Saturday, 29 July 2017 12:42

“ባህርይን ማረቅ … ከአልወለድኩ ብሎ አለመጨነቅ…”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ይድረስ ለላንቺና ላንተ አምድ አዘጋጆች ከነታዳሚዎቻችሁ እንደምንሰነበታችሁ የሚለውን ሰላምታ ያገኘነው ከአንድ አንባቢ ነው፡፡ የግል ታሪኩን የብዙዎች ሰዎች ገጠመኝ ሊሆን ስለሚችል እባካችሁ አስነብቡልኝ ብሎናል፡፡ የአምዱ ዝግጅት ክፍልም በሀሳቡ በመስማማት እነሆ ለንባብ ብሎአል፡፡
እኔ ያደግሁት በጣም ብዙ ቤተሰብ ውስጥ ነው፡፡ እናትና አባቴ አስር ልጆች ነበር የወለዱት፡፡ እኔ አራተኛ ስሆን ወንድ ለመወለዱ ግን የመጀመሪያ ነበርኩ። የእኔ ታላላቆች ሴቶች ናቸው፡፡ የሚገርመው ነገር ከእኔም በሁዋላ ወንድ አልተወለደም፡፡ ስለዚህም ስሜ የወንድወሰን ተባለ፡፡ እናትና አባቴ ሁልጊዜ የሚናገሩት ነገር ነበረ፡፡ ይኼውም እኔ ወንድ ልጅ ስለሆንኩ ከመንደር ልጆች ጋር ኳስ ስጫወት እውላለሁ፡፡ ወደእኔ ቤት ይመጣሉ ወደእነሱ ቤት እሄዳለሁ፡፡ ታዲያ እናቴ ምርር ሲላት “ምን የመንደር ውሪ ተሰበስባለህ? እዚህ ያለው ሰው መች አነሰና ነው? አርፈህ አትቀመጥም? የሁልጊዜ ንግግርዋ ነበር፡፡ እኔ ግን ልጅ በጣም እወድ ስለነበር ብቻዬን መሆን አልፈልግም ነበር፡፡ አባቴ ደግሞ በበኩሉ “እኔ በበኩሌ የምፈራው ይህ ልጅ ካለዘር እንዳይቀር ነው” ይል ነበር፡፡ በዚህ ንግግሩ እንዲያውም እናትና አባቴ ሁልጊዜ ነበር የሚጣሉት፡፡
ትዳር መያዝ አይቀርምና ጊዜው ደርሶ ተዳርኩኝ፡፡ ነገር ግን አመታት እየተቆጠሩ ሄዱ፡፡ ልጅ አልመጣም። አባቴም “ይኼውላችሁዋ… እኔ የሚሰማኝ አላገኘሁም እንጂ ብዬ ነበር” ሲል እናቴ ደግሞ “ብዬ ነበር ማለት ምን ማለት ነው? ልጅ በሰው እጅ አይሰራ…ምን ማድረግ ይቻል ነበር? መካንነቱ ከእሱ ቢሆንስ?” አባቴም “ተይ ባክሽ ይቺ… ምን ትላለች… እኔ እንደሆንኩ በዘሬም መካን የለም…. በእርግጥ ያንቺን አላውቅም…” እናቴም ትመልስና “ወገኛ ነህ እባክህ፡፡ ስለእኔ እንኩዋን አሳምረህ ታውቃለህ፡፡ በልጅቱም በኩል የሆነ እንደሆነ ዘር ማንዘርዋን አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ ወላዶች ናቸው። የራስ ልጅ ቢሆንስ መካን የሆነው? ምን ልትል ነው? ትለዋለች፡፡
የእናትና የአባቴ ንትርክ ጠዋት ማታ መሆኑን ታናናሽ እህቶቼ ይነግሩኛል፡፡ እኔ ያስጨነቀኝ ግን የእነሱ ጉዳይ አልነበረም፡፡ የእራሴ የትዳር መቀጠልና አለመቀጠል … እንዲሁም የልጅቱም ሆነ የእኔ ቤተሰቦች ፍላጎት መሟላት አለመቻሉ ነበር፡፡ ነገር ግን በቃ… አልኩና ቆርጬ ተነሳሁ፡፡ ይህ ነገር ስንፍና አይፈልግም ብዬ ከሐኪሞች ጋር መመካከር ጀመርኩኝ፡፡ ወደ ሕክምናው የሄድነው በተጋባን በ5 አመታችን ነበር። በጊዜው እኔ ማለትም ወንድየው ወደ 40 አመት የገባሁ ስሆን ባለቤቴ ደግሞ በሰላሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበረች። በእርግጥ በእነዚህ የትዳራችን 5 አመታት ለማርገዝ አስበን ባይሆንም እራሳችንን ግን አላቀብንም። ምክንያቱ ምንድነው? የሚለውን መልስ ለማግኘት ወደ ሐኪም ስንቀርብ ግን ዶክተራችን ጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንደምንገኝ እና በትእግስት እንድንቆይ  ነግሮናል፡፡ ታዲያ ብንጠብቅ ብንጠብቅ  እርግዝናው በፍጹም እውን ሊሆን አልቻለም፡፡ ብዙ ሞከርን፡፡ ግን አልተሳካም፡፡ በጣም በንዴት ለዶክተሩ እንዲህ አልኩት፡፡ “እኔ ገና የ40 አመት ሰው ነኝ፡፡ ሚስቴ ደግሞ የ32 አመት ሴት ናት፡፡ ምን ምክንያት ቢገኝ ነው የማታረግዘው?” ብዬ ጠየቅሁት፡፡ የእሱም መልስ አሁንም ጤነኛ ናችሁ ሞክሩ የሚል ሆነ። እኛ በጉጉት በራሳችን መንገድ አላማችንን ለማሳካት ጥረታችንን ጀመርን፡፡ ስንጀምረው ሁለታችንም ቶሎ እንደሚሆን አምነን ነበር። ምክንያቱም ሁለታችንም እንዋደዳለን፡፡ ባለቤቴም የእርግዝና መከላከያ ሞክራ እንኩዋን አታውቅም፡፡ እንዲያውም የወርአበባ ማስተካከያ እየተባለ ለማርገዝ ስንፈልግ በሞከርነው ሕክምና ኪኒኑን የዋጠችበት ወቅት ነበር፡፡ ምንም ቢደረግ ግን የወር አበባዋ  አይቀርም…. እርግዝና የለም። እናም ግራ ገባን፡፡ ትክከለኛው ጊዜ ሲደርስ ሊሆን እንደሚችል ለራሳችን ነግረን ጥረታችንን ኮስተር ብለን በቅንነት ቀጠልን፡፡ በኋላ ላይ ነበር ልጅ ለመውለድ የምናደርገውን ጥረት የሚያውክ ነገር በሁለታችንም መካከል መኖሩን ያመንኩት፡፡ እንዴት አወቅህ ብትሉኝ ስለጉዳዩ ማንበብ በመጀመሬ ነው፡፡ ሰዎች ልጅ መውለድ አልቻሉም ወይንም የማይችሉ ናቸው የሚባለው ካለምንም ጥንቃቄ ለአመታት ወሲብ እየፈጸሙ ነገር ግን ልጀ መውለድ ካልቻሉ እና ወይንም ቀደም ሲል የተወሰነ ልጅ ወልደው ነገር ግን ሴትዋ ድጋሚ ማርገዝ ሲያቅታት ነው፡፡ ይላል፡፡ እኛ ግን ከመጀመሪያውኑም ስላልወለድን ምክንያቱን ለማወቅ አሁንም የቻልኩትን ያህል ማንበብ ጀመርኩኝ፡፡ በዚህ ዙሪያ የተጻፉት መጽሐፎች ብዙ ነገር ይመክራሉ፡፡ ለምሳሌም፡-
የሴትዋ እድሜ በተለይም በተቻለ መጠን 29 አመት እስኪሆን ባለው ጊዜ ማርገዝ ብትችል፣
በተለያዩ ሕመሞች ምክንያት የተለያዩ መድሀኒቶችን መውሰድ፣
በወንድ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ እና እንዲሁም በሴትዋ ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች ማለትም በስነተዋልዶ አካላት ላይ ሊፈጠሩ በሚችሉ ችግሮች፣
በአኑዋኑዋር ምክንያት ሰውነት ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ አንዳንድ ጫናዎች ማለትም፡-
ቅጥ ያጣ ውፍረት፣
መጠጥ መጠጣት፣
አንዳንድ እንደ ሲጋራ ማጤስ የመሳሰሉ አጉዋጉል ባህሪዮች፣
የአመጋገብ ሁኔታ፣‘
በቂ የሆነ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ የመሳሰሉት ነገሮች ልጅ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ሊያውክ እንደሚችል ተረዳሁ፡፡
