ ያፏጫል፣ ዳንስ ይቃጣዋል፡፡ ሀሳቡን ይቀያይራል፡፡ አዳዲስ ነገር ይወድዳል፣ ማንም እንዲያዝዘው የማይፈልግ እብሪተኛ ነው። ከእግዚአብሔር መንግሥት የነቀለውም ራሱን አምላክ አድርጎ የመሾም ጥማቱ እንደሆነ ያውቃል፡፡
“አነበብከው ሚካኤል!”
ጎንበሥ ብሎ ሰላምታ ከሰጠ በኋላ፤
 “..አዎ…አንብቤዋለሁ”
“እና ምን ተሰማህ?”
“ደንቆኛል ጌታዬ! … ምን እንደፈለገ አይገባኝም! … ለምን ሁልጊዜ የሌሎችን እንደሚመኝ ግራ ይገባኛል… ሥራ ስለበዛብኝ ኃይል ይጨመርልኝ ነው የሚለው፡፡ ምን ማለት ነው? … ከኔና ከገብርኤል ሰራዊት፣ ለእርሱ የሚታዘዝ ጭፍራ ይፈልጋል ማለት ነው?”
እግዚአብሄር ዝም ብሎ ከአደመጠው በኋላ፤
“እና ምን ይሻላል? … ምን መልስ ቢሰጠው ትወዳለህ?
“እናጥፋው! … እናስወግደው!”
ከት ብሎ ሳቀ፣ እግዚአብሔር፡፡
“ከዚያስ … ምን የሚፈጠር ይመስልሃል?”
“ሰላም---ጤና---እረፍት!”
“ለእናንተ ሊሆን ይችላል፤ ለሰው ልጅ ግን እንደዚያ አይደለም ... ይህ የምትለው ቢሆን የአዳም ዘር፣ ሌላ አመፅ ይጀምራል”
“እና ጌታ ሆይ፤ አንተ ታውቃለህ! ….”
“አሁን የተሰጠው ዕድል ቢቀጥል ደግ ነው፤ የወደደ ይከተለው፤ ያልወደደ ያሳድደው፤ ይቃወመው”
“መች አርፎ ተቀመጠ? … ኃይል ይጨመር እያለ’ኮ ነው … ዓለምን ጠቀለልኩ ለማለት ነው”
“አይደለም፣ የሰው ልጅ ሸቀጥና ሀብት ፍለጋ በማመልከቻ አጨናነቀው መሰለኝ፣ በብልሃትም ከርሱ እየበለጡ ያዳገተው ነገር አለ፤ እስቲ አንዴ አንብበው ደግመህ--”
ፈጣሪ ሆይ! … እንደምታውቀው ካንተ ዘንድ በስህተቴ፣ ከተወገድኩ በኋላ የራሴን ቢዝነስ በታታሪነት እየሰራሁ ሺህ ዓመታት አሳልፌያለሁ። አንዳንዴ ያቀድኳቸው ዕቅዶች እየተሳኩልኝ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እየፈረሱብኝ፣ ጥሩ በሚባል ሁኔታ የመንግስቴን ፅናት አስቀጥያለሁ፡፡ ሌት ተቀን ያለ እረፍት በመስራት፣ ከአንተ ወዳጆች ጋር አንገት ላንገት ተናንቄ፣ ወዳጆቼን በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች በመደጋገፍና በማደራጀት እየሰራሁ ነው፡፡
አሁን አሁን ግን ግዛቴን በሚገባ ካደራጀሁ በኋላ፣ ወዳንተ ወዳጆች ሰፈር ሰርጎ ገቦችን በመላክ የጀመርኩት ተልዕኮ ተሳክቶ፣ አሁን ከራሴ ክልል ይልቅ የሃይማኖቶቸው አካባቢ የተሳካ የሥራ መስክ ሆኖልኝ፣ በስኬት እየተንቀሳቀስኩ ነበር፡፡ ይሁንና አሁን በቅርቡ ግን የአቅም ችግር እየደረሰብኝ ነው፡፡ የዕውቀትና የጥበብ ፈተና ውስጥም ገብቻለሁ፡፡ በተለይ የሃይማኖት ሰዎች በረቀቀ ስልት የሚያቀነባብሩት ጠሊቅ ተንኮል፣ ቀድሞ ከማውቀው በላይ ሆኖብኛል፡፡ እርስ በርስ ብቻ ሳይሆን እኔንም የሚያታልልና የሚሸነግል ስለሆነ በተንኮል ልወዳደራቸው አልቻልኩም፡፡ እኔ ሰው እገድልበት ከነበረው ረቂቅ ዘዴ ይልቅ የእነርሱ ዘዴ ልቆ ተገኝቷል፡፡ … ታዲያ በምን አቅሜ ልቻላቸው?
