Sunday, 06 August 2017 00:00

“ቢዚ ነኝ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሐምሌም አለቀ… ዓመቱም ሊያልቅ ነው፡፡ የምር ግን… አለ አይደል… የስምንተኛው ሺህ ምልክቶች ከሚባሉት ዓመቶች አንዱ ይህኛው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ልክ ነዋ…ለምን እንደሆን እንጃ እንጂ ለብዙዎቻችን ኸረ “ጦሳችንን ይዞ ጥርግ ይበል” የሚባል አይነት ዓመት ሆኗል፡፡ መለስ ብላችሁ ምን ያህል ልብ የሚሞላ፣ ደስታ የሚሞላ፣ ተስፋ የሚሞላ ‘ደግ ነገር’ እንደሰማችሁ፣ እንዳያችሁ የሆነ አራት መደብ ሂሳብ ምናምን ነገር ብትሠሩ፣ ነገርዬው ጭልምልም ያለ ይሆንባችኋል፡፡ (‘ደግ ነገር’ የሚለው ፍቺው፣ እንደየ ሰዉ እንደሆነ ልብ ይባልማ! ዘንድሮ አንድም እንዳንግባባ፣ እንዳንደማመጥ ያደረገን ነገር…ለአንዳችን ‘ደግ’ የሆነው ለሌኛችን ‘ክፉ፣’ ለአንዳችን መልካም ሰው የሆነው፣ ለሌላኛችን ‘የሰይጣን ቁራጭ’…ብቻ ምን አለፋችሁ፣ አይደለም ክርክር፣ የመዝገበ ቃላት ፍቺ እንኳን አያስማማንም፡፡ ስናደንቅ፣ ስንወድ፣ ሰማየ ሰማያት አድርሰን፣ በወርቅ ዙፋን ላይ…ስንተች፣ ስንጠላ፣ ደግሞ ከምድር በታች፣ ነዳጅ ምናምን ከሚገኙበት በታች ቆፍረን ካልቀበርን እንቅልፍ የለንም፡፡)
እኔ የምለው… እግረ መንገዴን በሥራ ሰዓት ይሄ ሁሉ ሰው አውራ ጎዳናውን፣ ካፌውን፣ ጠጅ ቤቱን፣ የመጠጥ ግሮሰሪውን ሁሉ የሚሞላው… በየመሥሪያ ቤቱ ማን ቀረ? ደግሞላችሁ…ከምታናግሩት አሥር ሰው፣ ስምንቱ … “ቢዚ ነኝ፣” ብሏችኋል፡፡ ታዲያ... ይሄ ሁሉ ሰው ቢዚ ከሆነ፣ መንገዶቹ ሁሉ በሰው የሚጨናነቁት…ሁላችንም ከሌላ ዓለም የሚመጡ መንትዮች ወንድሞችና እህቶች አሉን እንዴ!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ለምን እንደሆን አንድዬ ይወቀው እንጂ፣ ብዙዎቻችን ከሌሎች የተለየን ሰዎች መስለን ለመታየት መከራችንን እናያለን፡፡ ‘ቢዚ’ ነና! ባንቆፍርም፣ ባናርስም፣ ባንጎለጉልም ቢዚ ነና!  ያለ ምንም ምክንያት ሥራ ከገባን፣ ስንት ቀን ሆኖ እንኳን ‘ቢዚ’ ነና!
እናላችሁ…ይቺ “ቢዚ ነኝ” የሚሏት ነገር ለሁላችንም እንደ ጆከር ካርታ እያገለገለች ነው። “ቢዚ ነኝ!”…አለ አይደል… የሆነ ትከሻ ላይ የምትደረድረው ኒሻን፣ ሜዳሊያ ምናምን ነገር ያላት ነው የምትመስለው… በማህበራዊው መሰላሉ ከፍ ብሎ መቀመጥ፡፡
የሆነ ወዳጃችን ብዙ ጊዜ የተመላለሰበትን ጉዳይ ዳር ለማድረስ፣ የሆነ መሥሪያ ቤት ሀላፊ ዘንድ ይሄዳል፡፡ ጸሀፊዋ ሥራ አስኪያጁ ሊያናግሩት እንደማይችሉ ትነግረዋለች፡፡ ቀጠሮ ተይዞለት እኮ ነው የሄደው!
“ቀጠሮ እኮ አለኝ…”
“ዛሬ ማንንም ማናገር አይችሉም፣ ቢዚ ናቸው።”
(ቸልተኞች ሆነን ወደኋላ እንዳንቀር
በሁላችንም ዘንድ ቀጠሮ ይከበር
ብሎ ነገር ዘንድሮ አይሠራም፡፡)
ቢዚ ናቸው! ወንበሩ ላይ የተቀመጡት እኮ የወዳጄን አይነት ባለጉዳዮችን ለማገለገል ነው። እና ‘ቢዚ’ ናቸው! በነገራችን ላይ “ቢዚ ናቸው፣” የተባለው ከውጪ ሀገር ከመጣ ከረጅም ጊዜ ወዳጃቸው ጋር ቢሮ ውስጥ የሆድ የሆዳችውን እያወሩ ስለነበር ነው፡፡
እናማ…“ምንድነው ቢዚ ያደረገህ?” ተብለን ብንጠየቅ ጉድ ባይወጣ ነው!
