Monday, 31 July 2017 00:00

የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   • በአዳዲስ አቅጣጫዎች መጠናከሩን ቀጥሏል
                    • ከ10 በላይ ጋዜጠኞች ለዓለም ሻምፒዮናው ለንደን ይጓዛሉ
                    • አዲስ ድረገፅ ያስመርቃል
                    • የክልል ጋዜጠኞችን በሚያሳትፍ መዋቅር የመስራት እቅድ አለው

      የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በአዳዲስ የስራ አቅጣጫዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዝዳንቱ አቶ ዮናስ ተሾመ ለስፖርት አድማስ ገለፁ፡፡ ማህበሩ ከዓለም አቀፍ የስፖርት ማህበራት ጋር የላቀ ግንኙነት ፈጥሮ በመስራት አባላቱን ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብሏል። በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ከተቋቋመ ሁለተኛ የስራ ዘመኑን የያዘው ማህበሩ በዛሬው እለት ከአትሌቲክስ ፌደሬሽን አብይ ስፖንሰር ‹‹ሶፊማልት›› ባገኘው ድጋፍ ለሁሉም የስፖርት ጋዜጠኞች በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ያተኮረ ስልጠና አዘጋጅቷል፡፡ በስልጠናው ላይ የኢትዮያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኃይሌ ገብረስላሴ እንዲሁም የሶፊ ማልት እና የሄኒከን ብራንድ ማናጀር ራህዋ ገብረመስቀል በክብር እንግድነት ይገኛሉ፡፡ ስልጠናውን የሚሰጠው እውቅ የአትሌቲክስ ጋዜጠኛ፤ የአይኤኤኤፍ ዘጋቢ እና የማህበሩ አባል ኤልሻዳይ ነጋሽ ነው፡፡ በስልጠናው የዓለም ሻምፒዮናውን የሚመለከቱ ወቅታዊ መረጃዎች፤ የዘገባ ሁኔታዎችና አሰራሮችን በጥልቀት ይዳሰሳሉ፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ አጋጣሚውን በመጠቀም ለስፖርት ጋዜጠኞች ልዩ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ የሚጠበቅ ሲሆን፤ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ኦፊሴላዊ ድረገፁንም እንደሚያስመርቅ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ለንደን የምታዘጋጀውን 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ለመዘገብ ከ10 በላይ የማህበሩ አባላት  እንደሚጓዙ ለስፖርት አድማስ የጠቀሰው ፕሬዝዳንቱ አቶ ዮናስ፤  ስራ አስፈፃሚው በሁለተኛው የስራ ዘመን የመጀመርያው አንድ ዓመት ውስጥ በርካታ ጋዜጠኞችን ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ውድድሮችን እንዲዘግቡ እድሉን በመፍጠር በትጋት መስራቱን በተለይ ደግሞ የ4 ጋዜጠኞችን ሙሉ ወጭ በመሸፈን ድጋፍ መስጠቱን አመልክቷል፡፡
በሁለተኛው የስራ ዘመን ላይ የሚገኘው የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ  በመጀመርያው የስራ ዘመን የነበሩ የኮሚቴ አባላቱን ይዞ በመቀጠል ሁለት አዳዲስ አባላት ተጨምረውበት ለተጨማሪ አራት አመታት እንዲቀጥል የተወሰነው ከዓመት በፊት ነበር፡፡ ስለሆነም የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዮናስ ተሾመ፣ ፀሀፊ መንሱር አብዱልቀኒ፣ ደረጃ ጠገናው፤ የማህበሩ ገንዘብ ያዥ ቆንጂት ተሾመ ውጪ ፍቅር ይልቃል፣ ሀና ገ/ስላሴ፣ አርአያት ራያ፣ ግርማቸው ከበደ፣ ታደለ አሰፋ፣ ዳግም ዝናቡ፣ ኃይለእግዚአብሔር አድሃኖም በስራ አስፈፃሚነት ኮሚቴ እያገለገሉ ናቸው፡፡ የስራ አስፈፃሚ አባላቱ በ4 ንዑስ ኮሚቴዎች እና ሁለት ኮሚሽኖች በመከፋፈል እየሰሩም ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር የሙያተኛውን አቅም ለማጎልበት ትኩረት ማድረጉን የገለፀው ፕሬዝዳንቱ በየዓመቱ ከ4 በላይ ስልጠናዎችን ለማዘጋጀት እቅድ መያዙን ስልጠናዎቹን በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ለመስጠት እንደሚፈልግና በተለይ በክልል የሚሰሩ የስፖርት ጋዜጠኞችን በሚያሳትፉ እንቅስቃሴዎች ይሰራል ብሏል፡፡
በየዓመቱ ከዓለም ዓቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (IAAF) የሚገኙ ዕድሎች  በፍትሃዊነት ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን ለማዳረስ ጥረት እናደርጋለን ያለው አቶ ዮናስ፤  ባለፈው 1 ዓመት በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ውድድሮች ለዘገባ የተላኩ ጋዜጠኞች በየሚዲያ አውታሮቻቸው ከበፊቱ በተሻለ የሰጧቸው የዘገባ ሽፋኖች እንደሚያበረታቱ ገልጿል፡፡
በዓለም ዓቀፍ የስፖርት ማህበራት  የሚኖረውን እውቅናና የተቀባይነት ደረጃ ለማሳደግ ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር እና ከዓለም አቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ያለው ግንኙነት እየጠናከረ መጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የስፖርት እንቅስቃሴዎችና ዓለም አቀፍ ትኩረት ሊያገኙ የሚገባቸው የዜና እና የዘገባ ሽፋኖች እየበዙ ናቸው፡፡ በአገር ውስጥ ከሚገኙ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት እና አጋሮች ጋር በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች በስፋት ለመንቀሳቀስ እየሞከረ ነው፡፡ በተለይ ከኦሎምፒክ ኮሚቴው፤ ከአትሌቲክስ እና ከእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ጋር ነው፡፡
የማህበሩ አደረጃጀት የዓለም አቀፉን የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ስርዓት እንዲከተል እንፈልጋለን በማለት ለስፖርት አድማስ የተናገረው ፕሬዝዳንቱ አቶ ዮናስ ተሾመ፤ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በአፍሪካ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ያለውን ተፅእኖ ፈጣሪነት በማሳደግ አህጉራዊውን ጉባኤ ለማስተናገድ ማቀዱን ጠቁሟል፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አማካኝነት አዲስ አበባ ላይ የዓለም አቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ስራ አስፈፃሚ ልዩ ስብሰባ በአዲስ አበባ መስተናገዱ ይታወሳል፡፡  
የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በአሁኑ ወቅት ከ100 በላይ አባላት ያሉት ሲሆን፤ ከነዚህ መካከል 85ቱ ዓለም ዓቀፍ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር አባል ናቸው፡፡

Read 3224 times