ስለዚህ አንተ ለማንም ቢሆን እንደ ሥራው የምትከፍል ነህና፣ ምንም አማፂ ሆኜ ከመንግስትህ ብባረር፣ ከፈረድክብኝ ዘላለማዊ ፍርድ ወዲህ፣ ፍትህ ላይ ቁርጠኛ እንደሆንክ አውቃለሁና፣ ያንተ ፍጡር የሆንኩትን እኔን፣ እባክህ ታደገኝ፤ ይህንን ችግር የምቋቋምበት ኃይል ስጠኝ፣ ሰራዊት ጨምርልኝ፡፡---
አንብቦ ሲያበቃ፣ ሚካኤል፣ በመገረም፣ አንገቱን ነቀነቀ፡፡
እግዚአብሔር፤
“እስቲ ከሰው ልጆች፡- ሙሴን፣ ጴጥሮስንና ጳውሎስን ጥራልኝ--” አዘዘው ሚካኤል፡፡
ሦስቱም በአስቸኳይ መጡና ቆሙ፡፡
“በል አንብብላቸው!”
ከተነበበላቸው በኋላ ሦስቱም ተደናገጡ፡፡
“እንዴት ያለ ጉድ ነው?” አለ ሙሴ፡፡
“እና ምን ትላለህ ሙሴ?” ጠየቀው እግዜር፡፡
“የሰው ልጅ ነው ጥፋተኛው … እንዴት ከሰይጣን ጋር ያብራል፣ … እንዴት አምላኩን አንተን አይፈራም? … እንዴት ህግህን አይጠብቅም? … እንደኔ … እንደኔ -- ባልጠበቀው ህግ ልክ፣ ቅጣቱን መቀበል ይገባዋል…”
ጴጥሮስና ጳውሎስ ተንቆራጠጡ፡፡
“ጌታ ሆይ፤ ለሰው ልጅ ምህረት ይደረግለት፣ ዕድል ይሰጠው፤ አስተማሪዎች ይላኩለት፤ መንፈስ ቅዱስ ይርዳው… የሰው ልጅ ምስኪን ነው፤ አጣብቂኙ ብዙ ነው፡፡ እኔን እዚህ ያመጣኝ ምህረትህ አይደል? … ይቅርታህ አይደል! … ከሀዲውን የሚቀበልና የሚምር ልብ ያለህ ጌታ ሆይ፤ የሰውን ልጅ ይቅር በለው፡፡ ዶሮ ሳይጮህ ሶስቴ የካደውን ሰው በማርክበት ልብህ  ማረው!” ጴጥሮስ ተንበረከከ፡፡
“አምላኬ ሆይ! … እኔን አሳዳጅህን፣ እኔን ጠላትህን በደማስቆ መንገድ ተገልጠህ፣ ወደ ምህረት እንደመለስክ፣ ይህንን ህዝብ፣ መንገዱ ላይ ቆመህ መልሰው እንጂ ለዲያብሎስ አትተወው!”
ሙሴ ደስተኛ አልነበረም፡፡
“የሰው ልጅ እግዚአብሔር አምላኩን መፍራትና ማክበር አለበት” አለ ጳውሎስ”
“አባቴ ሙሴ፤ ፈተናው ብዙ’ኮ ነው፤ኑሮው፣ ትዳሩ፣ ልጆቹ ሁሉ ይፈትኑታል!”
“ከአብርሃም ለምን አይማሩም! … አንድያ ልጁን ለጌታው ሊያርድ፣ ሰይፍ የመዘዘውን ጎበዝ ለምን አያስታውሱም?”
“ሁሉ ሰው እንደ አብርሃም አይደለም!”
“እሺ ሁላችሁም ወደ የቦታችሁ ተመለሱ” አለ እግዜር፤ “ሚካኤል፤ እስቲ ለአንድ ወር ያህል ሰይጣንንና ሰራዊቱን እሰረው---- የሰው ልጅ ሕይወት ምን እንደሚመስል እየው፤ ለመሆኑ አሁን የዓለም ህዝብ ምን እያለ ነው?”