“ለአንድ አስቸኳይ ጉዳይ ፈልጌህ ነበር፣ ነገ ከሥራ በኋላ ብንገናኝ…”
“አልችልም፣ ቢዚ ነኝ…”
“ከሥራ በኋላ ነው እኮ…”
“ነገርኩህ እኮ ቢዚ ነኝ…”
“ለትንሽ ደቂቃዎች ነው፤ ጊዜህን አልወስድብህም፡፡”
“እየነገርኩህ!…ቢዚ ነኝ፡፡”
ይህን ሰውዬ ምናልባት ደሞዝ አካባቢ ከሆነ፣ የሆነ ቡና ቤት፣ የደሞዝና የ‘ሞዴል ስድስት’ ነገሮች አልፈው ከሆነ ደግሞ የጣሳ ባንዲራ የተሰቀለበት ቤት ልታገኙት ትችላላችሁ፡፡
እናማ…“ምንድነው ቢዚ ያደረገህ?” ተብለን ብንጠየቅ ጉድ ባይወጣ ነው!
የምር ግን እኮ ዘለዓለማችንን “ቢዚ ነኝ…” የምንል ሰዎች… አለ አይደል… “ምንድነው ቢዚ ያደረገህ?” ተብለን ብንጠየቅ ጉድ ባይወጣ ነው!
“እንትና እኮ በጣም ቢዚ ነው…”
“ምን እየሠራ ነው ቢዚ የሚሆነው!”
“ለሆነ ጉዳይ ደጋግሜ ፈልጌው ቢዚ ነኝ ብሎኛል፡፡”
እናማ…“ምንድነው ቢዚ ያደረገህ?” ተብለን ብንጠየቅ ጉድ ባይወጣ ነው!
እስኪ ሰው ጥሩልኝ እኔ ድምፅ የለኝም
እርቆ ከሄደ ወዳጅ አይገኝም
የሚሏት ነገር አለች፡፡ እናማ…ሁሉም ነገር የታይታ እየሆነብን፣ እህልና ገለባው ለመልቀም በሚያስቸግር መልኩ ተደባልቆብን…“እስቲ ሰው ፈልጉ” እያልን ነው፡፡
ደግሞላችሁ…
“ኃላፊውን ማናገር እፈልጋለሁ፡፡”
“ቢዚ ናቸው…”
“እባክሽ ጉዳዩ አስቸኳይ ነው፣”
“ጌታዬ፣ ቢዚ ናቸው አልኩዎት እኮ!”
እሳቸው ቢሯቸውም የሉም፣ ቤታቸውም የሉም፣ የሚታወቁ ጓደኞቻቸውም ዘንድ የሉም…ግን፣ ከከተማ ወጣ ብሎ ያለ ማረፊያ ቤት ውስጥ ምን እየሠሩ ነው!  ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ…“ምንድነው ቢዚ ያደረገህ?” ተብለን ብንጠየቅ ጉድ ባይወጣ ነው!
ደግሞላችሁ…
“ቢሮ ደውዬልህ ጸሀፊህ የለህም አለችኝ…ሞባይልህም ጥሪ አይቀበልም ነበር…”
“ቢዚ ነበርኩ…
“ይሄን ሰሞን ሥራው ትንሽ ቀሎልኛል ትለኝ አልነበር እንዴ!”
“ስብሰባ ነበረኝ…”
“የምን ስብሰባ?”
“ሥራ አስኪያጁ ቢሮ፣ የማኔጅመንት ስብሰባ ነበር፡፡”
“ሥራ አስኪያጁ፣ ከአገር ውጪ ነው ብለኸኝ አልነበር እንዴ!”
“አቦ አትጨቅጨቂኝ...ለራሴ ደክሞኛል፡፡”
“ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው ቻፕስቲከ መቀባት የጀመርከው……ወይስ የከንፈር ቀለም ለማጥፋት ነው!”
“አንቺ ሴትዮ፤ ዛሬ ጤና አልያዘሽም እንዴ!”
የመኝታ ቤቱን በር በርግዶ ገብቶ ጠርቅሞ መዝጋት!
ሰውየው ምናልባትም ከውሽሚት ጋር “እነሆ በረከት” ሲባባል አምሽቶ ሊሆን ይችላል፡፡ የእሷ ሴትዮ ነገር በቃ…‘ፐርማነንት’ ሆነ ማለት ነው! የሦስት ወር የሙከራ ጊዜዋን አለፈች ማለት ነው! እሱ ቤንች ላይ ተቀማጭ ባል ምናምን ነገር ሆነ ማለት ነው! ለነገሩ “ውሽማ ሲቆይ ባል ይሆናል” የሚሏት ነገር አትሠራም! መጀመሪያ፣ ‘ውሽማ’ የሚባለው ነገር፣ የአንድ ቀንም የአንድ ወርም ሊሆን ይችላል፡፡ ዘንድሮ ውሽማ ለመቆየቱ/ለመቆየቷ  ማረጋገጫ የለማ!
እናማ…“ምንድነው ቢዚ ያደረገህ?” ተብለን ብንጠየቅ ጉድ ባይወጣ ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5325 times