ከዚህም በመነሳት ለባለቤቴ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለየራሳችን አናቅርብ አልኩዋት፡፡ ጥያቄዎቹም የሚከተሉት ነበሩ፡፡ ምንም የጤና እክል ከሌለብን እንዴት እነዚህ ልጅ መውለድ አልቻልንም? ምንድን ነበረ ማስተካከል የሚገባን? ሰውነታችንን በትክክል ባለመጠበቃችን ነው?  ወይንስ አልኮል በመጠጣታችን ጫት በመቃማችን? እያልን ለእራሳችን ጥያቄውን ለየብቻችን መልሰን ከዚያም በጋራ እንድንነጋገር ተስማማን፡፡ መልሱ ሲመጣ ግን የሁለታችንም ሀሳብ አንድ አይነት ነበር፡፡ ሁለታችንም… ልጅ የለን …ለማን ብለን ነው? እረ ብዪ …አረ ብላ… አረ ጠጪ… አረ ጠጣ…እየተባባልን በጣም እንበላለን… በጣም እንጠጣለን፡፡ ከዚያም በሁዋላ ቅዳሜና እሁድ ከጫት የሚለየን ማንም የለም፡፡ አንዳንድ ማህበራዊ ጉዳዮች ሲገጥሙን እንኩዋን ምክንያት እየሰጠን የምንቀርባቸው ጊዜያት በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ልጅ ላለመውለድ ብቻም ሳይሆን ለራሳችንም ጤንነት ስህተትና ሊታረም የሚገባው መሆኑን አመንን፡፡
አንድ ቀን ሳንደባበቅ እንድንነጋገር ተስማማን። ከአዲስ አበባ ወጣ ብለን ማለትም ወደ ናዝሬት በመሔድ ለሁለት ቀን ቆየን፡፡ በዚያ መዝናኛ እያለን እስቲ የየሆዳችንን እንነጋገር ተባባልን፡፡ እውነታው እንደሚከተለው ነበር፡፡ እኔ ባልየው በተለይ በጣም ነበር የምበሳጨው፡፡ አባቴ እንደተናገረው መሐን ሆኜ መቅረቴ ነው…ወይኔ? እያልኩ ባለቤቴ ሳታየኝ እጅግ በጣም እበሳጭ ነበር፡፡ የሁዋላ ሁዋ ላም ባለቤቴን ሳናግራት…እኔ እኮ በየምሽቱ ከፈጣሪ ጋር እነጋገር ነበር፡፡ … ምን በድዬህ ነው ፈጣሪዬ? አረባክህ ከሰው አስተካክለኝ? እያልኩ እጅግ በጣም ነው የምጨነቀው፡፡ እንዲያውም ወሲብ ወደመፈጸም ስናመራ ለእራሴ…ምን ያደርግልኛል …ልጅ እንደሆነ አልወልድ…እያልኩ አማርራለሁ…ነበር ያለችኝ፡፡  
በሁኔታው እጅግ ተገርሜ እና አዝኜ ነበር ብድግ ብዬ ያቀፍኩዋት፡፡ ከዚህ በሁዋላ ለእኔ አንቺ እንደ ልጄ ነሽ የምቆጥርሽ … በቃ እርም ያድርግብኝ… ሁለተኛ ስለዚህ ነገር ብናስብ እግዚአብሔር ይፍረድብን አልኩዋት፡፡ እሱዋም እኔ ላንተ እያዘንኩ ነው እንጂ የምሰቃየው የምወድህ ባሌ ወንድሜ ስለሆንክ አንተን ካልከፋህ አረ እኔ ሁለተኛ ስለዚህ ነገር አላስብም አለችኝ፡፡ በዚህ ጊዜ ከተጋባን ወደ ስምንት አመት ሆኖናል፡፡ ሁለታችንም ስለወደፊቱ አኑዋኑዋራችንን ለእራሳችን ስንል ሁኔታዎችን እናስተካክል በሚለው ተስማምተን …አንዳንችን ለአንዳችን ቃል ገብተን በሙሉ ልብ በፍቅር ካለጭንቀት እንደ አዲስ ፍቅረኛ ተቃቅፈን አደርን፡፡ ወደቤታችንም ስንመለስ ያንኑ ቀጠልን፡፡ አዲስ ሕይወት ጀመርን፡፡  ልብ በሉ ብቻ፡፡ ይህ በሆነ በሶስተኛ ወሩ የወር አበባዋ ቀረ፡፡ አረ ተይው …አረ ተወው… እያሾፈብን ነው፡፡ ይልቅስ ሕመም እንዳይመጣ ታከሚ አልኩዋት፡፡ በሁለተኛውም ወር አልመጣም፡፡ ሕመም እንዳይሆን ፈርቼ ወደሕክምና ብወስዳት የምርመራው ውጤት እርግዝና ነው ተባለ፡፡ እኔና ባለቤቴ ተገርመን አሁንም ተነጋገርን፡፡ ከሆነ ይሁን ካልሆነም የራሱ ጉዳይ ብለን እራሳችንን ቅጥ ካጣ ደስታ ገደብን፡፡ ነገር ግን ሐኪማችንም እንደመሰከረው በመነጋገርና ጭንቀትን በማስወገድ ብቻ…እነሆ ዛሬ የሶስት ልጆች እናት እና አባት ነን፡፡ የመጀመሪያዋ ልጃችን ዘንድሮ ስምንተኛ ክፍልን ተፈተነች፡፡ ስለዚህ ኑሮን በአቅም ከማስተካከል …ባህርይን ከማረቅ ጀምሮ ወለድኩ አልወለድኩ ብሎ አለመጨነቅ ልጅ ለማግኘት ይረዳል፡፡

Read 1261 times