በአመፅ ተጨማልቀው፣ በጨለማ ሆነው፣ ብርሃን ውስጥ ነን ይላሉ”
“ኢትዮጵያ ምን ትላለች?” እግዜር፤ በልዩ ትኩረት ጠየቀ፡፡
“ኢትዮጵያማ ቅድስት ሀገር ነን ይላሉ፤ …ረሀብ ደጋግሞ እየቆላቸው … ሰይፋቸው ደም እየላሰ… ግፍና በደል ነግሶ… ሰው የጠንቋይ ደጅ እያጣበበ፣ መሪዎቻቸው በዘረፋ አብጠው፣ አሁንም ቅድስት ሀገር ነን ይላሉ …”
“ረሀብ ነው ቅድስና! … መገዳደል ነው ጽድቅ … መዘራረፍ ነው ክብር?....” ጠየቀ እግዜር ተገርሞ፡፡
“አዎ … በነርሱ ትርጉም ይህ ነው…. የሰይጣን ትርጉም ነው” ሚካኤል መለሰ፡፡
“በል አሁን ያልኩህን ትዕዛዝ ፈፅም፣ ለአንድ ወር ከእነ ሰራዊቱ እሰሩት …ጭፍራዎችህን ይዘህ ተንቀሳቀስ”
ቅዱስ ሚካኤል፤ክንፎቹን አወዛውዞ፣ ሰላምታ ሰጠና ተሰናበተ፡፡
*        *         *
“አሁን ስንት ቀን ሆነ - ሰይጣንና ሰራዊቱ ከታሰሩ?”
“አንድ ሳምንት!”
“ህዝቡ ምን የሚል ይመስልሃል፤ ሚካኤል?”
“ትንሽ እረፍት ያገኛል …ወዳጆችህም ያመሰግናሉ”
“ትሰማለህ የሕዝቡን ጩኸት?” አለና ሚካኤል፤ ድምጹን ለቀቀው፡፡
 “አየኸው የሰውን ልጅ---?” ሚካኤል ጠየቀ፤ እግዜርን፡፡
“ምንድነው የሚለው?” እግዜር ግራ የተጋባ ይመስላል፡፡
 “ምን ዓይነት ግራ የሚያጋባ ፍጡር ነው?... ጌታ ሆይ፤ ይህን ክፉ ህዝብ ለምን ፈጠርክ?” ተማረረ ሚካኤል።
“ተው…ተው…ሚካኤል- ግድየለህም---ታገሥ” እግዜር ትንሽ  አረጋጋው፡፡
“---ይገርማል ባልና ሚስት ፀብ አቆሙ። የሚደባደብ ሰው ጠፋ፡፡ ሌቦች ስርቆት ትተው ሰርተው መግባት ጀመሩ፡፡ ሀሜት ቀዘቀዘ፡፡ መጠጥና ዝሙት ጠፋ፡፡ ከተሞች ጭር አሉ፡፡ ጩልሌ ደላሎች አንደበታቸው ቀዘቀዘ፡፡ መሸታ ቤቶች ተዘጉ፡፡ ዳንስ ቤቶች ቤተስኪያን ሆኑ …ለዚህ ነው ህዝቡ ኑሮ ሰለቸን እያለ የሚጮኸው---አንድ ሳምንት እንኳን መታገስ አልቻለም” ሚካኤል አስረዳ፡፡
“እና ምን ይሁን?”
“በቃ ሰይጣንን ፍቱት!... የወደደ አብሮት ይቅበጥ!... ብልህ ሰው ያስተውል!.”.
ቅዱስ ሚካኤል ክፉኛ  አዝኖ አለቀሰ፡፡
“የሰው ልጅ፤ አንተ ያሳየኸው ፍቅር የሚገባው መቼ ነው?”
“እዚህ መጥቶ - ነገሮችን ሲያዩ…”
ሰይጣን በተፈታ፣ በሦስተኛው ቀን፣ ሚካኤል ከምድር ተመለሰ፡፡
“እንዴት አየኸው ምድሩን”
“እልልታ ነው፤ ፌሽታ ነው!”
“ሰይጣንስ ምን አለ?”
“እያለቀሰ ነው ጌታዬ፤ እያነባ ነው!”
“በምን ምክንያት?”
“አንድ ወር ታሥሮ ሲፈታ፣ እነ አዳም፣ የበለጠ ተንኮለኛ ሆነው ሳይጠብቁት አልቀረም!... ድሮ ሰይጣን ያሳስታል ይባል የነበረው መቅረቱን፣ ሰይጣን ራሱን፣ ሰው እንደሚያሳስተው አጫውቶኛል”
“አንተ ምን አልከው ታዲያ?” እግዜር እየሳቀ ጠየቀው፡፡
“ሳቅኩበት!...” አለና ሚካኤል መልሶ ሳቀ፤ “ቢሆንም ማመልከቻውን እንዳቀርብለት አደራ ብሎኛል!”
“ሃይል ይጨመርለታል!” መለሰ እግዜር፤ኮስተር ብሎ፡፡
ሚካኤል ሳቅ አለ፡፡ የተዋጠለት አይመስልም። ክንፎቹን አወዛውዞ፣ለእግዜር ሰገደና ወጥቶ ሄደ፡፡
የእግዚአብሔር መቅደስ፤ ውበት እንደተሞላ  ነበር፡፡

Read 5687 times